የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ /24/

አትበላሉ
“ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ” /ገላ. 5፡15/።
አንዲት ቤተ ክርስቲያን በኬልቄዶን ጉባዔ ለሁለት ተከፍላ ምዕራብና ምሥራቅ፣ ካቶሊክና ኦርቶዶክስ ተብላ ተለያይታለች።። ይህን መለያየት ተከትሎ እስልምና ተነሣ። በመቶ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከመካከለኛው ምሥራቅ ተነሥቶ ሰሜን አፍሪካን የወረረው ክርስቲያን ከእስላም ጋር ወግኖ ወንድሙን በመውጋቱ ነው።። እርስ በርስ ስንበላላ የሚሳለውን ሰይፍ እየረሳን ነው። ልጆቻችንን እንኴ በሰይፍ ሲቀሉ እያየን ለቀጣዩ አላሰብንበትም። በየአብያተ ክርስቲያናቱ መድረክ የሚነገረው የእርስ በርስ ጥላቻ ነው። እንኴን ወንድምን ጠላትንም መጥላት አይገባም። እርስ በርስ እንደ ዶሮ እየተነካከስን ስንት ዓይን አፈሰስን። እንደ ውሻ እርስ እየተበላላን ስንት አጥንት ሰበርን። ግላዊ ጠባችንን ብሔራዊ፣ ቅንዓታችንን ሃይማኖታዊ አደረግነው። ጠላት ቢመታን ቅርንጫፋችንን ዘነጠፈው። እኛ ግን የወንድማችንን ሥሩን ለመንቀል ታገልን። ከአላውያን ነገሥታት የሚነሣው ስደት ቤተ ክርስቲያንን ሲያለመልማት አይተናል። ቤተ ክርስቲያንን አከርካሪዋን የሚመታት የእርስ በርስ ፍጅት ነው። አንድ እንኴ ተዉ የሚል ጠፍቶ፣ አባቶች የልጆቻቸውን ጠብ የዶሮ ጠብ ያህል እንኴ ለምን እንዳልቆጠሩት ከማሰብ በላይ ነው።
አንድን ሰው ለማጥፋት የምናሰማራው ሠራዊት መጠኑን የጠበቀ አይደለም። አንድን ሰው ለመደምሰስ የምንጠቀመው ማንኛውም መሣሪያ እግዚአብሔር በዚህ ሰማይ ላይ መኖሩን የሚያምን ሰው የሚያደርገው አይደለም። ውሻ ለምንድነው የሚነካከሰው? ቤቱን መጠበቅ ሲሰንፍ ነው። ራሳችንን መጠበቅ ሲሳነን፣ ንስሐን የጠላንበት ፀፀት ሲያሰቃየን የጠብ ርእስ መፍጠር ተገቢ አይደለም። በቤተ ክርስቲያን የሚያጣላ ምድራዊ ርስት የለም። ሁላችንን የተሸከመ ጌታ ነው። ማንም ማን ሊከብደው አይገባም። ማንም ስለ ማንም አይጠየቅም። የሚፈርደው በዙፋኑ አለ። ተኮናኝ ሳለን ኮናኝ ማን አደረገን?
ወልዳ የምትበላዋ ድመት በቤተ ክርስቲያን ትንጎማለላለች። ዛሬም ወልደው የሚበሉ እየተንጎማለሉ ናቸው። ትላንት ያስተማርናቸው፣ ትላንት የመሰከርንላቸው፣ ትላንት ጸጋቸውን ያደነቅንላቸውን ዛሬ ስንሳደብ እግዚአብሔርን ባንፈራ ይሉኝታ ሊይዘን ይገባ ነበር። ፍቅራችንን ዓለም ይስማልኝ አላልንም፣ ጠባችንን ግን ዓለም ይስማልኝ ብለናል። ለእኛ ትልቁ ፍቅር ሳይሆን ጥላቻ ነው። የመበላላትና የመነካከስ መጨረሻው መጥፋት ነው። የክርስትና መዲና የነበሩት እን አልጀሪያ፣ ሊብያ፣ ግብጽና ሱዳንን ስንመለከት መለያየት የጠላት ጉልበትና የእኛ ጥፋት መሆኑን እንረዳለን። ልንጣላ እንችላለን፣ መጠላላት ግን ተገቢ አይደለም። አሳብን መቃወም ይቻላል፣ የሰውን ሰብእና ለመቃወም ግን ማን ሥልጣን ሰጠን? እኛን የእግዜር ቀጪ ያደረገን ማን ነው? ይህ እግዚአብሔርን መካድ ነው። መንግሥተ ሰማያትን የመውረስ አሳብ ካለን ዛሬ የምንጠላውን ወንድማችንን ነገ ለዘላለም አብረነው እንደምንኖር ማሰብ አለብን።
በእኛ መበላላት፣ ነውረኛ ንግግራችን ሰዎች ተሰናክለዋል። ገበሬ የሚያጭደው በዘራበት መሬት ላይ ነውና በዚሁ ዓለም ላይ የዘራነውን እናጭዳለን። መለያየት ጥፋትን እንደሚወልድ በሮብአም ዘመን የተለያዩት እስራኤል ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዓለም ላይ ተበትነው ቀርተዋል። እግዚአብሔር ልቡናችንን ይመልስልን። ሰላም እየረበሸን ከሆነ ምን ዓይነት መንፈስ እንደሆነልን መመርመር አለብን። መለኮት ያግዘን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ