የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(28)

ተገጣጠሙ

“እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም። እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፤ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል” (ኢዮ. 41፡8)።

ጻድቁ ኢዮብ በብዙ መከራና ፈተና ውስጥ አለፈ። እናጽናናለን የሚሉ በቃል ብዛት አደከሙት። የተሰወረ ኃጢአት ቢኖርብህ ነው አስታውሰህ ተናዘዝ አሉት። ኃጢአት ክፉ ነገር ነው። ክፉ ነገር ሁሉ ግን ኃጢአት አይደለም። በሽታ ክፉ ነገር ነው፣ በሽታ ሁሉ ግን ኃጢአት አይደለም። እንደ ኢዮብ እምነታቸው እንዲገለጽ ክፉ የሚደርስባቸው ሰዎች አሉ። በዮሐንስ 9 ላይ እንደምናገኘው ዓይነሥውር የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጥበት ጉድለት አለ። ከጸጋቸው የተነሣ እንዳይታበዩ ለቅዱሳን የሚሰጥ በሽታም አለ(2ቆሮ. 12፡7-9)። ዛሬ ሁሉን ክፉ ነገር ከኃጢአት ጋር የሚያያይዙ ክርስቲያን ፈሪሳውያን አሉ። ይህ መመጻደቅ፣ እኔ ንጹሕ ነኝ የማለት ውጤት ሲሆን የእግዚአብሔርንም ፍቅር አለመረዳት ነው። ኢዮብ በቁስሉ ላይ ጥዝጣዜ የሆኑበት የሚያጽናኑ የመሰላቸው አቁሳዮች ናቸው። በመከራችን ላይ ፈሪዎችን አለማማከር መልካም ነው። መከራው ካለፈ በኋላም አይረሱትምና ያባንኑናል። ተመጻዳቂዎችን አለመጥራትም መልካም ነው፣ ይፈርዱብናል፤ ብዬ ነበር የሚለውን ነቢይነታቸውን ያበዙብናል። በመከራችን እግዚአብሔርን መጠጋት መልካም ነው። እርሱ ብቻ ያዝንልናል።

የኢዮብ ባልንጀሮች ስተው ኢዮብን አሳቱ። ብዙ መልካም የሚመስሉ ቃሎችን ግን እውነት የሌላቸውን ቃሎች ወረወሩ። እግዚአብሔርም በመጨረሻ ተናገረ። ለምን እንዲህ እንደሆነ ማብራሪያ አልሰጠም። የበላይ የለበትም። በፈጠራቸው ፍጥረታት ምሳሌነት ግን ከአእምሮ በላይ መሆኑን ገለጠ። ከምሳሌው አንዱ አዞ ነው። የአዞን ጥንካሬ በገለጠበት ክፍል ስለ ጥርሶቹና ስለቅርፊቶቹ ሲናገር፦ “እርስ በርሳቸው የተቀራረቡ ናቸውና ነፋስ በመካከላቸው መግባት አይችልም። እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ናቸው፤ እስከማይለያዩም ድረስ ተያይዘዋል” ይላል።

ነፋስ ለማለፍ ጥቂት ክፍተት ብቻ ይፈልጋል። ለዚህ ነው ቤቱን ጠቅጥቀን ነፋስ የሚገባው። ነፋስን እንኳ ማስገባት የማይችል መቀራረብ ለእኛም ያስፈልጋል። አንዱ አንዱን አሳልፎ የማይሰጥበት፣ የኔ እህት የእኔ ወንድም ይህን አያደርጉም የምንልበት ወኪልነት ያስፈልገናል። ወዳጅ ማለት በሌለንበት ስፍራ እኛን ከእኛ በላይ የሚገልጥ ነውና። ክፍተት ብናይ እንኳ ልንደፍን፣ ያየነውን ሌላ እንዳያይ መሸፈን ያስፈልጋል። ወዳጃችንን አለማሳማት ሐሜትን ማስቆም መቻል አለብን። በዓይናችን የምናውቀውን ወዳጅ በጆሮአችን መፈለግ ተገቢ አይደለም። የመጠጥ ዕድሮች እንኳ ወዳጃቸውን አያስነኩም፣ መንፈሳውያን ግን ወዳጃችንን እናሳማለን። ነፋስ እንኳ እስከማይገባ በመካከላችን ክፍተት መፍጠር አይገባም። ሰው ሁልጊዜ አብሮ ላይኖር ይችላል። ጠባችንንና ፍቅራችንን በግላችን መጨረስ ጨዋነት ነው። በዛሬው ዘመን መልካም ፍቅር ብቻ አይደለም መልካም ጠብም እየጠፋ ነው። ጥሩ ጠብ የፍቅር ያህል ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ስንጣላም እንደሚታረቅ ሆኖ መጣላት ይገባል።

እስከማንለያይ ድረስ መገጣጠም አለብን። ወዳጅነታችንን ቀን ማሳለፊያ፣ በማንኛውም ጊዜ የምንጥለው ተጠባባቂ ጉዳይ ልናደርገው አይገባም። በእውነት ቃል ኪዳን ያለው ወዳጅነት ያድለን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ