የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(31)


አትተማሙ

“ወንድሞች ሆይ፥ እርስ በርሳችሁ አትተማሙ።ወንድሙን የሚያማ በወንድሙም የሚፈርድ ሕግን ያማል በሕግም ይፈርዳል… በሌላው የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?” (ያዕ. 4፡11)።

ሐሜት ሌላውን በክፉ ማንሣት፣ ባለቤቱን በሌለበት ቦታ እንዲነሣ ማድረግ ነው። ሐሜት ዘዴው ከፍ ሲልም ስለ ሌላው በጣም አድንቆ በማውራት ሌሎችን ለክፉ የሚያነሣሣ ነው። ሐሜት እያደገ ሲመጣ ልጁን፣ ትዳሩን፣ ንጉሡንና እግዚአብሔርንም ያማል። ሐሜተኛ ራሱን እንደ ሕግ አስከባሪ ስለሚያይ ሕግን መጠበቅ እንዳለበት አያውቅም። ክርስቲያን አበሳን የሚሸፍን እንጂ ያየውን ለማሳየት የሚጨነቅ አይደለም። እንኳን እግዜር የመከረው ጨዋ ያሳደገውም አየህ? ሲሉት አላየሁም የሚል ነው። ሐሜት በዛሬ ዘመን የዳቦ ስም አግኝቶ መረጃ ይባላል። የድሮ ሐሜት ቡና ላይ ነበር፤ ዛሬ ቡና በሌለበት ያለ ማጣቀሻ በኢንተርኔት የሰው ሥጋ እያወራረድን ነው። ሥልጣኔ ክፋትን ማፋጠኛ ሆኗል። ሌሎች ስንት ንግድ በሚያካሂዱበት በሚያስተምሩበት ሥልጣኔ እኛ እንተማማለን። እንከስራለን። ከቃል ሐሜተኛነት ወደ ጽሑፍ ሐሜተኝነት አድገናል። ሐሜት ግን አያሸልምም።

ሐሜትን የሚወልደው የበታችነት ሥቃይ ነው። ሰውዬውን ዝቅ አድርጎ ሲያማው ከእርሱ እኩል የሆነ ይመስለዋል። ሌላው ሐሜት በቀልም ነው። ሰውዬውን ወዳጅ ማሳጣት ነው። ለሐሜት በጀት ያላቸው የሚጋብዙ፣ ተሳፍረው የሚሄዱ ብዙ ናቸው። ከማደጋቸው ይልቅ የሌላው መውደቅ የሚያስደስታቸው እየፈሉ ነው። ገንዘብ ብንሰርቀው እንጠቀምበት ይሆናል፣ ክብር ግን አይሰረቅም። ሌላውን ባዋረድን ቁጥር ሰው እየናቀን ይመጣል። ሐሜት ሰውዬው ሲመጣ ፍቅር ይሆናል፣ ሰውዬው ሲሄድ ጠብ ይሆናል። ሐሜት ሽማግሌ የማይገባበት ጠብ ነው። ሐሜትን የሚወልደው ሌላው ነገር የግልጽነት ችግር ነው፣ ይህ ብቻ አይደለም የሚመለከተንን ለይተን ያለማወቅ ችግር ደግሞም ሥራ ፈትነት የሚወልደው ነው። ሐሜት መናገር ብቻ አይደለም መስማትም ነው። ሰሚ ባይኖር ተናጋሪ የለምና  ትልቁ ሐሜተኛ ሰሚ ነው። እሺ፣ አይገርምም፣ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው እያሉ ሐሜቱ ጅቡቲ እንዲደርስ ሀዲድ የሚዘረጉ አሉ። ሲጋራን ከሚያጨሰው አጠገብ ሆኖ የሚያሸተው ይበልጥ ተጎጂ ነው። ሐሜትም የሚሰማውን ይበልጥ ይጎዳል። ኅሊናው ይቆሽሻል፣ ለሰው ያለው ክብር ይቀንሳል፣ ፈሪና ተጠራጣሪ ይሆናል።

ሐሜት ሁለንተናን ይይዛል። ሐሜተኛ ሲያወራ ዓይኑ ይገላመጣል፣ ኮቴ ሲሰማ ይረበሻል። ሲራመድ አንድ ነገር ብሰማ ባይ ብሎ ሹክክ ይላል። ኮቴው አይሰማም። ባጠቃላይ ነጻነት ያጣል። ሐሜተኛ የጠብ ደቦ የሚፈልግ ነው። ጠልቻለሁ ጥሉ የሚል ነው። ሐሜት የሚነግሩን የናቁን ናቸው። ሐሜተኛ የሰው ልክ አያውቅም። … ሐሜተኛ ሲመጣ ሁሉም ፀጥ ይላል። ከተማው እንዲሰማው የሚፈለግ ነገር ካለ ለእገሌ ንገሩ ይባላል። የግል የሬድዮ ጣቢያ ነው።

ቅዱስ ያሬድ ስለ እውነተኛው ጾም ሲናገር አፍ ይጹም ብሏል። የበሬ ሥጋ የሚጾሙ የሰውን ሥጋ ግን ያለቢላዋ የሚያወራርዱ ብዙዎች ናቸው። ሐሜት ግን ቅበላና ፋሲካ የሌለው ጾም ነው። ሐሜት አቅሙን ስለማያውቅ ንጉሥንም ሲያማ ይውላል። ራሱ ግን ትዳሩን መምራት አቅቶታል። የራስን ኃጢአት መናዘዝ ንስሐ ነው፣ የሌላውን መናዘዝ ግን ሐሜት ነው።

ሐሜት መፍረድ ነው። ፈራጅ ደግሞ ሕግን አይጠብቅም። የሚፈርደውን ጌታ የለህም እያለ ነው። መፍረድ እግዚአብሔርን መካድ ነው። ቅጣቱም በፈረድንበት ውድቀት መገኘት ነው። ቀኝ እጅ ግራ እጅን ቆሰለ ብሎ አያማውም። እንዲድንለት ይመኛል፣ ይረዳል እንጂ። እኛ አካል ነንና መተማማት አይገባንም። እግዚአብሔር ይህን እየተስፋፋ ያለውን የሐሜት በሽታ ይንቀልልን። ይቅር ይበለኝ ይቅር ይበላችሁ!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ