የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(35)


አትከፋፉ
“እርስ በርሳቸውም እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ” (የሐዋ.15፡39)።

የጳውሎስና የበርናባስ የወንጌል ቡድን ማርቆስን አስከትሎ ይጓዝ ነበር። በአዲስ ስፍራ ቤተ ክርስቲያን እየተከሉ፣ የተከሉትን ደግሞ ተመልሰው እያጸኑ ምድርን በወንጌል ያርሷት ነበር። በእንዲህ ያለ መፋጠንና ሩጫ ላይ ሳሉ ማርቆስ ወጣትነቱ ተጭኖት ጵንፍልያ በምትባል ስፍራ ቀረ። ከእነርሱ ጋር ለወንጌል ሥራ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነም። ጳውሎስ በዚህ ቸልታ ልቡ አዘነ። በርግጥም ባሻገር እያሳመኑ አጠገብ ያለው አለማመኑ ያሳዝናል። የወንጌልን ሥራ አንገብጋቢ ያደረገው ከኋላ የክርስቶስ ሥቃይና ሞት ከፊት የሚመጣው ፍርድ እየታሰበ ነው። ይህን የሚያስብ ሰው እንኳን ለመቅረት ለመዘግየት ይጸየፋል። ማርቆስ ግን በወጣትነት ተታሎ ከዚህ የወንጌል ቡድን ተለየ። ጳውሎስ ልቡ ቆረጠ። በርናባስ ግን መጨከን አልቻለም። በዚህ ጊዜ ማርቆስን እናስከትል በሚል አሳብ ሁለቱ ወንጌላውያን እስኪለያዩ ድረስ ተከፋፉ። በርናባስም ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። ጳውሎስም ሲላስን መርጦ ወደ ሶርያ ሄደ። ሳያስቡትም ሁለት የወንጌል ቡድን ተፈጠረ። እግዚአብሔር ለበጎ አደረገላቸው።

ግዴለሽ በሆኑ ደቀ መዛሙርት ላይ ያለን ሁለት ዓይነት አመለካከት አገልግሎትን ለሁለት ይከፍላል። አባትና እናት በልጃቸው ስህተት ላይ ሁለት ዓይነት አቋም ሲይዙ ልጁ አይለወጥም የእነርሱም ኅብረት ይፈተናል። ከወንጌሉ አገልግሎት ይልቅ የእኛ ወዳጅነት የበለጠባቸውን ወደ መስመሩ ማምጣት ይገባል። እነዚህ ሰዎች በማንኛውም ስላች ይታጠፋሉ። ደስ ሲላቸው እኛን አባብለው ይመለሳሉ። በእነዚህ ወጣትነት በተጫናቸው ምእመናን ላይ ይቅርታ የሚመስል ቸልታና ቆራጥነት የሚመስል ጭካኔ እንዳናሳይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እነዚህ ለመብል የደረሱ ለሥራ ያልደረሱ ምእመናንን በጥንቃቄ መያዝ ይገባል። የበርናባስ ልበ ሰፊነት ማርቆስን ያህል ወንጌላዊ ከማጣት አድኖናል። ምእመናን ሆይ የቅዱሳን ልብ ሳይቀር ሊሻክር እንደሚችል እያወቃችሁ በትሕትና ተገዙ። የእግዚአብሔርን መንገድ ያሳዩአችሁን አክብሩ። እንኳን የሰማይን መንገድ የፒያሳ መንገድ በዚህ በኩል ነው ያለ ሰው ውለታው አይረሳም።

በእግዚአብሔር አገልጋዮች መካከል መለያየት እስኪሆን ድረስ መከፋፋት እየሆነ ነው። ያልቦካ ጭቃ ሰው ላይ እየለጠፉ፣ በደም እየታጠቡ ማገልገል ቀላል ጉዳይ ሆኗል። ሩኅሩኁን ጌታ እየሰበኩ በጭካኔ መመላለስ ተለምዷል። የአንድ ደብር ዘበኛ ተከሰው አለቃው ጋ ቀረቡ። “ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ለምንድነው የማይሳለሙት?” ቢባሉ ” ሰው መሥሪያ ቤቱን እንዴት ይሳለማል?” ብለዋል። አገልግሎትም ሕይወት ወይስ መሥሪያ ቤት? አገልጋይ በአገልጋይ የሚወረውረውን ቀስት ያላመኑ እየወረወሩ አይደለም። ለዚህ የሚያደርስ ምን ነገር አለ? ልመን ብሎ ዕዳ አለ ወይ? ደግሞም ምድር ሰፊ ናት። ወንጌልን ያልሰማ እልፍ ነው። ነጭ በለበሰ ከተሜ ከመጣላት በደም ልብሱ ባሸበረቀው ጌታ መፋቀር ይሻለናል። የምናነበውን እንድናስተውለው መንፈስ ቅዱስ ያግዘን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ