ብዙዎች ፍቅርን በሚመለከት ዝግ በር ናቸው፣ ቸርነትን በሚመለከት ግግር በረዶ ናቸው። ክርስቲያን እስኪወዱት አይጠብቅም፣ ቀድሞ ይወዳል። ፍቅሩም የቃላት ሳይሆን የተግባር ነው ። እርዳታውም ከንፈር መምጠጥ ሳይሆን መቆረስ ያለበት ነው። ለተጨነቁ ሰዎች የፀጥታ ሰዓቱን ይሠዋል። ጊዜዬ የእግዚአብሔር ነው ብሎ ስለሚያስብ የእኔ የሚል ጊዜ የለውም። ሕይወቱንም ለፍቅር ለመስጠት አይሰስትም:: ብዙዎችን ያነቃል። የዓለም የነጻነት ትግል ሁሉ ከክርስቲያን ውጭ አይደለም። የተኛውን ሊጥ እርሾው ያንቀሳቅሰዋል። ክርስትና ምቾትን በመረበሽ የታወቀ ነው። ግፍን ያወግዛል፣ ጭካኔን አይታገሥም፣ ለተጠቁት ዋስ ይሆናል። ሰዎችን ከአንበሳ ጋር እያታገሉ ይዝናኑ የነበሩ የሮም ቄሣሮች የቆሙት በክርስትና የለውጥ ግፊት ነው።
ዛሬም ሕዝብን ከኑሮ አንበሳ ፣ ከበሽታ ነብር ጋር እያታገሉ የሚዝናኑ ነገሥታትን ዝም አይልም። ባሕልን፣ ሃይማኖትን፣ ክብርን፣ ሥነ ምግባርን የሚበክል ሲመጣ እንደ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከፊት መቅደም የክርስቲያን ተግባር ነው። ጣዖታዊነት፣ የሰውን ተፈጥሮ የማይመጥን አምልኮ ሲስፋፋ ክርስቲያን አይቶ እንዳላየ አያልፍም። ቄሣሮች ሐውልታቸውን አቁመው መመለክ ሲያምራቸው አማኙ አይታገሥም። በካንሰር፣ በደም ግፊት፣ በአደጋ የምታበቃዋን ትንፋሽ ለሰማዕትነት ያውለዋል። አማኝ መግደል ባይችልም መሞት ግን ይችላል።
እርሾ በውስጥ ይሠራል
በፈርዖን ቤተ መንግሥት ሙሴ ነበረ፣ በአክአብ ቤተ መንግሥት ነቢያትን የሚታደግ አብድዩ ነበረ፣ በፋርስ ቤተ መንግሥት አስቴር ተሰውራ ነበር። እጅግ የተሰወረው መርዶክዮስ አይሁድን ከጥፋት ያዳነ ነው። የሚታዩትን ያፈሩት የማይታዩት ናቸው። የሙሴን እናት አናውቃትም፣ ሙሴን ግን ለዚህ ክብር ያበቃች ናት። መንፈስ ቅዱስ ይሠራል፤ የሚሠራው ግን ሳይታይ ነው። የሚታየው ዓለም መገኛ የማይታየው ነው። አሳብ በዓለም ላይ ትልቁ ኃይል ነው፣ አሳብ ግን አይታይም። እርሾም ሳይታይ ይሠራል። ያለ ማቋረጥ ይንቀሳቀሳል፤ ሌሎችንም ያንቀሳቅሳል። አማኝ ሌላውን ለጸሎት፣ ለተጋድሎ፣ ለፍቅር፣ ለወንጌል ተልእኮ ያነሣሣል። አደባባዩን ሁሉ ይመኘዋል ፣ ትልቁ ሥራ ያለው ግን በስውር ነው። ወታደር ቢዋጋም ድሉ ያለው በማይታየው የጦር ሰፈርና ደጀን ላይ ነው። እያንዳንዱ የአደባባይ ስኬት ከጀርባ የማይታየው የእናት ጸሎት፣ የሚስት ጥሩነት አለበት።