እስፓኒሾች፡- “እሳትና ውኃ ጦርነት ቢገጥሙ የሚሸነፈው እሳቱ ነው” ይላሉ ።
አባባሎች የኑሮ ጭማቂ ናቸው ። አባባሎች ሰፈፍ የሌላቸው ወለላዎች ናቸው ። አባባሎች የአንድ መጽሐፍ አሳብን በአንድ መስመር የያዙ ናቸው ። አባባሎች ሩቅ መንገድ የሚሄድ ሰውን ደግፈው የሚይዙ ትንንሽ የምግብ እንክብሎች ናቸው ። አባባሎች እያስደነቁ የሚያስተምሩ ፣ እየጣሙ የሚበሉ ናቸው ። አባባሎች በጥበብና በዕድሜ ከሸመገሉ ሰዎች የሚገኙ ሀብት ናቸው ። አባባሎች የአገርና የሕዝብ ስም ማስጠሪያ ናቸው ። ኢትዮጵያውያን አንዲህ ይላሉ ፣ ስፓኒሾች እንዲህ ይላሉ ይባላል ።
ጥበብ በሁሉ አገር ፣ በሁሉ ዘመን ፣ በሁሉ ትውልድ ፣ በሁሉ ቤት አለ ። እግዚአብሔር በተፈጥሮ ፣ በዕለት ገጠመኝ ፣ በልቡና ምሪት ፣ በመከራ ፣ አብሮ በመኖር የሚያስተምረው ትምህርት አለ ። መደበኛ የእግዚአብሔር የማስተማሪያ ዘዴው ግን በቃሉ በኩል ፣ በመምህራን አንደበት ነው ። እኛ ኃጢአተኞች የምንልበትና እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን የሚጠራበት ድምፀት ልዩነት አለው ። እኛ ይጸድቃሉ የምንላቸውና እግዚአብሔር ይጸድቃሉ በሚላቸው መካከል ልዩነት አለ ። እግዚአብሔር በእኛ ዓይን ምስኪኖችን ሊያይ ይችላል ። በእኛ ዓይኖች ዓይቶ ግን ኃጢአተኞች ላይ አይፈርድም ። እግዚአብሔር ዓይናችንን የፈለገው የተራቆቱትን እንድናጋልጥበት ሳይሆን እንድንሸፍንበት ነው ።
እሳት በአዎንታዊ መንገድ ሲገለጥ ተነሣሽነትን ፣ ትኩስነትን ፣ ወጣትነትን ፣ ባለ ራእይነትን ፣ ባለ ስጦታነትን ያመለክታል ። አብ እሳት ነው ፣ ወልድ እሳት ነው ፣ መንፈስ ቅዱስ እሳት ነው በማለት ስለሚያድነው አንድ እሳት ቅዳሴ እናቀርባለን ። እሳት በአሉታዊ መንገድ ሲገለጽ ቍጣን ፣ በቀልን ፣ ችኩልነትን ፣ የዓመቱን በዕለት ላጥፋ ማለትን ፣ አለመታገሥን ፣ ስሜታዊነትን ፣ መንቀልቀልን ፣ ንዴትን ፣ አበድ አበድ ማለትን ያመለክታል ። እሳትና ውኃ በረከት እንደሆኑ ጥፋት ሲሆኑ ጉዳታቸው የጥቅማቸውን ያህል ነው ። የዓለም ኑሮ እየተጓዘ ያለው በእሳትና በውኃ ነው ። እሳትና ውኃም ይህችን ዓለም እያጠፋ እንደሆነ እናያለን ። የሚጠቅሙ ነገሮች በቅጡ ካልተያዙ የሚያጠፉት የጥቅማቸውን ያህል ነው ። ሰው ሁልጊዜ የሚሰጋው የሚጎዱ ነገሮችን ነው ። የሚጎዱ ነገሮችን ስለሚጠነቀቅና መፍትሔ ስለሚፈልግባቸው ያን ያህል አይጎዱም ። የሚጠቅሙ ነገሮች ግን ጥበቃ ካልተደረገላቸው የሚጎዱት ያን ያህል ነው ። በጣም መልካም ሰዎችን አክብረን ካልያዝን ለመልካምነት ያዋሉትን ኃይል ለክፋት ሲጠቀሙበት በእጥፍ ይጎዱናል ። የባንኮችን ሥርዓት የሚሰብሩ ሰዎችን ይዘው ከፍ ባለ ገንዘብ ይቀጥሩአቸዋል ። የኮምፒዩተር ቫይረሶችን የሚፈጥሩ ሰዎችን ይዞ መጠቀም ዓለማውያን የደረሱበት ዘዴ ነው ። ክፉ የሚሠሩትን ለበጎ መቅጠር አስፈላጊ ነው ፤ መልካም የሚሠሩትን ማበረታታት ክፉ እንዳይሆኑ የሚያግዝ ነው ። ክፋት ትንሽ ኃይል የሚፈልግ ነው ። ክፋትም ክፋት የለበትም ፣ ማለትም ፈታኝ የለበትም ። መልካሞች ክፋት ከጀመሩ ግን በብዙ አቅምና በብዙ ፈተና ደግ ማድረግን ችለዋልና ቀሏቸው ክፋትን ይፈጽማሉ ። እባካችሁ መልካሞችን ተንከባከቡ ።
በሰላም ዘመን እሳት ውኃን በእርጋታ ያሸንፈውና ያሞቀዋል ። ውኃም ቅር ሳይለው በረዶነትን እያፈረሰ ፣ ቅዝቃዜን እየሻረ ፣ ለሰስ ወደ ማለት እያደገ ፣ እየሞቀ ፣ እየፈላና እየተንተከተከ ይመጣል ። እሳት በእርጋታ ውኃን ባልንጀራው ያደርገዋል ። እሳት ውኃን ባልንጀራው የሚያደርገው ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሳይሆን በድስትና በማፊያ ተከልሎ ነው ። በአልችልም ባይነት በረዶ የደደሩ ፣ ተስፋ በመቍረጥ ቅዝቃዜ ውስጥ የሚኖሩ ፣ ነውም አይደለምም ለማለት በመቸገር ለሰስ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ ። ሁሉን የሚጠራጠሩ ፣ አልሰማም ፣ አላይም በሚል መርሕ ራሳቸውን የሚጠብቁ ቍጥራቸው ጥቂት አይደለም ። እነዚህን ሰዎች ከበረዶ ድንጋይነት ፣ ከቅዝቃዜ ሬሳነት ፣ ከለብታ ሚና የለሽነት የምናድናቸው ቀስ ብለን ነው ። እውነቱን ሳይጠሉት እኛን ግን ላይወዱን ይችላሉ ፣ ሐቁን ሳይቃወሙ አቀራረባችንን ግን ላይፈቅዱት ይችላሉ ። እሳትነታችን ውኃ እንዳይሆን ከመጋፈጥ በምን መንገድ ላተርፋቸውና ባልንጀራ ላደርጋቸው እችላለሁ ማለት ይገባል ። እሳት አይጨበጥም ፣ በሙቅ ውኃ ግን ይጨበጣል ። ተዋሕዶው ግን ድልድይ ያስፈልገዋል ያ ድልድይ ውኃን የሚሰፍር ፣ እሳትን የሚችል መሆን አለበት ።
በጦርነት ዘመን ግን እሳቱ በውኃው ይሸነፋል ። እሳት ውኃን ሲያሞቀው ቀስ እያለ ፣ እያሳመነ ነው ። ውኃ እሳትን ሲያጠፋ ግን እያዋከበ ነው ። እሳቶች ወደ ውኃ ብቻቸውን ይወርዱና እንኳን እሳት ሊያደርጉ ራሳቸው ውኃ ይሆናሉ ። ግለት ብቻ ይዘን ጥበብ ግን ሳይኖረን ወደ መንፈሰ ቀዝቃዞች ስንሄድ “አንተ የምትለውን ድሮ እኛ እንለው ነበር ፣ ከእኛ በላይ ፉጨት አፍ ማሞጥሞጥ” ሲሉን ቅዝቃዜ ቸልሰውብን ፣ ሞት ወርውረውብን እንመለሳለን ።
ስፓኒሾቹ ግን፡- “እሳትና ውኃ ጦርነት ቢገጥሙ የሚሸነፈው እሳቱ ነው” ያሉት ቍጣንና ግልብልብነትን የሚያሸንፈው ጽሞናና ትዕግሥት ለማለት ነው ። እውነትን በንዴት ብናወራ የሚያሸንፉን ሐሰትን በትዕግሥት የያዙት ሰዎች ናቸው ። እውነታችን ሥነ ምግባር ከሌለው የሐሰት ያህል ይጠላል ። ልባችን የጦርነት መድረክ ነው ። ቤቱ ፣ ሰፈሩም ጦርነት አያጣውም ። የሚያሸንፉ ግን እንደ ውኃ የሚቀዘቅዙ ፣ የሚያረኩ ፣ የማይቆረቁሩ ፣ መልኬ ይህ ነው የማይሉ ፣ የሚታገሡና ዋጋቸውን ዝቅ አድርገው ሰውን የሚቀርቡ ፣ ሌላውን ለማንጻትና መልካም ነው ለማለት የሚፈጥኑ ፣ የሰውን ገመና ለመሸፈን ልቡ ያላቸው ሰዎች ናቸው ።
እሳት ሆነው ለመጡብን ውኃ ሆነን ማብረድ ይገባል ። ውኃ ሆነው ለመጡትም እሳት ሆነን ማቀጣጠልና ወደ ራእይ መምራት ያሻል ። በሥጋ መሻት ፣ በፍትወት ልብ ሲመጡብን በቅድስና በፈሪሃ እግዚአብሔር ማብረድና ወደ ንስሐ መጋበዝ ይገባናል ። እሳትነታችን የሚያበስል እንጂ የሚያሳርር እንዳይሆን ውኃነታችንም የሚያመጣጥን እንጂ የሚያጠፋ እንዳይሆን መገምገም አለብን ።
በእውቀት ጀማሪ ሆነን ስንቀጣጠልና ስንዘባርቅ እሳትነታችንን ያላጠፋ ውኃነታችሁ ይባረክ ብለን ትዕግሥተኛ ሰዎችን መመረቅ አለብን ። እውቀት ያበርዳል ፣ ራእይ ያሞቃል ። መካከለኛው ግን የእሳትና የውኃ ተዋሕዶ ነው ።
ብቻ ከቍጡነት ትዕግሥት ድል አለው ።
ትዕግሥቱን ያድለን !
የብርሃን ጠብታ 1
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ።