የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እስክመጣ

በመጀመሪያ የምታውቀኝ ፣ መጀመሪያን የሰጠኸኝ ፣ አባት እናቴ ሳያዩኝ ከዓለም በፊት ያየኸኝ ፣ ወዳጆች ከማይከተሉበት ከመቃብር በኋላ ዘመድ የምትሆነኝ ፣ ለቀንህ ምሽት ፣ ለብርሃንህ ጽልመት የሌለብህ ፣ ድሀውን እንዲሁ የምታስደስት ፣ ያለ ድጋፍ ሰማይን ያቆምህ ፣ የምስኪኗን ማድጋ በዘይት የሞላህ የፍቅር አባት እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ ። “ሰላም ለእናንተ ይሁን” የምትለው በመምጣትህ ሞት ፣ በመናገርህ ሁከት የሚበረግግልህ ፣ ለሕይወቴ ሕይወት ፣ ለአገሬ ሰላም ትሰጥ ዘንድ እለምንሃለሁ ። እንዳልተቃኘ በገና ፣ እንዳልተጠገነ ማጫወቻ ድምፄ የሚረብሸውን ፣ ምሬትን እንጂ ምስጋናን ማመንጨት ያልቻልሁትን ቃኝተህ የክብርህን ዜማ ስጠኝ ። ከባለጠጋው ግብዣ ፣ ከንጉሡ ገበታ ድሀ አይገኝም ። ነዌን በገንዘቡ ያላፈርኸው ፣ አልዓዛርን በቍስሉ ሳትጠየፍ በቤትህ የጋበዝኸው ፣ እኔንም ከታላቁ እራት አትለየኝ ። ሰዎች ሲቆጥሩ የገደፉኝን ፣ ከቍጥር የማልገባውን ፣ ከሰው ተራ የማልመደበውን አንተ የአብ ልጅ ተቀበለኝ ። ብዙ አባክኜ የመጣሁ ፣ በረከቴን ፣ ጤናዬን ፣ ሰላሜን በመናኛ ቦታ የጣልሁ ነኝና መንፈስ ቅዱስ ሆይ ናዝዘኝ ። ዞሬ ስመጣ የማገኝህ ፣ ልቤን ስዘጋብህ በርህን ከፍተህ የምትጠብቀኝ ፣ ካደረሱብኝ በላይ የደረስክልኝ አንተ አምላኬ ነህና አመሰግንሃለሁ ። እየቻልሁ ያላደረግሁትን ፣ እያልቻልሁ ላደርገው እመኛለሁ ። ባለፈው ዕድሌ ሳይሆን ባለው ዕድሌ መጠቀምን ስጠኝ ። ጸጸት ንጉሥ ሁኖ አይግዛኝ ። ውዳሴ ለተወደስከው ይሁንልኝ ። እስከመጣ ሰላም እልሃለሁ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ