የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እቅድ ሁለት

ከዛሬ ሃያ አንድ ዓመት ጀምሮ ወዳጅነታችን ጥብቅ ነው ። የወዳጅነታችንን ጥብቅነት በሁለት ነገሮች አረጋግጫለሁ ። የመጀመሪያው ፈተናችን አንድ ዓይነት ነው ። ሁለተኛው በእርሳቸው ላይ አንድ ችግር ሲደርስ ባለሁበት ሆኜ አውቃለሁ ። በወዳጆች መካከል የመረጃ ድንበር የለም ። የወዳጃችንን ጉዳቱን ካለንበት ቦታ ሁነን እናውቃለን ፣ ከልብ የምንዋደድ ከሆነ ። ዘመኑን ለእግዚአብሔር የሰጠ መነኩሴ በጣም አከብራለሁ ። መንፈሳዊነትን ከአዋቂነት ጋር ስለያዙት ከእርሳቸው ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች መነጋገር አዋቂም መንፈሳዊም ያደርጋል ። ርቀት ዛሬም ሳይገታው ፍቅራችንን እግዚአብሔር ጠብቆታል ። አብረውን የነበሩ ዛሬ ወደውም ፣ በግድም የሉም። ወደው በከዳተኝነት ፣ በግድ በሞት አልፈዋል ። ሞትን አልተቀየምነውም ፣ ክዳትን ግን ታዝበነዋል ። በችግር ዘመን ችግራችን የበለጠ የሚሰማን ለምንወደው ሰው ማድረግ አለመቻላችን ነው ። እናት ድህነቷን የበለጠ የምታማርረው ለልጇ ምግብ መስጠት ያቃታት ቀን ነው ። እኔም የእግዚአብሔር መጻተኛ እንደ መሆኔ ማድረግ ባለ መቻሌ ብዙ ዘመን ተሰምቶኛል ። ቢሆንም ሁሉም ሲያልፍ ፍቅር ግን ይቀራል ። ታዲያ ከእኒህ አባት ጋር መነጋገር በደቂቃዎች አንድን አገር በሙሉነት ፣ አንድን ዘመን በከፊል ለማየት ያስችላል ። ታዲያ ተጠፋፍተን ሰነበትን ። ያው ስልክ አታላይ ነው ። ሲያወሩ በአካል የተገናኙ ያህል ይደልላል ። ታዲያ አሁንም ርቀት ስለገደበን በስልክ ተገናኘን ። ስንጫወት፣ ስንጫወት እዚህ ርእስ ጋ ደረስንና ይህን መደምደሚያ ሰጡኝ ፡- “ሰይጣን መጀመሪያ ክፉ ሊያሠራህ ይሞክራል ፣ ያ ካልተሳካለት ቢዚ ያደርግሃል ።”
አዎ ብዙ ጨዋ ሰዎች ፣ ብዙ መንፈሳውያን ሰዎች ከሰይጣን ጋር የሚታገሉት ክፉ ላለ መሥራት ነው ። ሰይጣን ግን እቅድ አንድና እቅድ ሁለትን ይዞ የሚንቀሳቀስ፣ የብዙ ዓመታት የውጊያ ልምድ ያለው ነው ። እቅድ አንዱ ካልተሳካ እቅድ ሁለቱን ተግባራዊ ያደርጋል ። በአንድ አቅጣጫ ብቻ ችክ አይልም ። ዙሪያችንን ይዞረናል ። በሚጠሉን ይሞክራል ፣ ካልተሳካ በሚወዱን ይመጣል ። ደግነት በሚመስል ማባከን ፣ ፍቅር በሚመስል ስሜት ፣ ቆራጥነት በሚመስል ጭካኔ ፣ ርኅራኄ በሚመስል መልፈስፈስ ፣ መመስከር በሚመስል መለፍለፍ ፣ ትዕግሥት በሚመስል ስንፍና ይታገለናል ። እርሱ ዱላ ይዞ የሚያስፈራራ ሳይሆን ሸንጋይ ጠላት ነው ። በዚህ ሽንገላው የበረቱ ሳይቀር ወድቀዋል ። አንድ ሰባኪ ፡- “ሰይጣን ላለፉት ሰባት ሺህ ዓመታት እንደ አንተ የታገለኝና ያሸነፈኝ የለም ብሎኛል” እያለ በኩራት ሲናገር ሰምቻለሁ ። ሰይጣን ሸንጋይ ነው ። አጥማቂዎቹና ፈዋሾች ነን የሚሉት በዚህ ተጠልፈዋል ። ሰይጣን ሲሸነግላቸው ረጅም ሰዓት ቃለ መጠይቅ ያደርጉለታል ። ሰይጣን ግን ቢያመሰግንም ቢመሰክርም የሚባለው “እግዚአብሔር ይገስጽህ” ብቻ ነው ። የአየር ሰዓት ተገዝቶለት የእርሱን ሽንገላ ለዓለም ማስተላለፍ አሳዛኝ ክስተት ነው ።
የሰይጣን የመጀመሪያ ጥረቱ ክፉ ማሠራት ነው ። ካልተሳካለት ግን ቢዚ ማድረግ ትልቅ ስልቱ ነው ። አንድ ሰው አውቃለሁ “ራበኝ” ብሎ የመጣውን ሰው ደብዳቤውን አይተው በንጉሡ “ሠ” መጻፍ ሲገባህ በእሳቱ “ሰ” ጽፈሃል ፣ አስተካክለህ ና ይላሉ ። መቼ ? ሲላቸው የሳምንት ቀጠሮ ይሰጣሉ ። ፊደላት በተገቢ ቦታቸው ፣ በሚሰጡበት የድምፅ ቦታ መቀመጥ እንዳለባቸው በብርቱ አምናለሁ ። ለራበው ሰው ግን ፊደልና ሰዋስዉ ማውራት ጭካኔ ነው ። ሰይጣን የሌሎችን ረሀብ እንዳንመለከት ቢዚ ያደረገን በምንድነው ? የአገር ሽማግሌዎች መዋል የሚገባቸው የተጣላውን ሲያስታርቁ ፣ ያዘነውን ሲያጽናኑ ፣ ወጣቱን ሲድሩ ነበር ። ነገር ግን እነዚህ አባቶች ቢዚ የሆኑት በምንድነው ? የሃይማኖት አባቶች መሰብሰብ ያለባቸው ለምንድነው ? ትውልድን ለመቅረጽ ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋፋት ፣ በተለያዩት መካከል ድልድይ ለመዘርጋት አይደለም ወይ ? ነገር ግን ዓመት ቀጥረው የሚገናኙትና ቢዚ የሚሆኑት በአብዛኛው ላልተጠሩበት ዓላማ ነው ። የአንድ መንፈሳዊ አባት ሥራ ቼክ ላይ መፈረም አይደለም ። ማስተማር ፣ መባረክና ክህነትን መናኘት ነው ። አባቶች ግን ቢዚ የሆኑት በምንድነው ?
በሚመስል ነገር የሰው ልጆች ዕድሜ እያጠረ ነው ። ከደረቅ ውሸት ይልቅ የሚመስል ነገር የሰይጣን ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ።
ወጣቶች መሮጥ ያለባቸው ከገንዘብ ይልቅ እውቀትን ፣ ከወሬ ይልቅ የኑሮ ልምድን ለመቅሰም ነበረ ። ዛሬ ግን በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች የሰው ፎቶ ሲያዩ ፣ ጉድ እንደሌለበት በሌላው ጉድ ሲስቁ ይውላሉ ። ሰይጣን ክፉ ባንናገርም ክፉ እንድንሰማ ያመቻቸናል ። “ዛሬስ ምን አሉ ?” እያሉ የሰይጣንን ሐሜት ሲቃርሙ መዋል በዒላማው ውስጥ መግባት ነው ። ብዙ ሰባኪዎች ሊወጠሩበት የሚገባው ድርሻ ወንጌልን ለፍጥረት ለማድረስ ነው ። ብዙ ሰባራዎችንም በቃለ እግዚአብሔር ለመጠገን ነው ። ዛሬ ግን ቢዚ የሆኑት ለሚሰድቧቸው መልስ በመስጠት ላይ ነው ። አዎ ክፉ ላለመሥራት ተጠንቅቀዋል ። ነገር ግን በሰይጣን ሁለተኛ እቅድ ውስጥ ገብተዋል ። ቢዚ ናቸው ።
እኛስ የተፈጠርንበትን ዓላማ እንዳናሳካ ፣ ለሌሎች መፍትሔ እንዳንሆን ቢዚ የሆነው በምንድነው? ወደ ቅድስና ከምንጓዝበት መንገድ አንዱ ቢዚ የሆንበትን ነገር ሰብረን በመውጣት ነው ።
እግዚአብሔር ያግዘን
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ሚያዝያ 18/2010 ዓ.ም.     
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ