እስር ያለው አእምሮ ላይ ነው ። ሰው በቤተ መንግሥትም ቢታሰር እስር ከባድ ነው ። ነጻነትን ማጣት በዚህ ዓለም ትልቁ ቅጣት ነው ። ሰዎች በብሕትውና አርባ ዓመት ከአንድ ጠባብ በኣት ላይወጡ ይችላሉ ። የአገር ድንበር የሚጠብቅ ወታደር በአንድ ምሽግ ለብዙ ጊዜያት ሊያሳልፍ ይችላል ። በሕግም ይሁን በእገታ እስር ከባድ ሁነት ነው ። እኔን አያገኘኝም የምንለው አይደለም ። ክፉ ስለ ሠራን ብቻ ሳይሆን እንደ ዮሴፍ ከክፋት ጋር አልተባበርም በማለታችንም ወኅኒ ልንወርድ እንችላለን ። በእስር ቤት ከነገሥታት እስከ ሎሌዎች ይገኛሉ ። በጥንቱ የነገሥታት ልጆች የሚታሰሩበት “አምባ” ተብሎ የሚጠራው ለአገራችን የእስር ቤት ታሪክ እንደ መነሻ ሁኖ የሚጠቀስ ነበረ ። የእስር ቤት ኃላፊዎች፡- “ለጥንቱ እስር ቤት ፣ ከርቸሌ ይባል ነበር ፣ አሁን ግን ማረሚያ ቤት ብለነዋል ። ሰው የሚማርበት ስፍራ ነው” ይላሉ ። ከማጎር የተሻለ ትምህርት መኖሩ ግን ያጠራጥረኛል ። ጌታ የታሰረን ጠይቁ ማለቱ እጅግ ትክክል ነው ። እስረኞችን ለማስተማርም ለመርዳትም በምሮጥበት ዘመን እስረኛ ማለት ማን እንደሆነ ፣ እስርም ምን ማለት እንደሆነ አውቄአለሁ ። እኔ በምሯሯጥበት ዘመን በአንድ ማረሚያ ቤት ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ታስረው አይቻለሁ ። የደርግ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ሰውም ደጋግሜ አነጋግሬአለሁ ። ለይቅርታ መጽሐፌም ደስታቸውን ለመግለጥ ፣ ለወጠኝ የሚሉትን ሌላ መጽሐፍ እንዳነብ ጋብዘውኛል ። እነዚህን ባለሥልጣናት በምጎበኝበት ቀናት ሁሉ እስር ከባድ እንደሆነ ተረድቻለሁ ። ብዙ የደርግ ባለሥልጣናትም ንስሐ ገብተው ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው እስር ቤቱ ገዳም ሲሆንላቸውም አይቻለሁ ፣ ተሳትፌአለሁ ።
ከሳምንት በፊት አንድ ወዳጄ ታስሮ እርሱን ለመጠየቅ ሄድኩኝ ። የጥየቃ ሰዓቱ ሃያ ደቂቃ ይቀረዋልና እግሬ ወደ ኋላ ቀረት እያለ ወደ እስር ቤቱ ደጃፍ ሲቃረብ አንድ እጅግ የጎሰቆሉ ፣ የኮሰመኑ ፣ ያለቁ ፣ ኑሮ እብድ ያስመሰላቸው ፣ ችግር አናታቸው ላይ ወጥቶ ያሰከራቸው እናት ላይ ዓይኔ አረፈ ። የተቀመጡት ፖሊስ አጠገብ ነው ። በአጠገባቸው ቀድመው የመጡ ሦስት የሚሆኑ ዘመናዊ ወጣቶች አሉ ። በእነርሱ መሐል የተቀመጡት እናት ግን ጉስቁልናቸው ደምቆ ይታያል ። ጥሩ የለበሰ ዓይን ውስጥ እንደሚገባ እኒህ እናትም ጉስቁልናቸው ከሩቅ ይታያል ። ብዙ ድሆችን ያየሁ ይመስለኛል ፣ የእኒህ እናት ጉስቁልና ግን ልዩ ሆነብኝ ። አንድ ችግር ውስጥ እንዳሉ ግን ተጠራጠርሁ ። ችግር ቁመናቸውን አሳጥሮታል ፣ በተፈጥሮም አጭር ናቸው ። ድህነት ደግሞ በብረት ዘነዘና ወደ ታች እየመታ መሬት ቀብሯቸዋል ። ሰውነታቸው አልቋል ። ሠላሳ ኪሎ የሚመዝን ሰው አይቼ አላውቅም ፣ ከአርባ ኪሎ እንደማይበልጡ ግን እርግጠኛ ነኝ ። አንጀታቸው ወደ ውስጥ ስለሰመጠ እጃቸው ሸለቆውን ለማግኘት ወደ ውስጥ ገብቷል ። የልብሳቸው አዳፋ የጎዳና ልጆችም እንደዚህ ሲቆሽሹ አላየሁም ። የፊታቸው ትካዜ የልባቸውን ስብራት በደንብ ይገልጣል ። ነጠላ ልብስም የላቸውም ። አሮጊትነቱ የሚፈቅደውን አለባበስ ድህነት የሚባለው ባለጌ ገፏቸዋል ። ወዲያው ላያቸው ሰው ይህችን ዓለም ከመርገም ውጭ ምንም ሊል አይችልም ። አብሮኝ የነበረው መንፈሳዊ ልጄ እንዳያቸው ኪሱን ዳበሰ ። “ቆይ እስቲ” ስለው “ምን ቆይ ይባላል” ብሎ ከመቶ የዘለቀ ከሁለት መቶ የተጠጋጋ ብር ሰጣቸው ። እርሳቸውም ተቀብለው፡- “ክፉ አይንካህ ፣ እንደ እኔ ከመሆን ይሰውርህ” ብለው በተሰላቸ መንፈስ መረቁት ። ንግግር እንዳስጠላቸው ግልጽ ነው ።
ፖሊሱን ግን፡- “ኃላፊው ይኖራል ልጄ የት እንዳለ እጠይቀው ነበር ፤ ያውቀኛል ይነግረኝ ነበር” አሉት ። ፖሊሱም “የለም” ብሎ አጭር መልስ ሰጣቸው ። ፖሊሱ ጫማው ጫፍ ላይ ያለውን ጭቃ በእስፖጅ ለመጥረግ ወደ እጅ መታጠቢያ ኮረና ወዳመጣው መታጠቢያ ሄደ ። እኛም ሰዓቱ እስኪደርስ አጠገባቸው ተቀመጥን ። “ልጅዎ ምን አድርጎ ነው ” ስንላቸው “ከተከራይ ጋር ተጣልቶ ነው ፣ ያመዋል ሕመሙ ሲነሣበት ቢጣላቸው አሳሰሩት” አሉ ። ተከራይ ሲሉ እኒህ ሴት ቤት ያከራያሉ ማለት ነው ብለን ንቅት አልን ። በግርምት “ያከራያሉ ወይ?” ብለን ጠየቅናቸው “አዎ” ብለው በተሰላቸ ድምፅ መለሱልን ። … ምን ዓይነት ቤት ይሆን ? እንጃ ።
ወደ ውስጥ ስንገባ ልጃቸው ዘመድ መጠየቂያው ላይ ቆሟል ። ልጁ እርሳቸውን ይመስላል ። የድሮ መልካቸው እርሱ ላይ ይታያል ። ያ ልጅ ቀጭን ፣ አጠር ያለ ፣ ንቁ ፣ ቆንጆ ፣ አለባበሱ ዲያስፖራ የሚመስል ቁምጣ የለበሰ ነው ። ፊቱ ግን እንደ ድሀ ልብስ በየአቅጣጫው ተሰፋፍቷል ። ግንባሩ ላይ አንድ ስፌት ወደ ጎን አለ ፣ አፍንጫው ላይ ሌላ ስፌት ወደ ታች አለ ። አገጩ ላይ አሁን ወደ ጎን የተሰፋ ይታያል …። እርሳቸውም፡- “አለህ ልጄ” ብለው በደከመ ድምፅ ጠየቁት ። እርሳቸው የሚያውቁትና ሊያውቁት የሚፈልጉት ነገር ሕመሙ ሲነሣበት ቍጠኛ ይሆናል ፣ ከሰው ጋር ሲጣላ ይታሰራል ብለው ነው ። አይ የእናት አንጀት ። ልክ ሲያያቸው አፈጠጠባቸው ። እርሳቸውም አንገታቸውን ሰበር አደረጉ ። የትዝብት ሳቅ ሳቀባቸው ። የጭካኔ ፈገግታ አየሁበት ። “ምን ልትሠሪ መጣሽ ?” ብሎ አፈጠጠባቸው ። እርሳቸውም ወዲያው ጨመቱ ። “አልነገርኩሽ ?” አላቸው ። በዚህ ጊዜ ሆዳቸው ውስጥ አጥብቀው ይዘዋት የነበረውን ሁለት ሽልጦ እንካ ብለው ሰጡት ። እቤት የጋገሯት ትመስላለች ። “አምጪ” ብሎ ከተቀበለ በኋላ ሲያፈጥባቸው ድምፁንም ፣ የጭካኔ ፊቱንም ለማየት ጊዜም አልነበራቸውም ። ያቺን ደጅ ላይ የተቀበሉአትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ሰጡት ። እርሱም የመንጠቅ ያህል ተቀበላቸው ። በዚህ ጊዜ ውስጤ እሳት ነደደ ። “በሥርዓት አነጋግራቸው ፤ ስላንተ ተጨንቀው ደጅ ላይ ተቀምጠው ነበር ። ሥርዓት ይዘህ አናግራቸው” አልኩት ። አጠገቡ ያለውን ወዳጄን ረስቼዋለሁ ። ወዳጄም እስር ላይ ነውና ይህን ልጅ አደገኛነቱን ያወቀ ይመስል ገርመም አደረገኝ ። እኔ ግን ትዝም አላለኝም ።
በዚህ ጊዜ ደንገጥ አለና፡- “እሺ ዋልሽ ወይ ?” ብሎ አናገራቸው ። መቼም ዱርዬ አካባቢውን በመምሰል የተካነ ነው ። “እነ እገሌ ምን አሉ ?” አላቸው ። አጭር መልስ ሰጡ ። “የቤት ኪራዩ ደርሷል ተቀበልሻቸው ወይ ?” አላቸው ። እርሳቸውም፡- “አልተቀበልኩም ደርሷል እንዴ ?” አሉት ። እርሱም በዓይኑ እያወራ “ተቀበያቸው” አላቸው ። መልእክቱ ቶሎ ይዘሽ ነይ ማለቱ ነው ። እርሳቸውም “እሺ” ብለው አንገታቸውን ደፍተው ሲወጡ እኔም ቶሎ ጠይቄ ተከተልኳቸው ። …
እኔም እኒህን ሴት በቁም የቀበራቸው ፣ ተንቀሳቃሽ ሬሳ ያደረጋቸው ፣ እንደ ነቀዝ በልቶ የጨረሳቸው ይህ ልጅ እንደሆነ ተገነዘብኩ ። አይፈልጋቸውም ፣ እርሳቸው ግን ባይፈልጋቸውም ይፈልጉታል ። እየወጣን እያለን፡- “እንዲህ አይሁኑ ፣ ልጅም ራስን ሲጥሉ አይወድም ። ለራስዎ አስቡ” አልኳቸው ። “አይ ሁሉም ሰው እንዲህ እያለ ይመክረኛል ፣ አቃተኝ እንጂ” አሉ ። … እርሳቸውም ወደ መንገዳቸው ሄዱ ፣ እኔም አብረውኝ ከመጡት ወገኖቼ ጋር እያዘንኩ ወደ ቤቴ ተመለስኩ ። ከጠያቂው እስረኛው የሚያምርበትን አገር እያሰብኩ ወደ ቤቴ መጣሁ ።
ያ ልጅ አይፈልጋቸውም ፣ እርሳቸው ግን ይፈልጉታል ። እግዚአብሔርም “ላልፈለጉኝ ተገለጥሁ” አለ ። /ኢሳ. 65፡1/ “እግዚአብሔር ብቸኛ እንዳይሆን ሰግቶ እናትን ፈጠረ” ያሉኝ ባልቴት ትዝ አሉኝ ።
እግዚአብሔር ከታሰርንበት ሊፈታን ስንት ዘመን ፈለገን ። አንተ አባታችን ነህ ፣ አንተ እናታችን ነህ መባሉ እውነት ነው ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም.