መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » እኔ ግን አለሁ !!!

የትምህርቱ ርዕስ | እኔ ግን አለሁ !!!

ያፈገፈገን አይቼ ወደ ኋላ ስል ፣ እንደገና በፍቅርህ ገመድ ስበኸኝ ፣ በቤትህ እኔ ግን አለሁ ። አስጨናቂ ዘመናት ፣ ላያልፉ የመጡ የሚመስሉ እነዚያ ቀናት አልፈው ፣ በሕይወት እኔ ግን አለሁ ። እያንዳንዱ እርምጃዬን ጠላት ሲከታተለው ፣ ጠላቴን ሳትገድለው እኔን አድነህ እኔ ግን አለሁ ። ለድርድር ሳቀርብህ ፣ መስቀልህን ትቼ ወርቅ ስሸከም ሁሉን አሳጥተኸኝ ፣ አንተ ብቻ ትርፍ ሆነኸኝ ፣ ከነድካሜ እኔ ግን አለሁ ። በነበሩት ሳዝን ፣ ባለው ሳልረካ ፣ በሚመጣው ስሰጋ አቅሜን ብጨርስም ፍቅር ዋስ ሆኖኝ እኔ ግን አለሁ ። የሚወክለኝ ባይኖርም ፣ ብቻዬን የምወዛወዝ ቢመስለኝም ፣ ሥራዬን እየሠራህልኝ እኔ ግን አለሁ ።

አሳዛኝ ሆኜ ሰዎችን ባቆስልም ፣ እሾሃማ ሆነው ሰዎች ቢያደሙኝም ይቅር ብለኸኝ ፣ እኔ ግን አለሁ ። ለመታረም ዕድል ቢኖረኝም ፣ እኔ ግን “ንጹሕ ነኝ” ብዬ በእልህ ብቆምም ሳትጸየፈኝ እኔ ግን አለሁ ። ምግባር ሳይኖረኝ ጸጋህን ብገፋም ፣ የመልካምነት ምኞት እንጂ ኑሮው ባይሳካልኝ ፣ ሁሉን እስክረዳው ታግሠኸኝ እኔ ግን አለሁ ። ጳውሎስን መሆን እያማረኝ ሳውልን ስሆን ፣ በክፉ ብጀምርም በመልካም ለመጨረስ ስጥር ፣ “አይዞህ በርታ” እያልከኝ እኔ ግን አለሁ ። ከኅብረት ለማስወጣት ጠላቴ የሰውን እንከን ሲያሳየኝ ፣ መንፈስህ ግን “ወደ ራስህ ተመልከት ያን ጊዜ ነጻ ትወጣለህ” እያለኝ ፣ በግልግል እኔ ግን እስካሁን አለሁ ።

ለሥርዓት እየተጠነቀቅሁ ፣ ፍቅርን ስደፈጥጥ ፣ የተገለጸ ውድቀት ይዤ የተሰወረ የሰውን በደል ሳስስ ፣ “ተው ልጄ” እያልከኝ እስከ ዛሬ አለሁ ። ተከራካሪነቴን “ለእግዚአብሔር ክብር ነው” ብልም ለራሴ የበላይነት ነበረ ፣ ፈጥረህ አትጥልምና እኔ ግን አለሁ ። አይረባም ተብዬ ተጥዬ እንዳልኖርሁ ፣ አይረቡም ብዬ ሰውን ስገፋ እገረማለሁ ። ያስመረረኝ ድህነት በሰው ላይ ወድቆ ሳየው እጨክናለሁ ። አንተ ግን የረከሰውን ልቤን አጥበህ ከእኔ ጋር ልትኖር መቍረጥህን አውቄአለሁ ። ትዕግሥትህ የመኖር ምሥጢር ሆኖኝ እኔ ግን አለሁ ። ተማሪዎችህን ሳይ እየቀናሁ “እኔ ለዚህ ክብር እበቃ ይሆን ወይ” ስል ዛሬ ግን ደቀ መዝሙርህ ሆኛለሁ ። በሩቅ የምሰማህ ባለ ዝና ስቀርብህ በልጠህ አገኘሁህ ። ዓመታትን አሳልፈህ ፣ ሊያሳልፈኝ የመጣውን አሳልፈህ እኔ ግን አለሁ ።

ካንተ ካልረዳህ በቀር ማንም አይረዳም ። ለክፉ ቀን ያሉት ራሱ ክፉ ቀን ይሆናል ። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በጸጋህ ለምልሜ እኔ ግን አለሁ ። የነገውንም አንተ ታውቃለህ ። ለመኖር አቅም ትሆነኛለህ ። እኔ ግን አለሁ ክበር ተመስገን !!!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ