የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዐቢይ ጾም በሰላም አደረሳችሁ !

ጾመ እግዚእ
“ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም ፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ ።” /ሉቃ. 4፡1-2/ ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላላቅ መገለጦችን ያደረገው በልደቱ ፣ በ12 ዓመቱና በሠላሣ ዓመቱ ነው ። ዘመነ ሥጋዌ የመገለጥ ዘመን ቢሆንም ከሠላሳ ዓመቱ እስከ ሠላሳ ሦስት ዓመቱ ያለው ጊዜ ግን ያስተማረበትና ቤዛ የሆነበት ነው ። በሠላሳ ዓመቱ ራሱን ለዓለሙ ገለጠ ። በእናቱ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ብቻ የሚታወቀው አመጣጡ አሁን መላው ዓለም ሊያውቀው ጊዜው ደረሰ ። በዮርዳኖስ ወንዝ ፣ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ጥምቀታችንን ከባረከ በኋላ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ ። ሠላሳ ዓመቱ አዳም የተፈጠረበት የሙሉ ሰው ዕድሜ መሆኑን ሲገልጥ ለአዳም ሊክስ እንደመጣ ያስረዳናል ። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በጾምና በጸሎት መቆየቱ ደግሞ የአዳምን ፈተና ድል ሊነሣና ድልን ሊሰጠን እንደ መጣ ይገልጻል ። ጌታችን ወደ ምድረ በዳ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ መወሰዱ ሰዎች በድንግልና በምንኩስና ለመኖር ቢፈልጉ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ እንዳለባቸው የሚገልጥ ነው ። ከታላላቅ ውሳኔዎች በፊት ጾምና ጸሎት አስፈላጊ ነው ። ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ ለዘመን ጉልበት የሚሆን ነው ።

መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ መባሉ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ተመርቶ ወደ ሥላሴ ምሥጢር ስንገባ ደግሞ በራሱ እስትንፋስ ተመርቶ ወደ ምድረ በዳ ተወሰደ ። በየዘመናቱ የተነሡ መናፍቃን “ከማርያም የተወለደው ሰው ነው ፣ ባሳየው ታዛዥነትም በሠላሳ ዓመቱ በዮርዳኖስ የአምላክ ልጅ አደረበት ፣ በጸጋም አምላክ ሆነ” ብለው አስተምረዋል ። መንፈስ ቅዱስ ግን የወረደው ልጅነቱን ለመመስከር እንጂ ልጅነትን ሊሰጠው አልነበረም ። እርሱ የተፀነሰው በመንፈስ ቅዱስ ነው ። “ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት መልአኩ ለድንግል አብስሯታል ። ሉቃ. 1፡35 ። በሠላሳ ዓመቱ ልጅነትን አገኘ ለሚሉ ይህ ይመሰክርባቸዋል ። እርሱ ከአዳም ኃጢአት ጋር እንዳልተወለደ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለው ያስረዳል። እግዚአብሔር እንደሆነም “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚለው ንባብ ያትታል ። እመቤታችንም ከአዳም ኃጢአት መጠበቋን መንፈስ ቅዱስ ይጋርድሽናል ወይም ይጸልልሻል የሚለው ንባብ ይገልጣል ።
“አምላክነትን በጸጋ በሠላሳ ዓመቱ አገኘ” የሚሉ ሰዎች ምንም ማስረጃ የላቸውም ። እርሱ አምላክ ካልሆነ ሰብአ ሰገል ለተወለደው ሕፃን ስግደትን በማቅረባቸውና ግብር በመስጠታቸው አምልኮ ባዕድን ፈጽመዋል ማለት ነው። ማቴ. 2፡11 ። ኢሳይያስም የተወለደው ሕፃን ኃያል አምላክ የዘላለም አባት መሆኑን ተናግሯል ። ኢሳ. 9፡6 ። የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ካልሆነ ሕፃን ኃያል አምላክ ፣ የዘላለም አባት መሆን አይችልም ። ደግሞም ስሙ “አማኑኤል” ተብሏል ። ማቴ. 1፡23 ። አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው ። በሥጋዌ ሥርዓት አምላክ ሰው በመሆኑ የወጣለት ስም ነው ። እርሱ እግዚአብሔር ባይሆን ኑሮ በመወለዱ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ተብሎ አይጠራም ነበር ።
እመቤታችን ድንግል ማርያምን “ወላዲተ ሰብእ እንጂ ወላዲተ አምላክ አይደለችም” በማለት የተናገረውና በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባዔ የተወገዘው ንስጥሮስ የተባለ አሳች ነው ። እርሷን “ወላዲተ አምላክ” አለማለት ጌታን አምላክ አይደለም ማለት ነው ።
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ