እኔን ጌታዬ
ከልዕልቶች ሳይሆን የነፍስ ጌጥ ካላት ከድንግል የተወለድህ ፣ ዘር ምክንያት ሳይሆንም ከብርሕት ደመና የተገኘህ የሕይወት ዝናብ ክርስቶስ ፤ እኔን ጌታዬ ፤ ስላልተቀበልኩህ አዝናለሁ ። በእኔ ዓለም መጥተህ ችላ አልኩህ ፣ ባንተ ዓለም መንግሥትን ልትሰጠኝ እየጠበቅኸኝ ነው ። ሰማየ ሰማያት የማይችሉህ በናዝሬት ብሥራትህን ፣ በቤተ ልሔም ልደትህን ፣ በዮርዳኖስ ጥምቀትህን ፣ በኢየሩሳሌም ሞትህን ፣ በደብረ ዘይት ምጽአትህን ያደረግህ ፤ እኔን ጌታዬ በበረት ወድቀህ እኔ ግን በቤት አደርኩኝ ። አልጋ ቢጠብ እንኳ መሬት ወርጄ አላስተናገድኩህም ፤ ጎረቤት ለምኜ የዛሬን አሳድሩልኝ አላኩህም ።
የዘላለም አባት ሳለህ ሕፃን የተባልህ ፣ ዓለማትን በመዳፍህ ይዘህ በድንግል እቅፍ ያደርህ ፤ እኔን ጌታዬ ከከብቶች አንሼ ልብስ እንኳ ባይኖረኝ እስትንፋሴን አላሞቅሁህምና ኀዘን ያዘኝ ። ከምሥራቅ የመጡ ሰብአ ሰገል ሲሰግዱልህ የቅርቡ እኔ ግን ሞትህን ስመኝልህ ፣ ነገሥታት አምነውህ እኔ ድሀው ስክድህ እኔን ጌታዬ አብጄ እንጂ ጤነኛ ሆኜ አይደለምና ይቅር በለኝ ። ዮሴፍና ሰሎሜ ሲያገለግሉህ እኔ ግን ለማይሞላው ኑሮዬ ስሮጥ ፣ ቀኑ አልበቃ ብሎኝ በሌሊትም ስማስን ፤ እኔን ጌታዬ ችላ አልኩህ ። ዓለምን ሳትለያት ወደ ዓለም የመጣኸው ፣ የሰጠኸውን የምትቀበል እንጂ የባሕርይውን የሚሰጥህ የሌለ ፣ እኔን ባለጠጋ ለማድረግ አንተ የበለሶን ቅጠል ለበስህ ። እናትህ ቢጨንቃት ወደ ከብቶቹ እስትንፋስ አስጠጋችህ ። የሚራገጡ ከብቶች ተንበርክከው በትንፋሻቸው አሞቁህ ፣ እኔን ጌታዬ ብራቆት የሚያምርብኝ እኔ ነበርሁ ። አንተ ግን ስድቤን ወስደህ ክብርን ፣ ነውሬን ወስደህ ጽድቅን ሰጠኸኝ ። ሰው ከብት ብሎ ይሳደባል ፣ ባንተ ላይ ግን በሩን ዘግቷል ። ሰው አህያ ብሎ ያዋርዳል ፣ አህያ ግን በዕለተ ሆሳዕና አንተ ተሳፍረህባታል ። አህያ ተሸክማህ ኢየሩሳሌም ገባህ ፣ ሰው ግን መስቀል ይዞ ጠበቀህ ። ከከብቶቹ ከአህዮቹ ያነስን ፣ የገነባኸውን መቅደስ የምናፈርስ ነን ። እኔን ጌታዬ እኔን በመውደድህ አዘንኩልህ ።
የጥበብ ሰዎች ከሩቅ መጡ ፣ እኔ ግን አንድ የፍልስፍና መጽሐፍ አንብቤ ክርስቶስ ማነው ? አልኩህ ፣ እኔን ጌታዬ ያልካድከኝን ካድኩህ ። ባለጠጋ አገሮች በእግዚአብሔር እናምናለን ሲሉ ፣ የእኔ ድሀ አገር ግን ስምህን ለመጥራት አፈረች ፤ እኔን ጌታዬ መሬትን ዘርግተህ ከመሬት ከፍ አድርገን ሰቀልንህ ። ሩቅ መንገድ ተጉዞ የመጣ ፣ ከሰማይ ወደ ምድር የተዘረጋ እንዳንተ ያለ የሩቅ አገር እንግዳ የለም ። እኔ ግን እንግዶቼን ዘመናይነትን ፣ የወረት ፍቅርን አስበልጬ ቸለል አልኩህ ። እኔን ጌታዬ ስሸሽህ ትከተለኛለህ ። ሰው የለኝም እያልኩ ስጨቀጭቅህ ፣ ያሉትም ሰዎች የጨው ውኃ ሆነው መልሰው ሲያስጠሙኝ ፣ አንተ ግን ሰው ሆነህ መጣህልኝ ። እኔን ጌታዬ ሳልስምህ አለፍኩኝ ።
አንተ የሰው ልጅ ካልተባልህ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ አልባልምና ፣ ሁለተኛ ልትወልደኝ ሁለተኛ ልደት ከድንግል የተወለድህ ፣ እኔን ጌታዬ ከሚጫወቱ ሕፃናት መሐል ጎትቼ ሳላቅፍህ ዘመን አለፈብኝ ። ያለፈውን ዕድሜዬን ብትመልሰው ማንም ሳይጋራኝ ላንተ ብቻ እኖርልህ ነበር ። ለባከነው ጊዜ ሲቆጨኝ እየባከነ ያለው ዛሬ ተረሳኝ ። እኔን ጌታዬ እባክህ ለራስህ አኑረኝ ። በሃያ የጠፋ ልብ በአርባ ይገኛል ፣ እኔን ጌታዬ እኔ ግን ልብ ካልሆንከኝ በስድሳም ወደ ማስተዋል አልመጣም ። እኔን ጌታዬ አንተን ብቻ አሰቃየሁህ ፣ የምፈልገውን በቅጡ ሳላውቅ በመቅበጥበጥ በጠበጥኩህ ።
እረኞችና መላእክት የተራራቁ ናቸው ። ልደትህ ግን አንድ አደረጋቸው ፣ ሰማይና ምድርን ያገኛኘ ልደትህ ቡሩክ ነው ። እኔን ጌታዬ ሳላስብህ ሌሊቱ ነጋብኝ ። የክፉዎችን ክፋት ሳስብ ያንተ ደግነት ተጋረደብኝ ። ስምዖን በታቀፈህ ጊዜ መኖርን ጠገበ ። የመኖር ልኩ መድኃኔዓለም እኔም በእምነት ልቀፍህና ከዚህች ዓለም ጋር ያለኝ ሰማንያ ይቀደድ ፤ ጋብቻውም ይፍረስ ። በመወለድህ ለዓለም ፍስሐ ሆነህ እናትህ ግን በነፍስዋ ሰይፍ አለፈ ። እጅግ ለሚወዱህ ሰይፍን የመደብክ ፣ ለራስህም ሳትሳሳ በመስቀል የሞትህ ፣ የመዳንን ጉዞ በልደትህ የጀመርህ ፤ እኔን ጌታዬ ሸክምህን ሳልካፈልህ ቀረሁ ። ዕዳህ ሳለሁ ልጄ ፣ ጠላትህ ሳለሁ ወዳጄ ፣ ዕውር ሳለሁ ብርሃኔ ፣ ብቸኛ ሳለሁ ዓለሜ ያለኝ ፍቅርህ ይባረክ !!!
ነገን ከሰጠኸኝ ፣ ቀኑን ከልቡ ጋር ካደልከኝ ላመሰግንህ እተጋለሁ ። ዘንድሮን አይቻለሁ ፣ ነገም ያንተ ምሥጢር ነው ። ራሴን ለማሳየት ፣ መልኬ ቅላቴ ለማለት እጨነቃለሁ ፣ ነገ ሲፈርስ ላፍር ዛሬ በዚህ ውበቴ አንተን እጋርድበታለሁ ። እኔን ጌታዬ ፣ ራሴን ጨረታ ካወጣሁበት ፣ ልታይ ልታይ ካልሁበት አለማወቅ አድነኝ ። ልታይ ስል ስለጋረድኩህ ይቅር በለኝ ። የልደትህ በረከት ለእኔና ለሰው ልጅ ሁሉ ይድረስ ። አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐሙስ ታኅሣሥ 29 ቀን 2013 ዓ.ም