የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንኳን ለ2014 ዓ.ም ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ !

ሰው ለመሆንህ ሰላም እላለሁ !

ሰው ፣ ሰው መሆንን ሲጠየፍ አንተ ግን ሰው ሆንህ ። ሰው አምላክነትን በሕግ አፍራሽነት ሲሻ ፣ አንተ ግን በፍቅር ሰው ሆንህ ። ሰው የሌለውን አምልኮት ሲያስስ ፣ አንተ ግን የሌለህን ሰው መሆን ገንዘብህ አደረግህ ። ሰው የሌለውን ከፍታ ሲናፍቅ ፣ አንተ ግን የማይገባህን ዝቅታ ሰው በመሆን ወረስህ ። ሰው ጌትነትን ሲፈልግ ፣ አንተ ግን በባሪያ መልክ ተገለጥህ ። ሰው ፣ ሰውን ሲሸሸው ፣ አንተ ግን ሰውን በፍቅር ተከተልከው ። ሰው ፣ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆኔ በቂ አይደለም ሲል ፣ አንተ ግን ሰው ለማዳን ሰው መሆን ያስፈልጋል ብለህ መጣህ ። ሰው ከሆነችው ከባሕርያችን መመኪያ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ፣ ከንጽሕትና አዛኝ ከምትሆን እናትህ ሰው ሆንህ ። ሰው ከእናቱ ማኅፀን ሲወጣ ቀዳማዊ ልደቱ ነው ፤ አንተ ግን ከድንግል ማርያም ስትወለድ ዳግማዊ ልደትህ ነው ። አዳም ከመሬት ፣ ሔዋን ከገቦ አዳም ፣ አቤልና ቃየል ከዘር ከሩካቤ ተወለዱ ። ያንተ ሰው መሆን ያንተ ልደት ግን ከድንግል ነው ። ልዩ ለሆነው ልደትህ ሰላም እላለሁ ! ለዳግም ልደት ታበቃን ዘንድ ዳግም ለተወለድከው ፣ ሰውነትን ታከብረው ዘንድ ሰው ለሆንከው ፣ ደናግላንን ከፍ ታደርጋቸው ዘንድ በድንግልና ለተወለድከው ፣ ለምስኪኖች ታዛ ትሆን ዘንድ በበረት ለወደቅኸው ክርስቶስ ሰላም እላለሁ !

ክርስቶስ ሰው ሆነ ፤ ሰዎች ሆይ ደስ ይበለን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ