የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንደሚገባው የሚሠራ

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ፤  እንደሚገባው የሚሠራ” 1ጢሞ. 3፡2
ሕይወት በሩጫ ሜዳ ላይ እንደ ተሰመረ መስመር ናት ። በተሰመረልን መስመር ካልሮጥን ግጭት ውስጥ እንገባለን ። ግጭትም ወደ መውደቅ ያመራናል ። የተሰጠንን ድርሻ በትክክል ማወቅና ያንን በትጋት መፈጸም ይገባል ። ካልፈቀዱልንና እርዳታችንን ካልጠየቁ በቀር በሰዎች ሥራ ውስጥ መግባት አይገባንም ። ሥራችንን በውጤታማነት የምንሠራው በሁለት ነገሮች ነው ። የመጀመሪያው ስለምንሠራው ሥራ በቂ እውቀት ሊኖረን ይገባል ። ሁለተኛው ትጋት ያስፈልገናል ። ለምንሠራው ሥራ በቂ እውቀት ከሌለን ለፍላፊና ነገር አመላላሽ እንሆናለን ። “አፍና ቅብቅብ ሁልጊዜ አያበላም” እንዲሉ ለሁልጊዜ በዚያ ሥራ መቆየት አንችልም ። ለምንሠራው ሥራ በቂ እውቀት የሚኖረን በአስተውሎት ፣ በመማር ፣ በመጠየቅና ልምድ በመቅሰም ነው ። ለመሳሳት ካልፈቀድን በቂ እውቀት ሊኖረን አይችልም ። ወደ ፍጹምነት የሚያድግ እንጂ በጅምሩ ፍጹም የሆነ ነገር የለም ። አንድን ነገር አድምተን ማወቅ አስፈላጊ ነው ። ለዚያ ነገር ተፈላጊም ተጠያቂም እንሆናለን ። ጠቅላላ እውቀት አስፈላጊ ቢሆንም ለጋዜጠኝነት እንጂ ለባለሙያ ብዙም ላይሆን ይችላል ። ብዙ ነገሮችን አውቃለሁ ስንል ምንም ነገር ላናውቅ እንችላለን ። ዓለም በጋራ የምናቆማት ቤት ናትና ሁሉን ማወቅ አይጠበቅብንም ። በማወቃችን ሌሎች ሲፈልጉን ፣ በማወቃቸው ሌሎችን እንፈልጋለን ። የምንሠራውን በቅጡ ካወቅን ሌሎችን ማስተባበር እንችላለን ። አሊያ ነገሩ “ለራሷ ክርስትና አልተነሣች ልታቋቁም ሄደች” እንደሚባለው ይሆናል ።

ሁለተኛው ነገር ትጋት ነው ። ትጋት ቅዱሳን የሚታወቁበት ነው ። እግዚአብሔር በሰማይ ካደሩ መላእክት በምድር እስከሚኖሩ ቅዱሳን ድረስ ልጆቹ ትጉኃን ናቸው ። ስንፍና ሰይጣንን የጣለው ነው ። አለማመስገን ስንፍና ነውና ሰይጣን አላመሰግንም አለ ። ቀጥሎ መመስገን የሚገባኝ እኔ ነኝ አለ ። በዚህ ምክንያት ከክብሩ ተዋረደ ። ጎዳናውን ስናጸዳ እግዚአብሔር ይደሰታልና በደንብ እናጽዳ ፣ ሰሐን ስናጥብ አገልግሎት ነውና ከልባችን እንጠብ ። ማልደን ወደ ሥራችን ስንሄድ ወደ እግዚአብሔር ሥራ እንደምንሄድ እንቊጠር ። ሥሩ ያለ እርሱ ነውና መሥራት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ነው ። አንዳንድ ሰዎች ሥራቸውን በትክክል ያውቁታል ፣ ሙያው አላቸው ። ትጋት ግን የላቸውም ። ወደ ሥራቸው የሚገቡት ተለምነው ነው ። ብዙ መጀመር እንጂ አንዱን መፈጸም አይሆንላቸውም ። ሌሎች ደግሞ ትጋቱ አላቸው ለሥራው ግን በቂ እውቀት የላቸውም ። አንድ እጅ አያጨበጭብምና አዋቂው ትጋትን ፣ ትጉሁ እውቀትን ሊጨምሩ ይገባቸዋል ።
ኤጲስ ቆጶስ የሚሠራውን የሚያውቅ ፣ ሥራውንም በትጋት የሚፈጽም ሊሆን ይገባዋል ። ኤጲስ ቆጶስ ያለበትን ወንበር ሊያስበው ይገባዋል ። የተቀመጠበት ወንበር ወደ ኋላ ሲሄድ ቅዱሳን ሐዋርያት ከሁሉ በላይ የቅዱሳን አምላክ ክርስቶስ ያገለገለበት መንበር ነው ። እስካሁን ሐረጉ ሳይ                               ቋረጥ  ሁለት ሺህ ዓመታት የዘለቀ አደራ የሐዋርያት አደራ ነው ። በዚህ ዘመን ያሉ አባቶችና መምህራን የዚያ ሐረግ ፍሬ ናቸው ። ኤጲስ ቆጶስ፡-
·        የተቀመጠበትን መንበር ክቡርነት ማወቅ ፣
·        ሥራውን በትክክል መገንዘብ ፣
·        ሥራውን በትጋት መሥራት ይገባዋል ።
በአግባቡ ፣ እንደሚገባው ፣ በሥርዓት መሥራት ምንድነው ? ብለን መጠየቅ አለብን ። የመጀመሪያው የባለ አደራነት ስሜት መያዝ ይገባል ። አደራ በሥላሴ ዙፋን ፊት የምንመልሰው ትልቅ ጥያቄ ነው ። አደራ ከሰማይና ከምድር ይከብዳል ። አደራ ከሞት በላይ አስፈሪ ነው ። ሰው ለአንድ ጊዜ እንኳ ለአደራ ካልታጨ ሰውነቱ ሙሉ አይደለም ። ለአደራ ለመታጨት የሚያስፈልገው ታማኝነት ነው ። ኤጲስ ቆጶስም መጀመሪያ የሚያስፈልገው እምነት ነው ። በእግዚአብሔርና በተግባሩ ማመን አለበት ። ከዚያ የነፍስን አደራ ሊጠብቅ ይታጫል ። እምነት ቀጥሎ የባለ አደራነት ስሜት ፣ ሦስተኛ ሹመት ሲሆን ቀጥሎ ሥርዓት ወሳኝ ነው ። ሥርዓት ዓለም የተዋቀረበት ፣ ውበትን ያገኘበት ነው ። ሥርዓት ዓለም የምትቀጥልበት ምሥጢርም ነው ።ድንገተኛ ደግነት እግዚአብሔርን አያከብርም ። ለዚህ ነው ነቢዩ፡- ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው” ያለው መዝ. 40፡1 ። የሚያስብ ማለቱ ከድንገተኛ ደግነት የታሰበ ደግነት ዋጋ ስላለው ነው ። ሥርዓት ማለትም የታሰበ ፣ የታቀደ ተግባር ማለት ነው ።
በሥርዓት የሚሠራ አንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እግዚአብሔርን ይዞ ማቀድ አለበት ። ለእቅዱም የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጥ አለበት ። የማይችለው ጋር የሚደርሰው ዕለት ዕለት የሚችለውን በመሥራትም ነው ። ዕለት ዕለት ሐረገ ክህነቱ እንዲቀጥል ደቀ መዛሙርትን ማጨት ፣ ያላመኑ እንዲያምኑ ማስተማር ፣ ያለ ትምህርት ያሉ ካህናትን ማሰልጠን ይገባዋል ። ሥራውን በሥርዓት የሚሠራ ማለት እንደሚገባ መሥራት አለበት ። ዓለማውያን ሥራቸውን ለማከናወን በማለዳ ሲሮጡ የእግዚአብሔር አገልጋይ ከዚያ የበለጠ ሥራ ይዞ መተኛት የለበትም ። ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅብኝ በዚህ መጠን ነው ብሎ መትጋት ይገባዋል ። ሥራው አንሶ እንዳያስወቅሰው ፣ በዝቶ እንዳይጥለው ማመጣጠን አለበት ። እግዚአብሔር ከአቅም በላይ እንሮጥ ዘንድ የሚያስገድድ ጨካኝ አምላክ አይደለም ። በሥርዓት ከሠራን ግን አቅሙም ጊዜውም አለ ። ደግሞም እልፍ የምናደርገው እንጂ እኛ የምንጨርሰው ሥራ የለም ። ለሚቀበለን እንዳናረፍድበት በጊዜ መሮጥ ይገባናል ።
ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ መጪው ጊዜ ይታየዋል ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መጪውን ዘመን አይተው የሰበካ ጉባዔ አቋቁመው ነበር። ወዲያው ደርግ መጥቶ የቤተ ክርስቲያን ንብረት ሲወረስ በሰበካ ጉባዔ መዋጮ እነዚያን የመከራ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን ለማለፍ በቅታለች ። አሁንም እየመጣ ያለ የመከራ ዘመን ያለ ይመስላል ። ዋዜማውን እየቀመስን ነውና ። ፈጣንና ተግባራዊ ሥራ ካልሠራን መሻገር ሊከብደን ይችላል ። ቤተ ክርስቲያን ስልትን መጠቀም ፣ ዘመኑን መቅደም በእጅጉ ያስፈልጋታል ። ይልቁንም ንብረትን ሳይሆን ሰውን ሀብት ማድረግ በጣም ያሻታል ።
እንደሚገባው የሚሠራ መሆን ለአንድ መሪ ያስፈልገዋል ። ጳጳስ የጫነውን ግብር ንጉሥ ቢቀንስ ነውር ነው ። ኤጲስ ቆጶስ ያባረረውን ፍርድ ቤት ሲመልሰው የዓለም መሳለቂያ መሆንም ነው ። ሥራችንን እንደሚገባ ከሠራን ስህተትን እንቀንሳለን ። እንደሚገባ መሥራት ለቦታው የሚመጥነውን ሰው ማስቀመጥም ነው ። የዜማ አዋቂውን የነገረ መለኮት ፍርድ ስጥ ማለት ተገቢ አይደለም ። ሰባኪን ገንዘብ ቤት ፣ ቀዳሽን ደረሰኝ ቆራጭ ማድረግ እንደሚገባ አለመሥራት ነው ። በዋናነት የቤተ ክርስቲያን ሀብት መባከን ያለበት ስብከተ ወንጌል ላይ ነው ። ስብከተ ወንጌል የሲኖዶስ ተግባር እንጂ የአንድ መመሪያ ተግባር አይደለም ። “ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ” እንዲሉ በስብከተ ወንጌል የተሰበሰበች ቤተ ክርስቲያንን ያለ ስብከተ ወንጌል እመራለሁ ማለት ዘበት ነው ። ሕዝብ ካልተማረ ጠላት ይሆናል ።
እንደሚገባን እንሥራ ።
1ጢሞቴዎስ 37
ጥር 12 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ