እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
በመንፈሳዊ ዓለም ትልቅ ትርጉም ካላቸው ቃላት አንዱ ትንሣኤ የሚለው ቃል ነው። ትንሣኤ ከፊቱ ሞት አለ። ትንሣኤንም ተናፋቂ የሚያደርገው የሞት ገዥነት ነው። ሞት ነፍስን ከሥጋ ብቻ ሳይሆን ወዳጅን ከወዳጅ የሚለይ ነው። ሞት ሰው ሊዘለው የማይችል ትልቅ እንቅፋት፥ ከመንገድ የሚያስቀር መሰናክል ነው። ሞት የመልካምም የክፉ ሥራም ማብቂያ ነው። ሞት የሀዘን የስብራት መገኛ ነው። ይህን የሚቆርጥ ስለት፥ የሚያለያይ ግንብ፥ መልክ አፍራሽ ጨካኝ፥ እንባን የተጠማ ደግሞም የማይረካ ዳኛ የምንለያየው በትንሣኤ ብቻ ነው። ሞትን ገስጾ ትንሣኤን የሚያውጅ ለዘመናት አልተገኘም። ታላላቅ ግዛቶችን የገዙ ሞትን ግን ማሸነፍ አቅቶአቸው፥ የሁሉም መጨረሻ ሞተ የሚል ሆነ። ጠቢባን ሐኪሞች ሁሉ እስከ ሞት ድረስ ይሯሯጣሉ፥ ጠቢብም ይባላሉ። ሞት ሲመጣ ግን ከመቀመጥ ውጭ ቀጣይ ጥበብን ለማሳየት እንኳ አይግደረደሩም። ሞት ሕሊናን ጭምር የገዛ ነው። ሳይመጣ በስጋት፥ መጥቶ በሀዘን የሚጎዳ መርዝ ነው። ይህንን እናትና ልጅን የሚለየውን፥ ንጉሥን ከዙፋን አውርዶ አፈር ውስጥ የሚያስተኛውን፥ ያማረውን ገላ የሚያፈርሰውን፥ ስምን በደቂቃ ሰርዞ ሬሳ የሚያስብለውን፥ የሚሳሳውንና ቤቱን የማያምነውን ሰው ጨካኝ አድርጎ የማይመለስበትን መንገድ የሚያስጀምረውን ሞት ማን ድል እነሣዋለው ብሎ ይግደረደራል? ባለ አንድ መንገድ የሆነውን፥ መሄጃ እንጂ መመለሻ የሌለውን ይህን መንገድ ማን አስፍቶ ባለሁለት ጎዳና ያደርገዋል?
ሞት፥ ሞት አጥቶ እስከ መቼ ይንጎማለላል? ሁሉን ውጦ እስከ መቼ ዝም ይላል? ዘመናትና አዝማናትን እያስረጀ ለምን ያስረሳል? ሞት በየትኛው ችሎት ይከሰሳል? በቃህ ተብሎ ገዥነቱን ማን ይነጥቀዋል? አዎ ገዥ ነውና ገዥ፥ በገዥ ይሻራል። ገዥን በፍላጎት ማሸነፍ አይቻልም። በሥልጣንና በኃይል የሚሽረው ያስፈልጋል። ይህን ሥልጣንና ኃይል የሚያሟላ ከፀሐይ በታች አልተገኘም። ሥልጣኑ ግዛትን የሚነጥቅ፥ ኃይሉ ያሰራቸውን ሰብሮ የሚያወጣ ነው። የሰው ልጅ በኃጢአት ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፥ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ሳለ፥ ሞትን በሞት የሚነቅል ታዳጊ መጣለት። እርሱም የትንሣኤው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ትንሣኤ ማለት መነሣት፥ መንቃት፥ እንደገና ለመኖር አቅምና ሥልጣን ማግኘት ነው። አንድ ሰው ለመኖር አቅም ያስፈልገዋል፥ እርሱም እስትንፋስ ነው። ሥልጣን ያስፈልገዋል። እርሱም ንጉሣዊ ፈቃድ ነው። ትንሣኤ በውስጡ መለኮታዊ ሥልጣን ያለው ነው። ከእግዚአብሔር በቀር እስትንፋስን የሚቀጥል፥ የመኖርን ፈቃድ የሚሰጥ የለምና። ሰው ገንዘብ እያለው ይሞታል፥ የነገሥታት ፈቃድ እያለውም ያሸልባል። ስለዚህ ሰማያዊ ሥልጣን ብቻ ትንሣኤን ያበስራል። ይህም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተገኝቷል። ትንሣኤን ከአሁን ህልውና ተነሥተን ስናስበው ያንስብናል። ከሞቱት ወገኖቻችን አንጻር ብናስበው ትንሽ ጎላ ይልልናል። እንደገና መጥተው ብናገኛቸው እንደገና ላንጣላቸውና ላንጠላቸው ቃል እንገባለን። የፈራነውና በደቂቃ ውስጥ ሞት ሲመጣ የሸሸነው ማንነታቸውን እንደገና እናቅፈዋለን። የሻርነውን ስማቸውን መልስን እንቀጽልላቸዋለን። ትንሣኤ ይቅርታንና ጠላትንነትን ያጠፋል። የተጸየፍናቸውን እንድንቀርብ ያደርገናል። ስማቸውን ያጠፋናቸውን በስማቸው እንድንጠራቸው ያደርገናል። ሞት ለከበባት ዓለም ትንሣኤ መልስ ነው። ዛሬም ትንሣኤ ብቻ የሚመልሰው ብዙ ሞት፥ ሞት የሚሸት ነገር አለ። በአገር፥ በትዳር በወዳጅነት መካከል ያለውን ችግር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሽኩቻ ስናይ አልሞትንም ብለን መዋሸት ይቸግረናል። መልሱ ትንሣኤ ነው። በራስ ኃይል መቃብርን መጣስ፥ በራስም ሥልጣን ከመቃብር በላይ መጓደድ አይቻልም። የትንሣኤው ጌታ ያስፈልገናል።
ትንሣኤ ሩቅ ነገር ሳይሆን በየቀኑ በምሳሌ የምናገኘው ነው። ስንተኛ ሞትን በምሳሌ እያገኘነው ነው። ስንነሣ ትንሣኤን በምሳሌ እየተሳለምነው ነው። ትንሣኤ የመዳንን ዋጋ ሙሉ ያደርገዋል። አዳም አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ያለውን አዋጅ ይሰብራል። አዳም ለሞት አልተፈጠረም። ሺህ ዓመት በምድር ኖሮ ታድሶ ወደ ሰማይ ደግሞ ይሄዳል። የሺህ ዓመት መንግሥትን እየመሠረተ ወደ ላይ ቤት ደግሞ እንዲሄድ ሆኖ ተፈጥሯል። ይህ እቅድ ግን በኃጢአት ፈረሰ። ኃጢአትና ሞት ንባብና ትርጓሜ ናቸው። ንባብ በሌለበት ትርጓሜ የለም። ኃጢአትም ባይኖር ሞት አይኖርም ነበር። ኃጢአት የሞት አባት፥ ሞትም ኃጢአተኛው የሚቀበለው ፍርድ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ የሞት አያቱ ምኞት፥ አባቱ ኃጢአት መሆኑን ይናገራል፡– “ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ይላል /ያዕ. 1፡15/። ንባብ ከሌለ ትርጓሜ የለም። ኃጢአትም ባይኖር ሞት አይኖርም ነበር። ትርጓሜ ከሌለ ንባብ ወደ ውስጥ አይዘልቅም። ሞት ባይኖርም ኃጢአት አያስፈራም ነበር። ኃጢአትን የሚከለክል የእግዚአብሔር ቅድስና ነው። ትእዛዛቱ ቅዱስ የሚባሉት ለዚህ ነው። “እኔቅዱስ ነኝና ቅዱሳንሁኑ” ይላል /1ጴጥ. 1፡15/። ኃጢአትን የሚቀጣ የእግዚአብሔር ጻድቅነት ነው። “ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል” ይላል /መዝ. 97።9/። ፍርዱን በተመለከተም ፈታሒ በጽድቅ ኰናኒ በርትዕ የምንለው ከዚህ በመነሣት ነው። ትንሣኤ እነዚህን መራዥና ገዳይ ነገሮች ይሽራል። ኃጢአት መርዝ በመሆኑ ትንሣኤ ልቡና ሲታወጅ ይጠፋል። ሞት ገዳይ በመሆኑ ትንሣኤ ሙታን ሲታወጅ ያበቃል። ሁለቱም ግን የሚከናወኑት በቃል ሥልጣን ነው። ቃል የትንሣኤ መሠረት ነው። በመጨረሻው ዘመን ላይ ስለ ሺህ ዓመት ፍጹማዊ መንግሥት፥ ስለ ትንሣኤ ሙታን የሚነገረው የመጀመሪያው የእግዚአብሔር እቅድ በአዳም ኃጢአት ተሰናክሎ ነበርና፥ አሳቡ ከልካይ የሌለው ጌታ አሳቡን ለመፈጸም ነው። ደግሞም ሞተ ሥጋ ወይም ወደ መቃብር መውረድ ዛሬ አልተሻረም። ጌታ መስቀል ላይ ሞቶ ፍዳችንን ከሻረ ይህ ፍርድ መች ይነሣል? የሚል ጠያቂ ካለ በትንሣኤ ሙታን የማዳን ሙሉ ክፍያ ይሆናል ብለን እንመልስለታለን። ስለዚህ ትንሣኤ ልቡና የምንለው በቃሉ የምናገኘው ልጅነት ከሆነ ትንሣኤ ሙታንም ልደት የሚል ትርጉም አለው /ማቴ. 19፡28/። “ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና” ይላል /የሐዋ. 13፡33/። ክርስቶስ በኩራችን ሆኖ ተነሥቷል። እኛም እንነሣለን። ተከታይ ባይኖረው በኩራችን አይሆንም ነበር። ስለዚህ መነሣታችን እርግጥ ነው። የምንነሣበት አንዱ ምክንያት የእግዚአብሔር ልጆች ብንባልም መልካችን ግን ዛሬ አይመስልም። በትንሣኤ አካል ግን ቅዱስና የኃጢአት ትግል የሌለበት አዲስ ማንነትን እንለብሳለን። ስለዚህ ያ ቀን የልደታችን ቀን፥ ክርስቶስን የምንመስልበት የፍጽምናችን ቀን ነው /ሮሜ. 8፡23/።
ስንተኛ ሌሎች ያዩናል። ስንነሣ ግን እኛ እናያለን። ሞትም በሌሎች መታየት፥ ፍጹም ራስን መጣል ነው። ትንሣኤ ግን መሰብሰብ ነው። ስንነሣ ሐፍረታችንን እንሸፍናለን። ትንሣኤ ንጋትና የማይመሽ ቀንን መጎናጸፍ ነው። በኩረ ትንሣኤ ሆኖ ጌታችን መነሣቱ የእኛን ትንሣኤ ማረጋገጡ ነው። አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ተብሎ የታወጀው መውረድ በከፍታ የሚለወጥበት ነው። ትንሣኤን የሚያብራራው ሌላው ምሳሌ አዝመራና መኸር ወይም አጨዳ ነው። አዝመራ መዘራት ነው። ሞትም ለመብቀል መዘራት ነው። ከቤት የከረመው እህል ደጅ ወጥቶ ይዘራል። እንዲሁም በአልጋ በምንጣፍ የከረመው ሰው በሜዳ ይዘራል። ያልዘሩት እንደማይበቅል ያልሞተም አይነሣም። ለማፍራት መሞት ሕግ ነው። ዛሬም እንድናፈራ ለእኔነትና ለፍቅረ ንዋይ መሞት ግድ ይላል። የሞተው ዘር ከፈረሰ ከበሰበሰ በኋላ በአዲስ አካል ይነሣል። እንዲሁም የሞተው ሰው የማይሞት ሆኖ ይነሣል። ዛሬ የፈረሰችው ዘር ዓለም ሲፈጠር በሦስተኛዋ ቀን የተፈጠረችው ቅንጣት ናት። የዛሬዋ ዘር ዕለተ ሠሉስ ላይ ትወስደናለች። የዛሬውም ትንሣኤ አዳም ላይ ሊወስደን ይገባል። ክሩን ወደኋላ ስንስበው አዳም ጋ እንደርሳለን። ልጆች ነንና አውርሰን ብንለው በእጁ ያለውን ሞት ይሰጠናል። ክሩን ወደፊት ስንዘረጋው ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ጋ እንደርሳለን። ልጆች ነንና አውርሰን ብንለው በእጁ ያለውን ትንሣኤ ይሰጠናል። ውርስ ወላጆች ሲበሉት ከነበረው ለልጆች የሚትርፍ ነው። አዳም ሞትን በልቶ ሞትን ያወርሰናል። ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከሞት ያስነሣናል።
በትንሣኤው ዙሪያ ተነገሩት መልእክቶች እጅግ አስደናቂ ናቸው። ማቴዎስ የመልአኩን ንግግር እንዲህ አስቀምጦልናል፡– “መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው” /ማቴ. 28፡5-6/።
በዚህ ዓለም ላይ እንደሚሞቱ የተናገሩ ሰዎች በብዛት አሉ። በሰው እጅ ተገድሎ በራሱ ሥልጣን እንደሚነሣ የተናገረ ግን ክርስቶስ ብቻ ነው። መቼ እንደሚሞቱ የተናገሩ ቅድስናቸው ይነገራል። እንደሚነሣ ተናግሮ ያደረገው ክርስቶስ ግን መለኮታዊ ባለሥልጣን መሆኑ ይታያል። ሰው ባይሆን ሞተ ማለት፥ አምላክ ባይሆንም ተነሣ ሊባል አይችልም። አንዱ ክርስቶስ የሞትና የትንሣኤ ባለቤት ነው። ዛሬም የምንሻው ማንን ነው? ብዙ መሻቶቻችን ፈሪ አድርገውናል። ክርስቶስን የምንሻ ከሆነ ግን አንፈራም። እርሱ የማይጎድል ሀብት፥ የማይበርድ ፍቅር ነውና። በርግጥ እንደ ተናገረ ተነሥቷል። ዛሬም፡– “ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር፦ አሁን እነሣለሁ ይላል መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ” ብሏል /መዝ. 11፡5/። በርግጥም ጌታ በጉዳዮቻችን ላይ ይነሣል። እንደ ደቀ መዛሙርቱ በራችንን ዘግተን በጸሎት ከጠበቅነው ትንሣኤው ደስታ ይሆንልናል። እንዳይነሣ መቃብሩን የምንጠብቅ ከሆነ ግን ትንሣኤው ደስታ ሊሆንልን አይችልም።
እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!