የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንደ ተናገረ ተነሥቷል

 “እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም”ማቴ. 28፡6
“ሃሌ ሉያ ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ
ገነዝዎ ለኢየሱስ በሰንዱናት
ለዘተንሥአ እሙታን በመንክር ኪን ።”
ትርጓሜ፡-
“ሃሌ ሉያ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
ድንቅ በሚሆን ጥበብ ከሙታን ተለይቶ የተነሣ
ኢየሱስን በበፍታ ገነዙት ።” /ቅዳሴ/  
በዓለም ላይ ገደልሁ ብሎ የማያርፍ ጠላት ከባድ ነው ። አይሁድ ጌታን ገደልነው ብለው አላረፉም ። ጠላት ለጊዜው እንጂ እስከ ዘላለሙ መግደል አይችልም ፣ ሥጋን እንጂ ነፍስንም መግደል አይችልም ። ትንሣኤ የገዳዮችን አለመቻል ያሳየ ነው ። መግደል የሚችሉ ማሥነሣት አይችሉም ። “ከጅል ጠብ ጠብቀኝ” ብሎ መጸለይ መልካም ነው ፤ የጅል ጠብ ማለቂያ የለውምና ። ገዳይም ከገደለ ሟችም ከሞተ ሁለቱም ለምን አያርፉም ? ገዳይን የሚገድለው ሞት ሳይሆን ትንሣኤ ነው ። የገደለን ቢገድሉት ከክፋቱ ጋር ሞተ ፤ ገዳይ ሺህ ጊዜ የሚሞተው በትንሣኤ ነው ። መግደል እየቻለ የሞተ ክርስቶስ ነው ። ሰው እየቻለ እንኳን ሊሞት ሊገላምጡት አይፈቅድም ። የሰው ልጅ መግደል ይችላል ፣ የእግዚአብሔር ሥልጣን ግን ማሥነሣት ይችላል ። መግደል ማፍረስ ነውና ሙያ አይጠይቅም ፣ ትንሣኤ ግን ሙያ ይጠይቃል ። ገደልን ብለው እንዳይደሰቱ እግዚአብሔር ትንሣኤን ያውጃል ። መሞት ባይኖር ትንሣኤ አይኖርም ነበር ። ጠላት ባይኖርም ሞት የለም ነበር ። በጠላት ሰፈር ሞቶ በእግዚአብሔር ክብር መነሣት በእውነት ትልቅ ነው ። ሞት ጊዜያዊ ትንሣኤ ግን ዘላለማዊ ነው ። ሞት መጨረሻ አለመሆኑን ያበሰረን የክርስቶስ ትንሣኤ ነው ። አልዓዛር ቢነሣ ለራሱ ተነሥቷል ፣ ክርስቶስ ግን እኛን ይዞ ተነሥቷል ። መስፍኑ ጲላጦስ ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን ከወታደሮቹ በየተራ ጠይቆ ከተረዳ በኋላ በትንሣኤው አመነ ። ይህንንም እምነቱን ለሮማው መንግሥት አሳወቀ ። በዚህ ምክንያትም ሰማዕት ሁኖ ሞተ ። የክርስቶስ ትንሣኤ ጠላትን ወዳጅ ፣ ገዳይን ሰማዕት ያደርጋል ። በመግደል ከምናሸንፋቸው በመነሣት የምናሸንፋቸው ብዙ ናቸው ። ከተነሣን ከክርስቶስ ጋር እንነሣ ። ገዳይ እንቅልፍ የለውምና እንቅልፍ አጡ ። ክርስቶስ ግን የወይን ስካር እንደ ተወዉ ኃያል ተነሣ ። ትንሣኤው ሞትን ማንቀላፋት እንድንለው አደረገን ። የተኙ ሁሉ ይነቃሉ ።

የመቃብሩ ጠባቂ ወታደሮች ጌታችን ዐርፎ ሳለ ነቁ ፣ ሲነሣ ተኙ ። እንደ በድን ሆኑ ። አይሁድ ለመግደል ሸንጎ እንደ ሠሩ ሲነሣ ሸንጎ አልሠሩም ፣ ትንሣኤውን አምነዋልና ። ሰው የመጨረሻ የጉዳት መሣሪያው መግደል ነው ። ትንሣኤ የሰውን አቅመ ደካማነት ያሳየ ነው ። በየቀኑ ስለ እርሱ እንገደላለንና በየቀኑ የትንሣኤው ኃይል ያስፈልገናል ። ጠንካራ ልብ እንኳን በተአምራት በትንሣኤውም አያምንም ። ብዙ ተአምራት ቢደረግ ተአምራቱን የሚያምን እንጂ ተአምር አድራጊውን የሚያምን ትውልድ አይነሣም ። እግዚአብሔር ኃይሉን የሚገልጸው እንዲያሳምነን ብሎ አይደለም ። እርሱ የሰውን ልብ የሚያንኳኳው በፍቅር ብቻ ነው ። ተአምራትን ለራሳችን ዝና የምንፈልገው ቢሆንም ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንላለን ። በቤተ ክርስቲያን ያለ ማቋረጥ የሚሠራው የትንሣኤው ኃይል ነው ። የካህናት ምክር ፣ የአለቆች ሴራ ፣ የመኳንንት ፍርድ ፣ የጎበዞች ቍጣ ፣ የይሁዳ ክዳት ፣ የጴጥሮስ ፍርሃት ፣ የማርቆስ ልብሱን አውልቆ መሸሸ ፣ የደቀ መዛሙርት መበተን ሁሉም ጸጥ አሉ ። በሞተ ቀን ሰዎች ይጮኹ ነበር ፣ ስለዚህ እግዚአብሔር ዝም አለ ፤ በትንሣኤው እግዚአብሔር ሲናገር ሰዎች ጸጥ አሉ ። በቤት የተደበቁ ደቀ መዛሙርት ወጡ ፣ ከተማውንም የሞሉ ተሰወሩ ። ትንሣኤ ገዳዮችን ያሳፈረ ነው ። በትንሣኤ ዘጉባዔ በመጨረሻዋ ቀንም ገዳዮችን ሁሉ የሚያሳፍር መነሣት ይሆናል ። ሰይጣን እስከ ጊዜው ቢበርድም ለክፋቱ ተስፋ አይቆርጥም ፣ ገሀነም ለሚባል ርስት ይህን ያህል መድከሙ ይገርማል ። “ለወሬ የለው ፍሬ ፣ ለአበባ የለው ገለባ” ቢባልም ሰው አሁንም በክፋት ጠንክሯል ። ሟቹ ሰው ይገድላል ።

አይሁድ የሞት ፍርድ መስጠት ስለማይችሉ ጌታችንን ወደ ጲላጦስ ወሰዱት ። ወደ ጲላጦስ ማምጣታቸው ብቻውን እንዲሞት መፈለጋቸውን ይናገራል ። ሞት ቀረሽ ዱላና ጥፊ አውርደውበታል ፣ ትንፋሹ ስትዳከም ወደ ጲላጦስ አምጥተውታል ። ክርስቶስ ሲነሣ ግን ወደ ገዥው ጲላጦስ መሄድ አልቻሉም ። የትላንት መቻል የዛሬ መቻል አይደለም ፣ የኮሩ ሁሉ የሚያፍሩበት ቀን ይመጣል ። ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት ሦስት ቀን በኢየሩሳሌም ቆዩ ፣ በጌታ ትእዛዝ ደግሞ በኢየሩሳሌም ለአሥር ቀን ቆዩና በበዓለ ሃምሳ ወጡ ። ሁለት ዓይነት መሸሸግ አለ ። አንደኛው ኃይል አጥቶ መሸሸግ ሲሆን ሁለተኛው ኃይል ለመቀበል መሸሸግ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ጉቦ ከፍለው ወታደር ጉቦ በልቶ በድኑን እንዳያወጡት መቃብሩ በንጉሣዊ ማኅተም ታተመ ። ታሽጓል የሚለው ማኅተም ሳይቀደድ በዝግ መቃብር ክርስቶስ ተነሣ ። ማኅተማቸውን አልነካም ፣ የትንሣኤውን ማኅተም ግን በሚያምኑት ላይ አተመ ።
መሞቱን የሚያረጋግጥ የሕግ አስፈጻሚዎች ማረጋገጫ ነበረ ። መነሣቱንም ሕጋውያን አረጋግጠዋል ። የአፍ አማኞችና ያላመኑ ክርስቶስን በመስቀል አንድ ሆኑ ። የአፍ አማኞች ቍጥራቸው ከከሀዲዎች ጋር ነው ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሥጋውን እንጂ ፍቅሩን መግደል አልቻሉም ። ሥጋም ሞቶ ሕያው መሆን ይችላል ፣ ፍቅር ሞቶ ግን ሕያው መሆን አይቻልም ። ጌታ ሲነሣ ወደ ቀያፋ ግቢ ሳይሆን ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄደ ። እርሱ ለብሽሽቅ አልተነሣም ። ትንሣኤ ወደ ሞት የሚለወጠው ከሰው ጋር ውድድር ውስጥ ስንገባ ነው ። የመነሣቱን ነገር ደቀ መዛሙርቱ በከፊል ልብ ተቀበሉ ፣ ቶማስ ጣቴን በተወጋው ጎኑ ካላገባው አላምንም አለ ። ጠላቶቹ ግን አምነዋል ። ደቀ መዛሙርቱ ሞቱን ሲነግራቸው አላመኑም ነበር ። ጠላቶቹም በሞቱ ሰግተው ነበረ ። ይሁዳን ጠቋሚ ፣ ጲላጦስን ዳኛ ፣ የመያዣ ሰዓቱን እኩለ ሌሊት ማድረጋቸው ስጋት ነው ። ትንሣኤውን ግን በሙሉ ልብ አመኑ ። ጠላቶቹ ትንሣኤውን ያመኑት ሳይነሣ ነው ፣ ደቀ መዛሙርቱ ግን ተነሥቶም ማመን አቃታቸው ። መላእክት የገረማቸው ትንሣኤው ሳይሆን ሞቱ ነው ፤ ሰውን ግን የገረመው ሞቱ ሳይሆን ትንሣኤው ነው ። ጌታችን የወዳጆቹን ስጦታ የሚያከብር ቢሆንም የመግደላዊት ማርያምን ሽቱ ግን ሳይቀባ በእኩለ ሌሌት ተነሣ ። ሕያው ነውና የሙታንን ሽቱ አልተቀባም ። በድሆች ቤት የኖረው በባለጠጎች መቃብር ለሦስት ቀን ተጋበዘ ። ሁሉ በሁሉ ነውና ። መቃብር ቶሎ የሄደ እንግዳ ያለ ዛሬ አላየችም ። መቃብር መቃብር ሳትሆን የእንግዶች ማደሪያ ሆነች ። ቤት የሌለው ማዕድ አቅራቢ ክርስቶስ በምድረ በዳ ስንቱን አጠገበ ። በተውሶ መቃብር ተቀብሮ ላዋሱት መለሰ ። ሰባት አጋንንት የወጣላት መግደላዊት ማርያም የሌሊቱ ጨለማ ሳያስፈራት ገሰገሰች ። ከትልቁ ጨለማ የወጣ ትንሹን ጨለማ አይፈራም ። ትንሣኤው ያልጠበቁት ነገር የሚገኝበት ነው ። መግደላዊት ማርያም ቅዱስ በድኑን ስትፈልግ እርሱ ተነሥቷል ፤ ከፈን ስታስስ ብርሃን ለብሷል ፣ ከመሬት በታች ስትሻው እርሱ ከተማውን አጥለቅልቋል ፣ በጠባብ ዋሻ ስትፈልገው ሰፊው ዓለም አልቻለውም ።
ሞቱን ለማየት የወጣው ሕዝብ ግን ትንሣኤውን ለማየት አልወጣም ። ሞቱን ሺህዎች ተመለከቱ ፣ ትንሣኤውን ግን አሥራ አንድ ሰዎች አከበሩ ። ስንሞት ብዙዎች ይመጣሉ ፣ ስንነሣ ግን ጥቂቶች ይመጣሉ ። ዓለሙ የሬሳ ስፖንሰር ነው ። ዓለም ሞት አንጋሽ ነው ። ክርስቶስ ግን ሕይወት አክባሪ ነው ። ጨለማ ፣ አጋንንት ፣ መቃብር ፣ ሲኦል ፣ ሞት ያልቻሉትን የክርስቶስን ትንሣኤ ማንም አይችለውም ። በጥንተ ተፈጥሮ ዕለተ እሑድ የሥራ መጀመሪያ ነበረች ፣ የአዲሱ ዘመን ብሥራትም በዕለተ እሑድ ሆነ ። ዓለም ከተፈጠረበት እርካታ ክርስቶስ የተነሣበት ድል ይበልጣልና ይህች ቀን ለክርስቲያኖች የዝማሬ ቀን ሆነች ። በዚህች ሌሊት ከጨረቃ ፣ ከከዋክብት ፣ ከፋኖስ ተለየ የትንሣኤ ብርሃን አበራ ። ጨረቃና ከዋክብት ለሥጋ ያበራሉ ። ትንሣኤው ግን የነፍስ ብርሃን ነው ። ሥጋን መግደል የቻሉት ነፍስን መግደል አይችሉምና በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻነትን ሰበከ ። መለኮት ግን ከሥጋውም ከነፍሱም ለቅጽበት እንኳ አልተለየም ።
ትንሣኤውን መረዳት ያልቻሉ ሰዎች ክርስቶስ ቅዱስ ስለሆነ ተነሣ ይላሉ ። ቅዱስ ባይሆን ኑሮ አይነሣም ማለታቸው ነው ። ስለዚህ ትንሣኤው የቅድስና ዋጋ ነው እያሉ ነው ። ክርስቶስ ግን የተነሣው በኃይልና በሥልጣን ነው ። ነገሥታት ሁሉ ሞታቸውን አያወሩም ። እነሣለሁ ብለውም አይናገሩም ። ቢናገሩም መተረቻ ሁነው ይቀራሉ ። እነሣለሁ ብሎ የተነሣው ግን ክርስቶስ ብቻ ነው ። እንደ ተናገረ ተነሥቷል ፣ በዚህ የለም ።
ጸሎት
ጌታዬ ሆይ የሕያውነትህን ሽቱ ከማርያም እንተ ዕፍረት ጋር ሆኜ ልቀባህ ።ሽቱ ብይዝም እንደ መግደላዊት ማርያም ሰዓቱ እንዳያልፍብኝ እባክህ እርዳኝ ። በምድር ተኝቼ በሰማይ ማገልገል እንዳያምረኝ ፤ ለማልኖርበት ዓለም ሰብስቤ ወደምኖርበት ዓለም ባዶ እጄን እንዳልሄድ እባክህ አንቃኝ ። ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እየሳሙ የገነዙህ ፣ አንተ የፍቅር ዳርቻው ፣ ከአንተ በቀር ፍቅር የለምና እኔም በእምነት እስምሃለሁ ። በረድኤትህ መሰወር ፣ እኔነቴን ባንተ መሸፈን ፣ በትንሣኤ መዝሙር መሞላት እሻለሁ ። መሸነፍን ፣ መውደቅን ፣ ለጠላት እጅ መስጠትን ከእኔ አርቀው ። በዘላለም ክብርህ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 5
ሚያዝያ 12 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ