የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዲህ ቢሆንስ …? /6/

“ባለቤቴ ትዳሩን በጣም የሚወድ ሰው ነው ። በታማኝነትም የምጠረጥረው አይደለም ፣ እርሱም ከብዙ ወንዶች መሐል ቢያየኝ በእኔ ይተማመናል ። ነገር ግን ቢሞትስ ፣ ልጆቹን ምን አደርጋለሁ ? እያልኩኝ እጨነቃለሁ ። በዚህም ምክንያት እርሱ ሳያውቅ የምተኛው በእንቅልፍ ኪኒን ነው” እያልሽ ይሆን ? ባለቤትሽ የሚያውቅሽ ከወላጆችሽ በኋላ ነው ። እግዚአብሔር ግን የሚያውቅሽ ከወላጆችሽ በፊት ነው ። በማሕፀን ሰውሮ የመገበሽ ማነው ? ገና ወላጆችሽ ሳያስቡሽ ዓለም ሳይፈጠር በፍቅር ያየሽ ማነው ? እግዚአብሔር አይደለም ወይ ? ከማሕፀን ስትወጪ ወላጆችሽን ፣ ከቤት ስትወጪ ባልሽን እንዲቀበልሽ ያደረገ ማነው ? አንቺን ሌጣዋን ያበዛሽ የሚወድሽ የሰጠሽ ወዳጅሽ እግዚአብሔር አይደለም ወይ ? ለሴትነት ምቾት በሌለበት ዓለም ላይ መንገድ ከሚያስቀሩ ፣ በአካል ፣ በጤና ፣ በክብር ከሚጥሉ ሽፍቶች ጠብቆ ለዚህ ያደረሰሽ ማነው ? አትችይም ተብለሽ አድገሽ እግዚአብሔር ባንቺ ሲችል አላየሽም ወይ ? በቅርፊት ውስጥ ያለች ጫጩት ጊዜዋ ሲደርስ ራሷ ሰብራ ወይም እናቲቱ ሰብራላት አሊያም ቅርፊቱ ተሰብሮ ትወጣለች ። ምናልባት አንቺም ራስሽ ሰብረሽ የወጣሽ ፣ ወላጆችሽ ባለ ራእይ ያደረጉሽ አሊያም ወቅቱ አግዞሽ እዚህ ደርሰሽ ይሆናል ። ነገር ግን በሁሉም ሥራሽን የሠራልሽ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው ። እርሱ ከበረታ ጋር ሳይሆን ከተጎዳ ጋር የሚቆም ፣ ባንቺ ላይ ያለውን የራሱን መልክ የሚያከብር ነው ።
ረቂቁን ዓለም ታዪ ዘንድ እግዚአብሔር በጥበብ ፈጥሮሻልና በትንንሽ ጉዳዮች አትዘግዪ ። የትውልድን አደራ ትሸከማለች ብሎ ማሕፀንሽን ዓለም ፣ ክንዶችሽን ትራስ ፣ ፍቅርሽ ጥላ አድርጎ ይህን ዓለም ከዚህ አድርሶታል ። አልችልም ባይነት ሲጠራሽ የእግዚአብሔር ሥራ አለብኝ በይ ። በትንሹ በጀት ገበታ መሙላት ፣ ባለቀው ዘይት በበረከት መኖርን ካንቺ ይልቅ የሚያውቅ ማነው ? ዓይኖችሽ መርማሪ የእግዚአብሔር አገልጋዮችን ችግር የምታዪ ፣ እግዚአብሔር ብቸኛ እንዳይሆን የእናትነት አንጀቱን የሰጠሸ ላንቺ አይደለም ወይ ? በራብ ዘመንም አገልጋይ ማስጠጋት በረከት እንዳለው የምታውቂ የሰራፕታዋ መበለት አንቺ አይደለሽም ወይ ? ተፈርቶ ነገር ግን ተርቦ የሚኖረውን ኤልሳዕን በር ከፍተሸ የተቀበልሽ ፣ በሰገነት ላይ ማደሪያ የሠራሽ የሱነም ትልቅ ሴት አንቺ አይደለሽም ወይ ? ዛሬ ነገሥታት እየነገዱብሽ ሥራ አስጀመርናት የሚሉሽ መቼ ሥራ ፈትተሸ ታውቂያለሽ? ጌጥሽ ቅድስና መሆኑን ረስተው በብልጭልጭ ነገር ሊያታልሉሽ የዘመቱት እንዴት አላዋቂዎች ናቸው ? ጓዳ ተቀምጠሸ የአደባባይ ሠራዊትን የምታሰለጥኚ ፣ አገር ሲደፈር ልብሽ ዘምቶ የምታዘምቺ አንቺ አይደለሽ ወይ ? የቤትሽን ገመና ሸፍነሽ ፣ ጦርነትን ያስቆምሽ አቢግያ ፣ የዳዊትን እጆች ከደም የከለልሽ ፣ የተቆረጠ እልቂትን የሻርሽ ጥበበኛ አንቺ አይደለሽም ወይ? ሳሙኤልን ወልደሽ ለእግዜር የሰጠሸ ፣ እግዚአብሔር መቻሉን ሲያሳይሽ መልሰሽ ለእግዚአብሔር የሰጠሸ አንቺ አይደለሽም ወይ ?
የሰማይ ማደሪያን በጸሎትና በእንባ ያራስሽ አንቺ አይደለሽም ወይ ? አዳም እንዳይቀየም በወንድ ጾታ ሰው ቢሆንም አምላክ ግን የተወለደው ከሴት ዘር አይደለም ወይ ? ከአዳም ጎን አንቺ ተገኘሽ ፣ ከድንግል ደግሞ ፈጣሪ ተወለደ ። ፍጡር ፈጣሪውን ወለደ የተባለው በአንቺ ላይ በተሠራው ሥራ ነው ። እውቀትን ፣ ጸሎትን ፣ ዝምታንና ትዕግሥትን ገንዘብ ስታደርጊ ባንቺ ዓለምን የሚለውጥ ሥራ እግዚአብሔር ይሠራል ።
አዎ ዘር ተቀብለሽ ልጅ አድርገሽ የምትሰጪ ፣ ትንሹን ፍቅር አብዝተሸ የምትመልሺ ነሽ ። መልካም ባል ብታገኚ የሠጠሸ የመልካሞቹ መልካም ፤ የሁልጊዜው መልካም እግዚአብሔር ነው ። የተሰጠሸ ነገር ስስት ሁኖ እንዲያከሳሽ ሳይሆን መልካም ነገር ከእግዚአብሔር ነው ብለሽ እንድታመሰግኚ ነው ። ጥሩውንም ባል ፍጹም ነው አትበዪ ። የጠላት ፍላጻ ውስጥ እንዳይገባ ባሌ የሚታይ መልአክ ነው ብለሽ አታውሪ ። የዘላለም ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር እንጂ ከሰው ጋር ያለው ኪዳን ሞት እንደሚፈታው አስቢ ። ሳሉ መዋደድ እንጂ ሲሞቱ መላቀስ ግብዝነት ነው ። ሁላችንም እንሞታለንና እገሌ ቢሞትስ ብለን አንጨነቅም ። ሞት ሁሉም ሰው የሚከፍለው የራሱ ዕዳ ነው ። በትክክል ለኖረ ሞት አሳሳቢ አይደለም ። ባልሽን አክብሪው ልጆችሽ ይፈሩሻል ። ባልሽን አስጊጪው አደባባዩ ይመርቅሻል ። ባልሽን ሸፍኚው አጥርሽ የማይደፈር ይሆናል።
እግዚአብሔር ላንቺ የሰጠሸ መርጦ ነውና ጉድለቱን እንደ ሙላት ተመልከቺ።የሚያናንቅ ሰነፍ መሆን ነውና ጎበዝ ሁኚ ። መኖሪያሽ የዘላለም አምላክ ነውና በሚዝል በሰው ክንድ ላይ አትንተራሺ ። ዕረፍት በማጣት እንዳይጎዳ ባልሽን ምከሪ ።  ኑሮዬ ይበቃኛል ካላልሽ ቤትሽ ይፈርሳል ። የሰው ልጅ ከምግብ ይልቅ የሚጠግነው ሰላም ነውና ሆደ ባሻ አትሁኚ ። ወንድ ልጅ ክብሩን ያመልካልና የስድብ ቃል ከአፍሽ አይውጣ ። በጓደኞቹን ፊት ድካሙን አታውሪ ። ሰዎች ዝም ብለው ያንቺን ብሶት የሚሰሙት የባሰ ጉድ በቤታቸው ተሸክመው ነው ። ልቅሶ የሌለበት ቤት የለም ። ጥርስ ፣ ልብስና አጥር የሸፈነውን እግዚአብሔር ብቻ ያውቀዋል ። በጣም ደስተኛ ለመሆን የሚሞክሩ ሰዎች በጣም ኀዘነተኛ መሆናቸውን እወቂ ። በምድር ላይ ካሉት ሁሉ ያንቺን ባል የሚመስል የለም ። ከሰው ሙሉ ያንቺ ጎዶሎ ያንቺ ነው ። በልጅ ተመክተሸ ባልሽን እንዳትረሺ ፣ ልጅ ለራሱ ነው ፤ ባልሽ ግን ላንቺ ነው ። ከደግ ልጅ ክፉ ባል ይሻላል ። ልጅ ምንም ደግ ቢሆን አምጣ ሲሉት ያሳቅቃል ። ባል ግን አምጣ ይባላል ።
ሞትን የሚፈራ በትክክል የማይኖር ነውና ብሞትስ ፣ ቢሞትስ ብለሽ አትስጊ።ራስሽንም አታውኪ ። ሞት ሲመጣ ከመጽናናት ጋር ነው ። ዛሬ ግን ያለመጽናናት በስጋት እንዳይጎዳሽ ተጠንቀቂ ። ነገ ያንቺ አይደለምና ዛሬን ኑሪ። ዛሬን በትክክል ከኖርሽ ለነገ ይተርፋል ። እግዚአብሔር ጓዳሽ ይባርክ።
ወደ ክርስቶስ መገስገስ 11
ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም.
ተጻፈ አዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ