መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » እንዴት ልዘን?

የትምህርቱ ርዕስ | እንዴት ልዘን?

የመደሰትና የማዘን፣ የመሳቅና የማልቀስ ተፈጥሮ ሰጥተኸኝ እንዴት ልዘን? ጌታዬ ቸግሮኛል። ሁሉም ነገር የእንቧይ ካብ ሲሆን፣ ላይነጋ የመሸ ሲመስል ከዚህ በላይ ምን ልሁን ? ላልቅስ  እንጂ ስል ፊቴ ትመጣለህ። ያጎረሰኝ እጅህ አሁንም ሊደግመኝ አፌ አጠገብ ነው። ኧረ ገለል በልልኝ ልዘን ፍቀድልኝ። እንደ ኑኃሚን ብዙ ሆኖ ወጥቶ ብቻ መመለስ ፣ ልጅን ቀብሮ ነጭ መልበስ እንዴት ይቻላል? እንዳዝን የሚጠብቀኝ ብዙ ወገን አለ፣ ለእውነትም ለይሉኝታም እባክህ እንዳለቅስ ፈቀድልኝ። እንባዬ ተሰንቅሮ፣ ልቤ ላይ ተተክሎ ወግቶ እንዳይገድለኝ እባክህ እንዳዝን ፍቀድልኝ።

ልቅሶዬን ፍቅርህ፣ ግፌን ውለታህ እየካሰብኝ እንዴት ልዘን እባክህ ገለል በልልኝ። ሃና ልቤ ልጅ ጎደለ ብሎ ሲያለቅስ ሕልቃና ማንነቴ ከአሥር ልጅ ጌታ ይበልጣል ይለኛል።

በአራቱ መዓዘን የተወጠርኩ ሲመስለኝ ፣ የወደድኩትን አጥቼ የጠላሁት ሲናፍቀኝ ላዝን ምንጣፍ አስተካክላለሁ ፣ ውለታህ ድቅን ሲልብኝ “ከጌታዬ  ምን ጎደለ?” ብዬ  እተወዋለሁኝ። መስቀሌ ውበት የለውም፣ ያንተ መስቀል ግን ውብ ያደርጋል። ደግሞም ሲያዩት ያምራል ፣ ዕርቃንህን ሆነህ መስቀል ላይ ታምራለህ። ለውበቴ የመጣውን ለሞቴ ነው ብዬ ትርጉም ሰጥቼ ለማዘን ጊዜ እመድባለሁ፣ ጠላቴም ሆድ እያስባሰኝ፣ እየቆነጠጠ ያስለቅሰኛል። ይህ ፅንስ አይረባም ይወገድ ተብሎ የተወለደ ዛሬ ላይ ደርሶ እንዴት ያዝናል? ባለሙያ ሞት አውጆብኝ በሕይወት ካለሁኝ ምንም ለማዘን መብቴ ቢሆንም አንተን እያየሁ እንዴት ልዘን? ሰው ነኝና አመነታለሁ፣ ግን ያላንተ አይሆንልኝም ብዬ መንገዴን እቀጥላለሁ ። ሰው ነኝና አልቅሼ ይውጣልኝ ብዬ መሐረብ አሰናድቼ በሬን እዘጋለሁ ። ከጎደለብኝ የሞላው ብዙ መሆኑን አይቼ አፍሬ በሬን እከፍታለሁ።

ብዙ መፈተን፣ በመከራ ሰፌድ ላይ እንደ ስንዴ መበጠር ከባድ ነው። አንዱ መከራ ለሌላኛው አቀብሎኝ ይሄዳል እንጂ ይበቃዋል ብሎኝ አይሄድም። በከበዱኝ ቀኖች፣ አንተን ባላውቅ ኖሮ ምነው በሞትኩ በምልበት ሰዓት እንኳ እኔ አለሁ አትበለኝ ፣ እንዳዝን ገለል በልልኝ። ልቅሶ ግዝረት፣ እንባ ጥምቀት ሆኖ ይገላግለኝ፣ እንዳዝን ፍቀድልኝ። የጸናው መሬት እኔ ስረግጠው ይናዳል፣ የመጣው ነገር ከምችለው በላይ ሆኗል ብዬ ላዝን ስዘጋጅ፣ ሆዴ ሲላወስ፣ እንባ ጋኑን ሰብሮ ሊወጣ ሲል የተቸነከረ እጅህን ታሳየኛለህ። ስላቆሰሉህ እልፎች ሳይሆን ስለ ቆሰልኩልህ አንዱ ስለ እኔ አስብ ትለኛለህ። ያለኝ አቅም እርሱ ነው ፣ ጨርሼ እንዳዝን፣ የኖርኩበትን ኑሮ እንድሰርዝ ፍቀድልኝ። በአሳብ የሚረዳኝ፣ በጉልበት የሚቆምልኝ የለም ። ከፈተናው የተነሣ የበደሌ ከፍታ ምን ያህል ቢሆንብህ ነው ? እላለሁ። መልስ ያጣሁ ሆኖ ተሰምቶኝ ላዝን ስዘጋጅ እንባዬን ነፋስ እንደሚበትነው ደመና ትወስድብኛለህ ፣ እንዳዝን ፍቀድልኝ።

ሞትን በምለምንበት፣ ይበቃኛል ጥራኝ በምልበት ሰዓት ኤልያስ ልቤን በሰረገላህ ትነጥቀዋለህ። ለሁሉም ነገር ጣዕም ሳጣ ፣ ለመመረር ሰዓቱ ነው ስል፣ ባወቅሁት መጠን አለመኖሬ ትዝ እያለኝ ምሬቴን እመልሳለሁ። የገነትና የሲኦል ጥያቄ ስላለብኝ ፣ ይቅርታ ጠይቆ ለማረፍም ሳይሆን ይቅርታ ልትጠየቅ የሚገባህ ክቡር መሆንህን አስብና መልሼ ይቅር በለኝ እልሃለሁ። እኮ እባክህ ዛሬ ልክ ልሁንና እንዳዝን ፍቀድልኝ። ከእኔ እንጂ ካንተ አልጎደለምና ፣ ከሰው እንጂ ካንተ ያጣሁት የለምና ልቆጣህ መጥቼ ተገሥጬ እመለሳለሁ።

የት ነህ ብባል እዚህ ጋ ነኝ በማልልበት በጨለማው መንገድ ላይ ስሆን ፣ ዕድሌ ምንድነው ? ብዬ ለማልቀስ፣ የሰውን ጥያቄ ለመሸሽ እጥራለሁ። ካንተ ጋር እየተሟገትሁ መኖር ይበቃኛል ብዬ ራሴን በኀዘን ለመቅጣት እነሣለሁ። ያነጋልኝ ቸርነትህን ሳስብ፣ በአልጋ ያሉትን በሽተኞች ሳስታውስ ማረኝና ልግባ አገሬ እላለሁ። የተቀበልኩት እውነትና የምኖረው ሕይወት ሲለያይብኝ፣ ራሴን ያለ ክርስቶስ ሳየው አስፈሪ ሥዕል ሲመጣብኝ ማዘን እፈልጋለሁ። መልሰህ በር ዘግተህ ትመክረኛለህ ። በጽኑ እጅህ ከጎርፉ ውስጥ ታወጣኛለህ።

ብቻውን የሚወድቅ ነገር የለምና ለትዳሬ መፍረስ፣ ለባልንጀርነቴ መበላሸት የእኔም እጅ አለበት። ጌታ ሆይ ትዳር ነበረኝ፣ ልጅ ነበረኝ ማለት ያቆስላል፣ አሁን እንኳ ተወኝ ልዘንበት? የሣር ተማሪ ሆኜ “ሀ” ያልኩበትን ዘመን አላውቀውም፣ ሁሉንም ነገር የምማረው በሐሳር ነው። እንዲህ ብዬ ላዝን እፈልግና ከእጅህ የበላሁት ያንቀኛል፣ የበረሃው ጓዴ መሆንህ ድቅን ይልብኛል። ባዝንም ባለቅስም አለማመስገን ይቆረቁረኛል።

እንዴት ልዘን? ያበላኝ እጅህ ይታየኛል !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከም 2 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ