መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » “እንግዲህ” በሉ

የትምህርቱ ርዕስ | “እንግዲህ” በሉ

 

“እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤” ኤፌ 4÷1

በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት ውስጥ በአዲስ ምዕራፍ ላይ እንግዲህ የሚል ንግግር እናስተውላለን ። ይህ የሚያሳየን ያለፈው ምዕራፍ እንዳላለቀና የአሁኑ ምዕራፍም መጀመርያ እንዳልሆነ ነው  ። “እንግዲህ” እና “ነገር ግን” የሚሉ መነሻዎች ሲገጥሙን መልእክቱ ሰንሰለታማ መሆኑን  ፣ ያሁኑን ምዕራፍ ለመረዳት ፊተኛውን ምዕራፍ ማየት እንደሚገባን ፣ ዳግመኛም የጀመርነውን ምዕራፍ ጨርሰን ማንበብ እንደሚያስፈልገን የሚጠቁም ነው ።

“እንግዲህ” በሚለው መክፈቻ ከትናንቱ የተቀበልነው እንዳለ ፣ ዛሬም የምንቀጥለው እንጂ የምንጀምረው ነገር እንደሌለ እንረዳለን ። እኔ ከማንም ያልተቀበልኩ ነኝ የሚል አስተሳሰብ ልቡሰ ሥጋ ጋኔን የሚደርግ ነው ። ለትናንት ክብር እንዳይኖረን ፣  የእኛም ነገ ላይ እንዳይከበር የሚያደርገው “እንግዲህ” የሚለው ማያያዣ ሲበጠስ ነው ።

ትናንትም ነገም የሌለው ትውልድ የሚፈጠረው “እንግዲህ” የሚለው ድልድይ ሲሰበር ነው ።

 ዛሬ ማዕከላዊ ነች መነሻም መድረሻም አይደለችም ። ሕይወት መግቢያ እና ማጠቃለያ እንዲኖራት “ትናንት” እና “ነገ” ያስፈልጓታል ። ትናንትን ብቻ ማዘከርም ለዛሬ በማይተርፍ ጉራ ውስጥ ያኖራል ፣ ነገን ብቻ ማለትም መንገዱ እንዲጠፋን ያደርጋል ። የምንሄድበት እንዳይጠፋን የመጣንበትን ማስታወስ ግድ ነውና ።

 አናሳ ታሪክ ፣ አናሳ ቤተሰብ ፣ አናሳ አገርና አናሳ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጠረው ዛሬ ብቻ የሚል ጣዖት ሲመለክ ነው ።

ዛሬ ብቻ የሚል የአራዊት እና የጅቦች ጉባዔ ነው ።  “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አለች አህያ ይባላል። እንዲህ ያለች  አህያ አናውቅም ፣ ያሉ ሰዎችን ግን እናውቃለን ። የመጠጥ ስብስብ ፣ የበልተን እንሙቶች ጉባዔ ፣ አባትም ልጅም የለን የሚሉ የአሳብ ምልምሎች ጥርቅም ዛሬን ብቻ ይኖራል  ። 

ጥርስ ከላይ ከንፈር ፣ ከሥር ምላስ አለው ። ከንፈር ካባ ነው ፣ ያለ ከንፈር የሰው ልጅ አስፈሪ ፍጡር ነው  ። ምላስም ከማጣጣም ባሻገር እንደየአቅሙ ይፈጭ ዘንድ ለፊት ጥርስ ቀላሉን ወይም የሚነጨውን ፣ ለኋላ ጥርስ ከባዱን ወይም የሚፈጨውን  ምግብ ታደላድላለች ። ምላስና ጥርስ በመልክና በአቅም ቢለያዩም በአንድ ቤት ውስጥ በስምምነት ይኖራሉ ። ዛሬ እንደ ጥርስ ሲሆን ከንፈር ትናንት ፣ ምላስ ደግሞ ነገ ነው ። የትናንት ትውልድ የክብርን ዋጋ ያውቃልና ክብር ይሰጥሃል  ፣ የነገ ትውልድ ደግሞ ፈጣን ነውና ይላክልሃል ። ሽማግሌዎች  የትናንት ፍሬዎች ፣ የዛሬ ጭማቂዎች ፣ ልጆች የዛሬ አበባዎች  የነገ ፍሬዎች ናቸው ።

ትናንት ሰገባው ፣ ዛሬ ሰይፉ ፣ ነገ ድሉ ነው ። ሰገባ ሰይፍን ያበርዳል ፣ የትናንት እውነተኛ ሽማግሌዎችም የሚያስታርቁ ናቸው ። ሰይፍ ተፈሪ ነው። ይከፍላል ፣ ይቆርጣል ፣ ይገርዛል ።  በሰይፍ መፈራት እንጂ ክብር ላይገኝ ይችላል ። ዛሬ ኃይለኞች  ከሆንን የነገን ድል ለማግኘት መታየትና ማብረቅረቅ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰገባው መከተት አለብን ። ትናንት  ሥር፣ ዛሬ አገዳ፣ ነገ ፍሬ ነው ። ምንም ባይታይ አገዳውና ፍሬውን የተሸከመው ሥሩ ነው ። “ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ?” እንዲሉ ። 

የዛሬዋን ቤተክርስቲያን እና አገር ያስረከቡ ትልልቆች ዋጋ ሲሰጣቸው፣  የዛሬው ትውልድ እኔም ዋጋ አለኝ ብሎ በጎ ለመሥራትና ሌብነትን ለመጸየፍ ይበቃል ። ትናንት የሌለው ዛሬ ፣ ነገ የሌለውን ዛሬ ይፈጥራል ። 

የዛሬ ባለትዳሮች የትናንትን እጮኝነት ፣ ነገ ደግሞ በክርስቶስ ወራሾች የሚሆኑበትን እኅትነትና ወንድምነትን ሊያስቡ ይገባል ።  ብዙ ጊዜ በእጮኝነት ሁለት ዓይኖች ይከደናሉ ፣ በትዳር ሁለት ዓይኖች ይገለጣሉ ፣ በሽምግልና አንዱ ዓይን ስህተት ሲያይ አንዱ ይጨፍናል ። እጮኝነት የወደደውን መልአክ ማድረጉ ፣ ትዳር ሰይጣን ነው ብሎ መሳሉ ተገቢ አይደለም ። ብስለት ግን ሰውን፣ ሰው ማለት ተገቢ እንደሆነ ያምናል ።

የዛሬ አገልጋይ የትናንት መምህሮቹን ክዶ በቀጥታ ከሰማይ ሰማሁ ቢል ፣ የነገ ደቀ መዛሙርትን ሊያፈራ አይችልም ። የዛሬ ሹም አገር የጀመረችው እኔ ስቀባ ነው ካለ የትናንትናዎቹን እያሳዘነ ፣ የነገዎቹን እየገደለ ይመጣል  ። “እንግዲህ” የሚለውን ንግግር የአሁን ትውልድ ሲጠቀመው ብዙ አይሰማም  ። ሲመጡ “እንዴት ዋላችሁ?” ሲሄዱ “ደህና ዋሉ” የማያውቁ ትውልዶች “እንግዲህ” የሚለውን መጠቀም አይችሉም ። የትናትናዎቹ ደካማዎች ቢሆኑም የእኛን እንጨምርበት እንጂ እነርሱን በመንቀፍ የራሳችንን ዘመን አንፈጽመው ። “ሙት መውቀስ ድንጋይ መንከስ” እንዲሉ ። ትናንት የሌለው አገር፣  ነገ ብሎ የሚጠራው ሀብት የለውም ። 

የተነሣንበትን አሳብ አንዘንጋ ። ሐዋርያው “እንግዲህ” ያለው ምዕራፍ ሦስትን ሲደመድም እግዚአብሔር አብን ፣ እግዚአብሔር ወልድንና ቤተ ክርስቲያንን የሚሞሽረውን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን በማንሣት ነው ። እግዚአብሔር አብ ልጁን ሰጠን  ፣ ልጁም ቤተ ክርስቲያንን ሰጠን ፣ መንፈስ ቅዱስም ለቤተ ክርስቲያን ጸጋን ሰጠ ።

“እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤” ኤፌ 4÷1።

በዚህ ክፍል ጥሪ የተባለው እምነትም ምግባርም አይደለም። የተመደብንበት የጸጋ ድልድል ነው ። ሁሉም በጸጋው ቢተጋ ጎዶሎዋ ዓለም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ትሆናለች ። 

“እንግዲህ” የምንል ያድርገን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

ነሐሴ 7 2013 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም