የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንግዳ ተቀባይ

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … እንግዳ ተቀባይ” 1ጢሞ. 3፡2
እንግዶችን መቀበል ከጥንት ጀምሮ የእግዚአብሔር ሰዎች ተግባር ነው ። ሰዎችን በእንግድነት እንቀበላለን ብለው ራሱን እግዚአብሔርንና ቅዱሳን መላእክትን ተቀብለዋል ። አብርሃም ሥላሴን በቤቱ አስተናግዷል ። ይህም በየዓመቱ ይዘከራል ። ይህ የሚያሳየን እንግዳን መቀበል በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ተግባር መሆኑን ነው ። የተለያየ የቅድስና ተግባር የነበራቸው ሰዎች በቅዱስ መጽሐፍ ታሪካቸው ሰፍሯል ። እግዚአብሔርን በቤታቸው ያስተናገዱ ግን እንግዳ ተቀባዮች ብቻ ናቸው ። እግዚአብሔርን እንቀበላለን ብለው ይህን ተግባር አልጀመሩም ። እግዚአብሔርም በእግዚአብሔርነቱ ግርማ ወደ እነርሱ አልመጣም ። እነርሱ ሰዎችን እየተቀበሉ ሳለ አንድ ቀን ግን እግዚአብሔርንና ቅዱሳን መላእክትን ተቀበሉ ። እግዚአብሔር እንግዳ ተቀባዮችን ይወዳል ። እንግዳ መቀበል በሕገ ልቡና ፣ በሕገ ኦሪት ፣ በሕገ ሐዲስ የጸና ትእዛዝ ነው ። ጻድቁ አብርሃምና ጻድቁ ሎጥ እንግዳ የተቀበሉት በሕገ ልቡና ዘመን ነው ። እንግዳ መቀበል በተፈጥሮ በውስጣችን የተቀመጠ ሕግ ነው ። ያንን ሕግ ካልፈጸምን ደስተኛ ልንሆንና ከራሳችን ጋር ልንስማማ አንችልም ። አብርሃም እንግዳ ተቀባይ ባይሆን ኑሮ እግዚአብሔርን በቤቱ አያስተናግድም ነበር ።

እግዚአብሔር እኛን የሚለካን ለሰዎች ባለን የፍቅር ገጽ ነው ። ለዚህ ነው ሐዋርያው፡- እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም ፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል ያለው ። 1ዮሐ. 4፡12 ። እግዚአብሔርን ያየው ማንም የለም ፣ እግዚአብሔርን ግን በእንግዶች ላይ ማየት ይቻላል ። የምናየውን ወገናችንን ስንቀበል አንድ ቀን የማናየውን እግዚአብሔር በቤታችን እንቀበላለን ። እግዚአብሔር የልባችን ብቻ ሳይሆን የቤታችንም እንግዳ ሁኖ ይመጣል ። ተዘጋጅተን መጠበቅ ያለብን ለሞት ብቻ ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ሊመጣ ይችላልና ብለንም ነው ። ጻድቁ አብርሃም እንግዳ ባይቀበል ኑሮ እግዚአብሔር ወደ ቤቱ አይመጣም ነበር ። በቤቱም የተሰማው የሣራ የመውለዷ ተስፋ አይነገርም ነበር ። አብርሃምም ለሎጥና ለሰዶም ሰዎች ምልጃ አያቀርብም ነበር ። ጻድቁ አብርሃም እግዚአብሔርን በቤቱ በመቀበሉ የበረከት በረከት የሆነው እግዚአብሔር ወደ ቤቱ ገባ ። የዛሬ ዓመትም እንደሚወልድ ተስፋ ሰጠው ። ለሎጥም በመማለድ ሕይወቱን አተረፈለት ። ለከተማይቱም መጥፋት ተጨንቆ ጸለየ ። አብርሃም እንግዳ ይቀበል የነበረው የፍቅር ሰው ስለነበረም ነው ። የሀብታቸውን ልክ ለማሳየት ግብር የሚያበሉ መኳንንትና መሳፍንት አሉ ። አብርሃም ግን እንግዳ ይቀበል የነበረው የፍቅር ሰው ስለነበረ ነው ። በዚህም ለሚጠፉ ከተሞች ማለደ ። በሰዶም አልፈረደም ፣ ለሰዶም ሕዝብ ግን ማለደ ። እግዚአብሔር የሰዶምን መጥፋት የነገረው ምሥጢሩን ለወዳጆቹ ስለማይሸሽግና እንዲጸልይም ነው ። የወንድሙ ልጅ ሎጥም ከዚያ ጥፋት የዳነው አብርሃም ስለጸለየለትም ነው ። የሚጸልይለት ወዳጅ ያለው ከጥፋት ያመልጣል ።
ሎጥም ከተማይቱን የሚያጠፉና እርሱን ግን የሚታደጉ መላእክትን በቤቱ ተቀበለ ። ዘፍ. 19፡1-2 ። ሎጥ ምግብና ውኃ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እንግዶቹን ከልጆቹ በላይ ከለላ ሰጥቷቸዋል ። እነዚያ እንግዶች ግን ቅዱሳን መላእክት መሆናቸውን አላወቀም ነበር ። አውቆ ቢቀበል ኑሮ ድንቅ አልነበረም ። የማይቀበል የለምና ። እንግዳ በቤታችን የተማጸነ ነውና ራሳችንን ልንሰጥለት እንደሚገባ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ይነግሩናል ። ዘፍ. 19፡4-11 ፤ መሳ. 19፡16-24 ። በአገራችን እንኳን ሰውን ግንድን የተማጸነ አይነካም ። እንግዳም የተማጸነ ነውና ሊነካ አይገባውም ።
በማናውቀው አገር ስንሄድ ግራ እንጋባለን ። ቅርቡ ሩቅ ይሆንብናል ። ቀጥሎ ምን ይገጥመን ይሆን የሚል ስጋት ያድርብናል ። ሰዎች ትንሽ ነገር ሲያደርጉልን ትልቅ ያደረጉልን ያህል ይሰማናል ። የከተማውን ሰው ሁሉ ዓይን ዓይኑን እናያለን ። ፍቅርና ስጋት ይቀላቀልብናል ። እንግዶችም እኛ ጋ ሲመጡ ይህ ስሜት ስላላቸው ነው እንግዶችን ተቀበሉ የተባልነው ። እግዚአብሔር አምላክ እስራኤልን ካስጠነቀቀበት አዋጅ አንዱ፡- የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” የሚል ነው ። ዘሌዋ. 19፡10 ። ዳግመኛም፡- እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” ብሏል ። ዘሌዋ. 19፡23 ። ይልቁንም ስደትን ያየ ሰው ለእንግዶች ማሰብ አለበት ። ካለን ነገር ላይም ለእንግዶች ሳናስቀር ፈጽመን መብላት የለብንም ። ገበሬ ለዘር ሳያስቀር ፍሬውን ሁሉ አይበላም ። እኛም ለራሳችን ብቻ ማዋል ለቀጣይ ዘር አልባ መሆን ነው ።
የመጨረሻው ቀን ጥያቄ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል የሚል ነው ። የመጨረሻው ቀን ጥያቄዎች ስድስት ናቸው ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።” ማቴ. 25፡35 ። አንዱ ባንዱ ይናበባል ። እንግዳ የተራበ ፣የተጠማ ፣ የታረዘ ፣ የታመመ ፣ የታሰረ ነው ። እንግዳ ፍቅርን የተራበ ነው ። እንግዳ ሰላምን የተጠማ ነው ። እንግዳ ለአገሩ ባዳ ለሰዉ እንግዳ ነው ፤ እንግዳ ሸፋኝ ዘመድ የታረዘ ነው ። እንግዳ ስሜቱ የታመመ ነው ። እንግዳ ባለማወቅ የታሰረ ነው ። ቅርብ ተጉዞ ሩቅ የሄደ የሚመስለው ነው ። እንግዳን መቀበል ራሱን ጌታን መቀበል ነው ። ይህንን ለጻድቃን ገልጦላቸዋል ። በመጨረሻው ቀን የነገረ መለኮት ጥያቄ የለም ፣ በመጨረሻው ቀን ብሉያትና ሐዲሳትን አመስጥሩ አንባልም ። የመጨረሻው ቀን ጥያቄ እንግዳ ተቀብላችኋል ወይ የሚል ነው ።
ኤጶስ ቆጶስ እንግዳ ተቀባይ መሆን አለበት ። እግዚአብሔርን ወክሎ በቤተ ክርስቲያን የተቀመጠ ነውና ስለ እግዚአብሔር ሁኖ እንግዳ መቀበል አለበት ። ቤተ ክርስቲያን የእንግዶች ማረፊያ መሆኗን የደጉ ሳምራዊ ታሪክ ይነግረናል ። ሉቃ.10፡34 ። ትልቁ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ እርሳቸውን ለመክሰስ የመጡትን በቤታቸው እንግድነት አስቀምጠው በችሎት ደግሞ ይዳኙ ነበር ።በቤተ ክርስቲያን ለጥምቀት እየተሰናዱና እየተማሩ ያሉ ንዑሰ ክርስቲያን እንግዶች ናቸው ። ኤጲስ ቆጶስ ሊቀበላቸው ይገባል ። ሕፃናት እንግዶች ናቸው ። በዓለም በረሃ ሲማስኑ የኖሩ እንግዶች ናቸው ። አግኝተው ያጡ ሰዎች እንግዶች ናቸው ። ኤጲስ ቆጶስ እነዚህን ሁሉ መቀበልና እንደ ፍላጎታቸው ማርካት ይጠበቅበታል ።
ከምንረሳቸው ነገሮች አንዱ ይህ ነውና ሐዋርያው፡- እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና” አለ። ዕብ. 13፡1 ።
በእንግዳ ምክንያት በትዳራቸው ላይ ጭቅጭቅ የሚያስነሡ ወገኖች አሉ ፤ አለማወቃቸው በረከታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል ። አንድ ቀንም እነርሱ እንግዳ ሁነው እንደሚሄዱ ረስተዋል ። ይልቁንም ይህን ዓለም ለቀን ስንሄድ በሰማይ እንግዶች ነንና በዘላለም ማረፊያው እንዲቀበለን እኛም በታማኝነት እንግዶች እንቀበል !
በረከቱን ያድለን !
1ጢሞቴዎስ 38
ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ