“ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና።” ሮሜ. 5፡6 ።
አንዳንድ ሰዎች ደስተኞች ናቸው ። ሳቃቸው ያስቃል ፣ ደስታቸው ይማርካል ። የተመቻቸው ባይሆንም ለመደሰት ግን ቁሳዊ ዋስትና አልፈለጉም ። የሕሊና ነጻነት የናፈቃቸው ሰዎች እነዚህን ሰዎች ማግኘትና አብሮ ማሳለፍ ይፈልጋሉ ። እነዚህ ሰዎች የባለጠጎች አጫዋች ሆነው አብረው አገር ካገር የሚዞሩ ፣ በአጫዋችነት ብዙ ገንዘብ የሚያከማቹ ሆነው ይሆናል ። ኮሜድያንም ከተለመደው ሕይወት ወጣ ብሎ ለመሳቅ መድረክ አዘጋጅተው ፣ አስከፍለው ያስቁናል ። የኑሮ ማደንዘዣ የሚሆኑ ጨዋታዎችን እንናፍቃለን ። ለደቂቃም ቢሆን ይህን ዓለም መርሳት እንደ ዕድል እንቆጥረዋለን ። አዎ ለደቂቃም ቢሆን ። የተወለድነው በደቂቃ ፣ የምንሞተውም በቅጽበት ነው ። ደቂቃ ዋጋ አላት ። ተጨንቆ ለሚያውቅ የደቂቃ እፎይታ በብዙ ገንዘብ አትገዛም ። ነጻነት ባይሰጡንም ነጻ የሚያደርጉንን ደስተኛ ሰዎች እጅግ እንወዳቸዋለን ። ውድ ሆነውብን እንደ ፈለግን ባናገኛቸውም ፣ ከአጠገባችን ባይርቁ እንመርጣለን ። የወደድነው ግን ሰብእናቸውን ሳይሆን ደስታቸውን ነው ።
መልከ ቀናን የሚጠላ ፣ ጥሩ አቋም ያለውን የማያደንቅ ጥቂት ሊሆን ይችላል ። መልክ የተሰጠ ቢሆንም ጥበቃ ይፈልጋል ፣ ቁመናም ግንባታና ዲሲፕሊን ይሻል ። ወንዶች ቆንጆ ሴትን ማግባት ይፈልጋሉ ። ጥበቃው እንደሚያደክም ግን አያውቁትም ። ሴቶችም ቁመናው ያማረ ወንድ ባል ቢሆናቸው ይመኙ ይሆናል ። እንዲህ ያለ ወንድ ግን ልቡ ቤት የሚያድረው ጥቂት ነው ። መልክና ቁመና ረጋፊ ቢሆኑም የሰዎችን ጠባይ ግን ይቀይራሉ ። መልክ ያላቸው ጠባያቸው እንደ ሳማ የሚለበልብ ሊሆን ይችላል ። ቁመናቸው ላይ ጊዜ ሲያጠፉ ጠባያቸውን ይረሱታል ። እነዚህን ሰዎች የወደድናቸው ራሳቸውን ሰዎቹን ሳይሆን መልክና ቁመናቸውን ነው ።
ታማኝ ሰዎች ፣ ታማኝ ያልሆኑ ነገሥታትና ባለጠጎች በመብራት ይፈልጉአቸዋል ። በፈርዖን ቤት ሙሴ ፣ በአክአብ ቤተ መንግሥት ነቢዩ አብድዩ ፣ በአርጤክስስ መንግሥት አስቴርና መርዶክዮስ ፣ በቂሮስ አገዛዝ ነህምያ ነበሩ ። የነገሥታት የቅርብ ሰዎች አማንያን ናቸው ። “ታማኝ ሰው ፈልጉልን” እያሉ ባለጠጎች ደጅ ይጠናሉ ። ታማኝነት በመብራት የሚፈለግበት ዘመን ላይ እንዳለንም ምስክሮች ነን ። እነዚህን ታማኞች የምንወዳቸው ስለማይጎዱን ፣ ሕይወታችንንና ንብረታችንን ስለሚንከባከቡ ነው ። ራሳቸውን ሰዎቹን ግን ላንወዳቸው እንችላለን ።
እግዚአብሔር ግን የወደደው ተጫዋችነታችንን ፣ መልከ ቀናነታችንን አሊያም ጥሩ ስማችንን አይደለም ። እግዚአብሔር የወደደው እኛን ነው ። የወደደንም ገና ደካሞች ሳለን ነው ። የሚገርመው የሞተልንም ገና እንደምንበድለው እያወቀ ነው ። ያሉን ነገሮች በዜሮ ሲባዙ የወደዱን ሰዎች ይጠሉናል ። እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ይወደናል ። እርሱ የሚወደው እኛን ነውና ። በድለን ንስሐ ስንገባ እግዚአብሔር እንዲወደን እያደረግን አይደለም ። እርሱ ለዘላለም ይወደናል ። እኛ ከቤት ባንወጣም ፀሐይ ትወጣለች ። እኛን ሳይጠብቅ እግዚአብሔር ወዶናል ። ብዙ ፍቅሮች ይፈተናሉ ፣ መንገድ ላይ ይቀራሉ ። ገና ደካሞች ሳለን የወደደን ግን ደከሙ ብሎ አይጠላንም ። “ምሕረቱ ለዘላለም ነውና” ትርጉሙ “ፍቅሩ ለዘላለም ነውና” ማለት ነው ። እስከ ዘላለም የቃል ኪዳን አጋሮቻችንና ልጆቻችንም አይወዱንም ። አንዲት ድሀ አሮጊት ልጆቻቸው ትልልቅ ቦታ ነበሩና “አይረዱዎትም ወይ?” ብላቸው “አይ ልጄ ዕድሜ ሲረዝም ልጅ አይወድም” አሉኝ።
ጠጪዎችና ሱሰኞች ተግባራቸው መልካም አይደለም ። እነርሱን ከተግባራቸው ነጥለን መውደድ ግን አንችልም ። እግዚአብሔር ኃጢአትን እየጠላ ኃጢአተኞችን ይወድዳል ፤ እኛ ደግሞ ኃጢአትን እየወደድን ኃጢአተኞችን እንጠላለን ። በዘማውያን ላይ ስንፈርድ እንውላለን ። መንገድ ላይ የሚቆሙትን ሴቶች እንደ አገር ጥራጊ እናያቸዋለን ። ክርስቶስ ግን እንደሚወዳቸው ለእነርሱም እንደ ሞተ ዘንግተናል ። የእርሱን የፍቅር ፀሐይ ለማስተላለፍ መስተዋት ልባችን ቆሽሾአል። ካልወደድናቸው እንዴት እግዚአብሔር ይወዳችኋል ብለን መናገር እንችላለን ? ሰውን ከክፋቱ የምንመልሰው በመውደድ እንጂ በመጥላት አይደለም ። እግዚአብሔር በደለኞች በኃይል ሳይሆን በፍቅር መማረክ ይሻል ። እኛ ደግሞ ፍቅርን ትተን በጥላቻ ሰዎችን ለመቀደስ እንፈልጋለን ። እነርሱ በሱስ ወድቀዋል ፣ እኛ ደግሞ በጥላቻ ወድቀናል ።
አዎ እግዚአብሔር የሚወደው እኛን ነው ። ይህ ፍቅር ፍጹም ነውና መጨመርና መቀነስ የለበትም ። በዚህ ፍቅር እባካችሁ ተመሰጡ! የተሰቀለው ክርስቶስ ፍቅሩ ይብዛልን ! አሜን ።
ዕለተ ብርሃን 8
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም.