የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እኛ ማን ነን?

  
                                 የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ — ቅዳሜ ታኅሳስ 5 2006 ዓ.ም
(ማቴ. 11÷16-19)፡፡
ሰውዬው ድንኳን ሰባሪ ነው፡፡ ሁለት ቦታ የአቡዬ ድግስ እንዳለ ይሰማል፡፡ ሰዓቱ ሲደርስ እንደ ተጠራ ሰው የክት ልብሱን ለብሶ ይወጣል፡፡ የሁለቱም ድግስ የተለያየ ቦታ ነበር፡፡ ወደ አንደኛው እየሄደ ሳለ የዚያኛው ድግስ ቢበልጥስ ብሎ ተመለሰ፡፡ ወደዚያም ጉዞ እንደ ጀመረ የዚህኛው ምስር ሆኖ ያኛው ቁርጥ ቢሆንስ ብሎ እንደገና ተመለሰ፡፡ እንዲህ ሲያመነታ ሰዓቱ እያለፈበት ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ በመካከለኛ መንገድ ላይ ቆመና በጭንቀት ‹‹አቡዬ የዛሬን ብቻ ለሁለት ይሰንጥቁኝ›› ብሎ ጸለየ ይባላል፡፡
ዓለምንም እግዚአብሔርንም መያዝ አይቻልም፡፡ ሁለት አባሮም አንድ መያዝ አይቻልም፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎም ሁለት ዛፍ አይወጣም፡፡ አንዷ ብትጠፋ አንዷ ትዳን የምትባል ሁለት ነፍስም የያዘ የለም፡፡ ከካደው ይልቅ መሐል ሰፋሪው የመመለስ ዕድሉ የመነመነ ነው፡፡ ዛሬ አብያተ ክርስቲያናትን ያጣበቡ ‹‹ምንም ይሁን ሰላም ይስጠኝ እንጂ›› ብለው የመጡ ናቸው፡፡ ዛሬን እንቅልፍ መተኛት እንጂ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት አይፈልጉም፡፡ ተባብረው ያድኗቸው እንጂ ፍጡርና ፈጣሪን፣ እግዚአብሔርንና ጠንቋይን አይለዩም፡፡ የሚያሳስባቸው ጉዳያቸው እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር አይደለም፡፡ ማዕዱን ትተው በፍርፋሪ ለመጥገብ የሚመኙ ሚና አጥተው ሁሉ ቦታ አሉ፡፡ ከቤታቸው ወጥተው ያሰቡበት አይደርሱም፡፡ ሁሉ ይጎትታቸዋል፡፡ የሚያዩት የሚሰሙት አፍዞ ያስቀራቸዋል፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ክርስትና አቋም ሳይሆን ፋሽን ነው፡፡ ክርስትና ቃል ኪዳናቸው ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ሊተውት የሚችሉት ነገር ነው፡፡ የንስሓ ዝማሬ፣ ጸሎትና የተሰበረ ሕይወት ‹‹አይመቸንም›› ይላሉ፡፡ መቆዘም የማይፈልጉ ሁልጊዜ የግርግር ደስታን ከ‹‹ሃሌ ሉያ›› የተራቡ ናቸው፡፡
ጌታ ስለ ጠፉት ሦስት ወገኖች ሲናገር አንደኛው ጠፊ ድሪሙ (ገንዘቡ) እቤት ውስጥ የጠፋ ነበር (ሉቃ 15÷8)፡፡ ዛሬም በቤቱ የጠፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሳይድኑ ለማዳን የሚሰብኩ፣ መመራትን ሳያውቁ የሚመሩ፣ ግጥም ገዝተው የሚዘምሩ፣ የገዛ ድምፃቸው አስለቅሷቸው የሚወርዱ ብዙ የጠፉ ወገኖች ዛሬም በቤቱ አሉ፡፡
በድንበር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ቋንቋቸው የተደባለቀ ነው፡፡ የንግድ ልውውጡም የደራ ነው፡፡ ሁለት አገር መሆናቸውን የሚያውቁት ፖሊስ ሲያዩ ነው፡፡ ዛሬም የድንበር ክርስትናን የሚገፉ፣ አንድ እግራቸው ዓለም፣ አንድ እግራቸው ቤተ ክርስቲያን የሆኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ በሰማበት ጣዱኝ የሚሉ፣ ቋንቋቸው የተደባለቀ ሕዝቦች ዛሬም በቤቱ አሉ፡፡ ክርስትናቸውን የሚያስታውሱት ሰባኪ ሲያዩ ነው፡፡ ግን እኛ ማን ነን?
ከእስራኤል ልጆች የሮቤልና የጋድ ነገድ ዮርዳኖስን ተሻግረው መውረስን አልፈለጉም፡፡ ከሚወርድ ጅረት ጋር መታገልን፣ ኢያሪኮን ማፍረስን፣ ጠላትን መደምሰስን አልፈለጉም፡፡ በከነዓን ትይዩ መቀመጥን ፈለጉ (ዘኁ. 32)፡፡ ውጤታቸው ግን ያለ ወንድሞቻቸው በበረሃ ተጠቅተው ቀሩ፡ ዛሬም ከክርስትናው ትይዩ አቅጣጫቸውን እያስተካከሉ የሚኖሩ፣ ዳር ዳር እየተጓዙ የሚቃርሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ውጤታቸው ግን እንዲሁ መና ሆነው መቅረት ነው፡፡ ላመኑበት ዋጋ ለመክፈል የሚፈሩ ለመኖርም ብቁ አይደሉም፡፡
ጌታ፡- ‹‹ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ÷ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ፡- እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል . . .›› (ማቴ. 11÷16-19) ብሏል፡፡ ወንጌል ሲሰበክለት የእኔ አይደለም የሚል፣ ፍርድ ሲሰበክለት እግዚአብሔር አይጨክንም የሚል ትውልድ ምሳሌው ምንድነው? ቃሉን እንደ ኪኒን፣ መዝሙርን እንደ ዘፈን መለወጫ የሚጠቀም ትውልድ ምን ዓይነት ትውልድ ነው?
እና ማን ነን? ማን እንደ ሆንን የምንጠየቀው ከውስጥ ነው፡፡ ደጁን ስናንኳኳ ማን ነው? ስንባል ‹‹እኔ ነኝ›› ካላልን የሚከፍትልን የለም፡፡ ‹‹እኔ ነኝ›› ማለት ካልቻልንም ሕይወት ደጇን አትከፍትልንም፡፡ ሰዎች ማን እንደሆኑ እናውቃለን እንላለን፡፡ ግን እኛ ማን ነን?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ