መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » እውነተኛው የወይን ግንድ

የትምህርቱ ርዕስ | እውነተኛው የወይን ግንድ

አዳም የሰው ልጆች መነሻ ነው ። አዳም የሰው ዘር ግንድ ነው ። የሰው ልጅ ጉዞ የጀመረው በእርሱ የቀጠለውም ከእርሱ አብራክ በተገኙት ልጆች ነው ። ሔዋንም የተገኘችው ከአዳም ነው ። አዳም የመጀመሪያው አባት ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያዋ እናት የሔዋን እናትዋ ነው ። አዳም በኃጢአት በወደቀ ጊዜ ብልየት ወይም እርጅና አገኘው ። ኃጢአት ያስረጃል ፣ የማሰብን አቅም ፣ የመናገርን ብቃት ፣ የመሥራትን ችሎታ ያሳጣል ። በኃጢአት ብልየት ውስጥ ያለ ጽድቅን በነበር ክፋትን በአሁን ያወራል ። አዳም እውነት የሆነውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደ ውሸት ቆጥሮ ሐሰት የሆነውን የዲያብሎስን ቃል እንደ እውነት ተቀበለ ። በዚህ ምክንያት ሐሰተኛ ሆነ ። ሲፈጠር እውነተኛ ግንድ እንዲሆን ነበር ፣ አሁን ሐሰተኛ ግንድ ሆነ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ዳግማዊ አዳም ተብሎ ነው ። እርሱ ርስት አስመላሽ ፣ ጠላትን ተበቃይ ነው ። ራሱ እውነት ስለሆነ እውነተኛው የወይን ግንድ ነኝ አለ ። ሐሰተኛው የወይን ግንድ መራራ ፍሬ እንድናፈራ ምክንያት ሆነ ። እውነተኛው የወይን ግንድ ግን ጣፋጩን የጽድቅ ፍሬ ለማፍራት አስቻለን ። ግንዱ አዳም ሞቶ ስለነበር ቅርንጫፎቹ የሰው ልጆችም በሞት ተይዘው ነበር ። በክርስቶስ ስናምን ከአሮጌው አዳም ግንድ ተነጥለን በአዲሱ ግንድ በክርስቶስ ላይ እንተከላለን ። ሕይወቱንም እንካፈላለን ። አዳም ልጆችን ለሞት ወለደ ፣ ክርስቶስ ግን በዳግም ልደት ምእመናንን ለሕይወት ወለደ ። የበደለው ቃየን ቢሆን ኖሮ እኛ እንተርፍ ነበር ። የበደለው ግን ግንድ የሆነው አዳም ነውና መትረፍ አልቻልንም ። ከምንጩ የደፈረሰ አይጠራምና ሁላችንም በዚህ ዕዳ ተያዝን ። ክርስቶስም ማሻሻያ በማድረግ ፣ አሮጌውን ግንድ በማከም ሳይሆን ሌላ ግንድ በመሆን መጣ ፣ በዚህም ፍጹም ድኅነትን አገኘን ። በአዳም ውስጥ የጽድቅ ምኞት እንጂ ፍሬው አልነበረንም ፣ በክርስቶስ ግን ለሰማይ የምንኖርበትን አቅም አገኘን ።

ገበሬው ወይኑን ሁልጊዜ ይገዝረዋል ። ከገበሬው እጅም ስለት አይጠፋም ። እውነተኛው የወይን ግንድ ክርስቶስ ሲሆን ገበሬው እግዚአብሔር አብ ነው ተብሏል (ዮሐ. 15፡1)። እግዚአብሔር አብም ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል ። ልጁ ካልሞተ ዓለም አይድንምና ። ስለትና ወይን አይለያዩም ፣ ክርስቶስና መስቀልም ለአንድ ቀን ተለያይተው አልታዩም ። ወደ ምድር መውረድ ፣ ከድሀ መወለድ ፣ በበረት መገኘት ፣ በግብጽ መሰደድ ፣ በሰው ሁሉ መጠላት ፣ ቤት አልባ መሆን ፣ የድህነት ኑሮ ፣ በባሪያ እጅ መጠመቅ፣ በሐሰት መከሰስ ፣ በመስቀል ላይ መዋል ፣ በተውሶ መቃብር መቀበር ፣ የሐዋርያት ስደት…. ይህ ሁሉ የመስቀል አካል ነው ። ወይን ስለት ካላገኘው አያፈራም ፣ ክርስቶስም መከራ ባይቀበል ኖሮ እኛን ማትረፍ አይችልም ነበር ። የመስቀሉ ትርፎች እኛ ነን !

አዳም እውነተኛነትን አጣ ። በዚህ ምክንያት በምድር ላይ የውሸት ኑሮ ተጀመረ ። አዳም የምድር ገዥና ትልቁ ንጉሥ ነው ። ውሸት በእርሱ ስለ ተገኘ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የምድር መሪዎች የውሸት አውራ ሠራተኛ ሆኑ ። እውነት የላችሁም ያላቸውንም ባላቸው አቅም የሚያጠፉ ሆነው ተገኙ ። እውነት በነገሥታት ጥቃት ውስጥ ያለማቋረጥ ታልፋለች ። በዛሬው ዓለም ፖለቲካ ተብሎ ሲጠራ ትርጉሙን ውሸት ብሎ ሰው ሁሉ እስኪያስብ ድረስ የአስተዳደር ክብር ወድቋል ። በምድር ላይ ከቤተ መንግሥት እስከ ድሀዋ ጎጆ እውነተኛ ኑሮ እየጠፋ ነው ፣ ብቁ መሪዎች ተደርገው የሚታሰቡም ሕዝብን ማታለል የቻሉት ናቸው ። በወርቅ በአልማዝ ተንቆጥቁጦ የሚወጣው ቆንጆ ውስጡ የተበላሸ ነው ። የራሱ መጨነቅ ሳይደንቀው መጨነቁን ሰው እንዳያውቅበት በብልጭልጭ ይሸፍነዋል ። ብዙ ሕዝብ የሚከተላቸው ዘፋኝና ተዋንያን ሰውን ሲያስደስቱ ራሳቸው ግን ኀዘነተኛ ናቸው ። የውሸት ሳቅ እንዳደከማቸው ይታወቃል ። ባደጉ ከተሞች የቀነጨሩ ሰዎች አሉ ። ባማረ ቤት የሚኖሩ ብዙዎቹ የፈራረሱ ናቸው ። ሕንፃውን አቁሞ ትዳሩ የተበተነበት ፣ ልጆቹ የወደቁበት አያሌ ነው ። ሰዎች በተቃራኒው መኖር ከጀመሩ ቆይተዋል ፣ እንደሚወዱን ሲናገሩ እየጠሉን ሊሆን ይችላል ፣ የጠሉን ሲመስለን ደግሞ በጣም እየወደዱን ነው ። ሰው አድራሻ የለሽ ፣ በቃሉ የማይያዝ ከሆነ ሰንብቷል ። ይህ ሁሉ ከሐሰተኛው ግንድ የተወረሰ ጠባይ ነው ። የሚያሳዝነው የውሸት ኖረን የእውነት መሞታችን ነው ።

ወይን ከሌሎቹ ተክሎች ልዩ የሚያደርገው ሕይወቱ ያለው ግንዱ ላይ ነው ። ቅጠሉ በጣም ቢያምርም በቅጠሉ ላይ ሕይወት የለም ፤ ፍሬው በጣም ቢያምርና ቢጣፍጥም ሕይወት በእርሱ ላይ ስለሌለ ወስደን ብንተክለው አይበቅልም ። የወይን ግንድ የቅርንጫፉና የፍሬው የሕይወት መገኛ ነው ። ከግንዱ የተለየ ወይን ይከስማል ። ክርስቶስ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው ። ምእመናን ቅርንጫፍ ናቸው ። ከእርሱ ተለይተው መኖር አይችሉም ። በራሳቸው ጉልበት ክርስትናን መፈጸም አይችሉም ። አንዳንድ ተክሎች በፍሬአቸው ይበቅላሉ ፣ ሌሎችም በቅርንጫፋቸው ሊበቅሉ ይችላሉ ። ወይን ግን ግንዱ ላይ ሕይወት ስላለ ያለ ግንዱ አይበቅልም ። ያለ ግንዱ ያለ ክርስቶስ ማመንም ፣ ማፍራትም አንችልም ። በፍሬው ግንዱ ይታወቃል ፣ በአማንያን ኑሮም ክርስቶስ ይሰበካል ።

ከቤተሰቡ በሚመጣው ነገር የሚሰጋ ሰው ብዙ ነው ። ባለሙያዎች ጋ ስንሄድ በቤተሰባችሁ እንዲህ ዓይነት በሽታ ነበረ ወይ  ብለው ይጠይቃሉ ። ቤተሰባቸው በሥልጣን ያሳለፈ ከሆነ ብዙዎች አገር ለቀው ይሰደዳሉ ። አገር የገዙ ሰዎች ለልጆቻቸው አገር እንኳ ማውረስ አይችሉም ። በቤተሰባቸው ባዕድ አምልኮ ያዩ የነበሩ ሰዎች በሚገጥማቸው አለመሳካት ሁሉ ያንን ያስባሉ ። ምናልባት ቤተሰባቸው የሚከተለው ሃይማኖት ከዚያ አላስጣላቸውም ብለው ስለሚያስቡም ለመሸሽ ብለው ሃይማኖት ይቀይራሉ ። ስጋቱ ከፍተኛ ነው ። በክርስቶስ ስናምን ግን እንኳን ከቤተሰብ ከአዳም ግንድነት ተነቅለን በሐዲሱ ግንድ በክርስቶስ ላይ እንተከላለን ። ስለዚህ በዘርማንዘር የሚመጣው ዕዳ ሊያገኘን ፣ ክፉም ሊይዘን አይችልም ። ጦርነቱ አብቅቷል ፣ ጠላትም ተሸንፏል ፣ ነገር ግን አሁን በጦርነት ውስጥ እንዳሉ የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። በክርስቶስ ያመነ የቤተሰብ ጣጣ ሊይዘው አይችልም ። ከዚህ በኋላ ለማፍራት ዕድልና አቅም አለውና በጽድቅ መኖር ይገባዋል ።

እውነተኛው የወይን ግንድ አንተ አንተ ክርስቶስ ነህ ። ከእገሌ ተወለድሁ ፣ ዘራችን ከእነ እስክንድር ይመዘዛል ፣ ከነ ቄሣር ይገናኛል ማለት ሐሰት ነው ። እነዚህ ሁሉ የሞትን ሥልጣን ማሸነፍ አቅቷቸው ወድቀዋል ። ታላቅ ቢባሉም ሎቶሪ ወጥቶላቸው ነው ። ታላቅነታቸውን ሲነጠቁም ፍርድ ቤት ቆመው አልተከራከሩም ። የእነርሱ አይደለምና ፀሐዩ ሲጠልቅ አንሰው ወደ ዋሻ ገቡ ። በባሕርይህ ባለሥልጣን ፣ ጌትነት ገንዘብህ የሆነ አንተ ብቻ ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ ። የእገሌ ዘር ነኝ ማለት ለኩራት እንጂ ለጥጋብ አይሆንም ። በአያቱ ድሀ ያልነበረ ባለጠጋ ፣ በአያቱ ባለጠጋ ያልነበረ ድሀ የለም ። ሁሉ ሐሰት ነው ፣ አንተ ብቻ እውነት ነህ ። ጌታ ሆይ የውሸት እየኖርን የእውነት መደሰት እንፈልጋለንና እባክህ ከተኛንበት ቀስቅሰን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም