የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ ጌጥ

 “እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ ።” 1ጢሞ. 2፡9-10
የወንዶች ትልቁ ፈተና አለመጸለይ ነው ። ሁሉን በጉልበቴ አደርገዋለሁ በማለት ከቤት አልፎ በዓለም ላይ ጦርነትን እየለኮሱ ሕይወትን ጭንቅ እያደረጓት ነው ። ወንዶች ጌጥ ፈተናቸው አይደለም ። የተጨማደደ በመልበስ ፣ ያልተጠረገ ጫማ በማጥለቅ የታወቁ ናቸው ። ጌጥን ለመውደድ በረቂቅ ማየት ይፈልጋል ። ከአጠቃላይ አንጻር የሚያዩና ቸልታን የሚመርጡ ወንዶች የጌጥ ፈተና የለባቸውም ። ብዙ ጊዜ ሴቶች ጌጥን በመውደድ ይፈተናሉ ።

ቤተ ክርስቲያን ለየጾታው የሚሆን አምላካዊ ምክር አላት ። ወንዶችና ሴቶችን አድራሻ አድርጋ ለመናገር አምላካዊ አደራ አለባት ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወንድና ሴት ለብቻ ቆመው እንዲጸልዩ በማድረግ አርቃ አጥራለች ። ይህም የሚደነቅ ነገር ነው ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥም የልብስና የጫማ ውድድር እንዳይኖር ወንዱም ሴቱም አንድ ዓይነት ነጠላ እንዲለብስ አድርጋለች ። በዚህም ሀብታምና ድሀ የሚል የኑሮ ልዩነት እንዳይታይ ሠርታለች ። ይህ የሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት በምእመናን መካከል የልብስ ውድድር ውስጥ ገብተው ፣ በጨርቅ ተባርኬአለሁ እገሌ አልተባረከም ወደ ማለት ደርሰዋል ። ክብርት ቤተ ክርስቲያን ግን የሥጋ ነገር ርእስ እንኳ እንዳይሆን አድርጋ አስቀድሞ አጥራለች ። በዚህም ልትመሰገን ይገባታል ። ሰው በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በደጅ ለማሳየት መጣር ያለበት ክርስቶስ ወይም በክርስቶስ የተለወጠውን ሕይወት ብቻ ነው ።
ከቅድስና ትምህርቶች አንዱ አለባበስ መሆኑን ብዙ ክርስቲያኖች የተረዱት አይመስሉም ። ክርስቲያናዊ አለባበስ እጅግ አስፈላጊ ነው ። ምስክርነትና ከዓለም ሰዎች የምንለይበትም ነው ። ይህ ማለት መጎሳቆልና መቆሸሽ ጽድቅ እንደሚመስላቸው ሰዎች እንሁን ማለት አይደለም ። መቆሸሽ ጽድቅ ሳይሆን ስንፍና ነው ። መድኃኔ ዓለም ውኃን አብዝቶ የፈጠረው እንድንጸዳ ነው ።
በአእምሮ ጭንቀት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ከመጠን በላይ ጌጥ ያበዛሉ ። የሚያልፉበትን ሕይወት ሰዎች ያወቁ ሲመስላቸው አንድ ጌጥ ይደርባሉ ፣ አይበቃም ሲሉ ሌላ ይጨምራሉ ። በጣም ማጌጥ ድሎት ሳይሆን ጭንቀትም ሊሆን ይችላል ። አትኩሮትን ፈላጊነት ጌጥን ማብዛት ያመጣል ። ጫማው ድምፅ የሚሰጥ ሲሆን መጣ ፣ መጣ እየተባልሁ ነው የሚል ስሜት ያመጣል ።ሽቶው ለወረዳው የሚሸት ከሆነ አልፌም አልረሳም ብለው ያስባሉ ። ወርቁ የውሻ ሰንሰለት ከመሰለ ሀብታም እባላለሁ በማለት አትኩሮትንና ርእስ መሆንን የሚፈልጉ ወገኖች አሉ ። እነዚህ ሰዎች የምንፈርድባቸው ሳይሆን ትልቁን ጌጥ መንፈሳዊነትን ልናስተምራቸው ይገባናል ።
የዓለማችን ሀብት ከሚባክንባቸው ነገሮች አንዱ ጌጥ ነው ። የጌጥ ትልቁ ችግር ውስጣዊውን ውበት እንድንረሳ ያደርገናል ። ደራሲው “ውበት ማጥመጃ ብቻ ሳይሆን መጠመጃም ነው” እንዳለ ጌጥና ውበትን በጣም መውደድ አይገባንም ። ምድራዊው ውበት መቃብር የሚያበቃ ፣ ጌጡም ተከትሎ ሰማይ የማይገባ ነው ። ሐዋርያው ራስን ስለ መጣል እያስተማረ አይደለም ።ራስን መጣልም ተገቢ አይደለም ። ራሳችንን ከጣልነው የሚያነሣን ማንም የለም ። ብዙ እህቶች ወደ ትዳር ከገቡ በኋላ ራሳቸውን በመጣል ኑሮን ብቻ በማሰብ ይጎሳቆላሉ ። በተገቢው መንገድ ራሳችንን መጠበቅ ግን ይገባናል ። ምክንያቱም ሰውነታችን ከእግዚአብሔር በአደራ የተቀበልነው ነውና ።
እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር ለሴት ልጅ መሸፈን ክብር ፣ ለወንድ ደግሞ እፍረት እንዲሆን አድርጎ ነው ። ሴት ልጅ መሸፈን እንዳለባት የፀጉር ካባዋ ገላጭ ነው ። የሠራን እግዚአብሔር የሚያምርባችሁ እንዲህ ነው ካለን የማንንም ምክር መጠበቅ አያስፈልገንም ። ሴት ልጅ ፀጉሯ ካባዋ ከሆነ ፀጉሯን መንከባከብ አለባት ማለት ነው ። ልታይ በማለት ግን ጌጥን ማብዛት ተገቢ አይደለም ። እዩኝ ፣ እዩኝ ማለት ደብቁኝ ፣ ደብቁኝ ያመጣልና ። ከተማውን ሞልተው የነበሩ ቆንጆ ሴቶች ዛሬ የት እንዳሉ አይታወቅም ። እግዚአብሔር እርሱን ስናሳይ እንጂ ልታይ ፣ ልታይ ስንል አይወድም ። አሁን ካሉት ቆንጆዎች ፣ ዛሬ ካሉት ጌጠኞች ያለፉት ይበልጣሉ ። ሁሉም ጥርኝ አፈር ሁነዋል ። ይህችን ዓለም በጥቂቱ ተረስቶ ማሳለፍ ጤና ነው ። የመሰንበት ምሥጢሩ መሰወር ነው ። ለቅማችሁ መጨረስ እስኪያቅታችሁ ፎቶአችሁን የበተናችሁ መካሪስ ዘመድ አልነበራችሁም ወይ ? እንደ ሞኝ በገዛ ፎቶአችሁ ስትዝናኑ አይገርማችሁም ወይ ? የተፈጠራችሁት ፍቅራችሁን እንጂ ፎቶአችሁን እንድታሳዩ አልነበረም ። የቅዱሳንን ሥዕል ሲቃወሙ የነበሩ ዛሬ በየአምልኮ ቦታቸው የራሳቸውን ፎቶ ሰቅለው ፣ አጋንንት ፎቶአችንን ሲያይ ይወድቃል ይላሉ ።
እንደሚገባ ሰውነትን መሸለም ማለት ዕራቁትነትን መሸፈን ብቻ ሳይሆን የሰውነት ቅርጽንም መሰወር ነው ። የሰው ልጅ ውበት ያለው በልብስ ውስጥ ነው ። እንስሳት ቢከሱ ፣ ቢወፍሩ ያለ ልብስ ያምራሉ ። እኛ ግን ክሳታችንም ውፍረታችንም ያለ ልብስ የሚያምር አይደለም ። ብዙ ሰዎች ለማውለቅ የሚግደረደሩ እስኪመስል የተቦጨቀ ልብስ ጣል አድርገዋል ። ሌሎችም ቅርጻቸው እስኪታይ የተጣበቀ ልብስ ለብሰዋል ። መሸለም ግን የክርስቲያን ወግ ነውና መልበስ ይገባናል ። ይልቁንም በአምልኮ ስፍራዎች ላይ ሴቶች መሸፋፈን ይገባቸዋል ። እንደሚገባ ሳይለብሱ ቤተ መንግሥት መግባት ክልክል ነው ። የእግዚአብሔር ቤት ከቤተ መንግሥት በላይ ነው ።
የሴቶች ውበት የተቀደሰ ማፈር ነው ። እግዚአብሔር ሲፈጥራቸው ተገቢ ማፈርን ውበት አድርጎላቸው ነው ። የማያፍሩ ማለት ተራቁተው የሚለምኑ ማለት ነው ። የሴት ልጅ ክብሯ ለባሏ ብቻ ስትገለጥ ነው ። ተገቢ እፍረት ለወንዶችም አስፈላጊ ነው ። መሰልጠን የራቃቸው ሰዎች ማፈርን ስላቆሙ በድፍረት ነቢይና ፈዋሽ ይሆናሉ ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውን የማያፍር ማለት ትልቅ ንግግር ነው ። ሰው ሁለቱም ነገሮች ሲለዩት ቆሞ የሚሄድ አውሬ ይሆናል ።
ለሴቶች ራስን መግዛት ትልቁ ውበታቸው እንደሆነ ተነግሯል ። ራስን መግዛት ለወንዶች ብቻ የሚነገር አይደለም ። ሴቶችም በተሰጣቸው ኑሮና የትዳር ጓድ ረክተው ሊኖሩ ይገባቸዋል ። የእነርሱ ባል ከሁሉ የተሻለ ነው። ድስት ያለ ግጣሙ እንዲሉ ሰው ባልተሰጠው ቦታ ትርፍ ወይንም ጎዶሎ ነው ። ራስን መግዛት ለዝሙት ብቻ የሚነገር ሳይሆን በንግግርም ፣ በቅንዓትም ራስን መግዛት ይገባል ።
“እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ” ይላል ። መልካም ማድረግ የሴቶች ዋነኛ መገለጫ ነው ። ኤልያስን የተቀበለችው የሰራፕታዋ መበለት ፣ ለኤልሳዕ ቤት የሠራቸው የሱነም ሴት መልካም አድራጊዎች ናቸው ። በየትኛው ዘመን ለአገልግሎትና ለአገልጋዮች የሚያዝኑና የቤተ ክርስቲያን ደጃፍ እንዲከፈት የሚጥሩ ሴቶች ናቸው ። ብዙ ወርቅና ጌጥ የሚያበዙ ሴቶች ለመልካም ሥራ ጊዜም አቅምም እያጡ ይመጣሉ ። መልካም ሥራ ከትርፍ ሳይሆን ከጉድለት ነውና ። ብዙ ልብስ ያላቸው የቱን ልልበስ ሲሉ ሰዓታት ይፈጃሉ ። ቶሎ ለብሶ የሚወጣ ትንሽ ልብስ ያለው ነው ። በመጠን መኖር ጊዜን ማትረፊያ ነው ። ወርቅና ዕንቊም ጠላት ማትረፊያ እንጂ በዛሬ ዘመን ጌጥ አይደለም ። ሰው በቀላሉ የሚያየውንም ኑሮ ሳይሆን የተሰወረውን ሕይወት መምረጥ ይገባል ። ደግሞም ጌጥ ወዳድነት ውድድር የሚወልደው ነው ። ገንዘብ ሥር የለውምና መልሶ መውደቅ እንደሚመጣ በማሰብ ቁምነገር ልንሠራበት ይገባል ።
አቤቱ ጌታ ሆይ ለቤትህ ሥራ የደከሙትን እናቶችና እህቶችን አትርሳ ።
1ጢሞቴዎስ 30
ታኅሣሥ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ