የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ ግርዶሽ

ሐሰተኛ ኑሮ ያደክማል ፣ እውነተኛ ኑሮ ከራስ ጋር ሰላም ያደርጋል ፡፡ እውነተኛ ኑሮን የምትኖረው እግዚአብሔር እንዳለና ሥራህን እንደሚመዝን ስታምን ነው ፡፡ ነጻነት ጨዋነት ከሌለው ተዘዋዋሪ ባርነት ነው ፡፡ ሥጋን ከሚገርፉ ገዥዎች ነጻ አውጥተን ነፍስን በሚገዙ አጋንንት እጅ የወደቀ ትውልድ ካፈራን የምናሳዝን ነን ፡፡ “ከእባብ ጉድጓድ አምልጦ ዘንዶ ጉድጓድ” እንዲሉ ፡፡ ዓላማ የሌለው ጉዞ መንከራተት  ነው ፡፡ በውስጥህ ያለው የኅሊና ሕግ ፣ በመጽሐፍ ያለው የእግዚአብሔር ሕግ በልብህና በተግባርህ እንድትቀደስ የተሰጡህ ናቸው ፡፡  ስለ እግዚአብሔር ለማወቅ በፈለግህ መጠን ወዳጅነትህ እየጨመረ ይመጣል ፡፡ አምላክ ላይሆኑ አምላክ ያሳጡህን አትርሳቸው ፡፡ ፍልስፍናዎች ፣ ርእዮተ ዓለሞች ፣ የበላይ አለቆች ፣ የጦር መሳሪያዎች ፣ የሀብት ድልቦች እነዚህ ሁሉ አምላክ ላይሆኑ ስንቱን አምላክ እንዳሳጡት እወቅ ፡፡ ሰው ላይሆኑህ ሰው ያሳጡህንም አትርሳ ፡፡ አለመርሳት ማለትም ለቀጣዩ ተጠንቀቅ ማለት ነው ፡፡
ኅሊናህን ቸል ብለህ ሰዎችን ወዳጅ ለማድረግ አታስብ ፡፡ የጠፋ ማኅበረሰብ የሚወለደው ከአሉታዊ ነጻነት ውስጥ ነው ፡፡ አሉታዊ ነጻነት ልቅነት ነው ፡፡ አዎንታዊ ነጻነት ግን የመናገር ፣ የመኖር ፣ አሳብን የመግለጥ ፣ የወደዱትን የማመን ፣ የእኩልነት ፣ እግዚአብሔር የሰጠውን የጾታና የዕድሜ መብት የሚያከብር ነው ፡፡ የተፈጸሙ ነገሮች የተጀመሩ ናቸውና ለመጀመር ተነሣ፡፡ የተጀመሩም ይፈጸማሉና ፍጻሜውን አትፍራ ፡፡ ቅዱስ መልአክ ላንተ ያስፈልግሃል ፣ ለደካማው ሰው ግን አንተ ታስፈልገዋለህ ፡፡ ከቆመ መልአክ የወደቀ ሰውን ሊፈልግ እግዚአብሔር ሰው ሆነ ፡፡ የአምላክን እናት ባሰብህ ጊዜ እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን የላቀ ክብር ትረዳለህ ፡፡ ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክ ብለህ ካላመንህ ክርስቶስ ሩቅ ብእሲ ወይም ፍጡር ነው ብለው ማመንህ እንደሆነ ተረዳ ፡፡
የኅሊናን ድምፅ ጠቅጥቀህ የምትመሠርተው ወዳጅነት ራስን ማጥፋት ነው ፡፡ በነፍስህ ዋስትና የሌለበት ሀብት በሬሳ አጠገብ እንደ ተቀመጠ ጥሩ መዓዛ ያለው ምግብ ነው ፡፡ ተገፋን ብለው ወደ አንተ የሚመጡ ሰዎች ምን ሠርተው ወደ አንተ እንደ መጡ አጥና ፡፡ “ጅብ የማያውቁት አገር ሂዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” ይባላል ፡፡ ከሁሉ ፀያፍ ነገር ሃይማኖት ለዋጭነት እንደሆነ እወቅ ፡፡ እግዚአብሔር በድንጋይ ጽላት ላይ ቃሉን ቀርጾ የሰጠን የእግዚአብሔር ቃል ዘመን የማይሽረው መሆኑን ሊያስተምረን ነው ፡፡ ሥነ ምግባር ስታጣ የምታሰድበው እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን አሳዳጊዎችህንም ነው ፡፡ የመጨረሻው ድህነት እግዚአብሔርን ማጣት ነው ፡፡  የመጨረሻ ብልጥግናም እግዚአብሔርን ማግኘት ነው ፡፡ እንደ ነጋ የቀረ ቀን የለምና አትመካ ፣ እንደ መሸ የቀረ ሌሊት የለምና አትሸማቀቅ ፡፡ የምትችለውን ማድረግ የማትችለውን ለማድረግ መንደርደሪያ ነው ፡፡ እውነተኛ የሀብት ውድድር በማጠራቀም ሳይሆን በመስጠት ከሆነ ደስታ አለው ፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ምን ያህል አጠራቀምህ ሳይሆን ምን ያህል ሰጠህ ትባላለህ ፡፡ የማይሰጥ ባለጠጋ ድሀ ነው ፡፡ ድሀ ሁለት ዓይነት ነው ፡፡ የገንዘብና የቸርነት ድሀ ፡፡ ከቸርነት ድሀነት የገንዘብ ድሀነት ይሻላል ፡፡
ከባድ እስር ቤት በራስ አመለካከት መታሰር ነው ፡፡ የሚያቆስለው  ሰንሰለትም የሚሰስት እጅ ነው ፡፡ የጨለማው ወኅኒም ማፍቀር አለመቻል ነው ፡፡ ዓለም ማለት በጎሬህ መጠን ፣ በሰፈርህ ልክ  ከመሰለህ ዘረኛ ሆነሃል ማለት ነው ፡፡ ዘረኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት መግጠም ነው ፡፡ ምክንያቱም ስለ ዘሩ የምትጠላው ያ ሰው ከዚያ ዘር ለመወለድ ያቀረበው አሳብ የለምና ፡፡ እውነተኛ እውርነት ፀሐይን ሳይሆን የፀሐይን ጌታ ማየት አለመቻል ነው ፡፡
የደስታ ቋጠሮ/16
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ሐምሌ 14/2010 ዓ.ም
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ