“ሀብታም ይደኸያል ፣
ሐኪምም ይሞታል ፣
ጎበዝ ይሸነፋል ፣
ብልህ ይሳሳታል ፣
የበራውም ጠፍቶ ፣
የሠሩት ይፈርሳል ፣
ጌጥም ሆነ ጥበብ ፣
ውበት ሆነ ክብርም ፣
ያማረበት ነገር ፣
ማስቀየሙ አይቀርም ።
እስካሁን የማይቀር ነገር ቢኖር ሞት ነው ። ሌሎች ነገሮች በምናልባት ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው ። ሞት ግን እርግጥ ነው ። የመቃብር ስፍራዎችን ቢያንስ በወር አንድ ቀን መጎብኘት መልካም ነው ። ብዙ ያስተምረናል ፣ ትሑት ያደርገናል ። መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብንሄድ ከቆመው ኃያል የሞተው ኃያል ፣ ካለው ምሁር መቃብር ያለው አዋቂ እንደሚበዛ እንረዳለን ። በዋናው በር ስንገባ ፊት ለፊታችን ሦስት ፓትርያርኮች ዐርፈዋል ። ከጀርባው ከቤተ ልሔሙ በስተቀኝ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዐርፈዋል ። ትልቁ ማዕረግ ጵጵስና ነው ። እርሱ አይበቃንም ብለው ፓትርያርክ ለመሆን ይመኙ የነበሩ ፣ በተሰጣቸው ሳይደሰቱ ያለፉ ይኖራሉ ። ግን ፓትርያርክም ጳጳስም በዚህ ስፍራ ዐርፈዋል ። በዋናው በር ስንገባ በስተቀኛችን ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች በስተግራችን አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በመካነ ዕረፍት ውስጥ አሉ ። ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድና ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ እንዳልካቸው በግፍ ተገድለው ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ ከሹመት በኋላ ሃያ ዓመት ታስረው አሁን በዚህ ስፍራ ዐርፈዋል ። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በዚህ ስፍራ ተወስነዋል ። ደራሲ ከፈለግን ከዋናው በር በስተቀኝ ሐዲስ ዓለማየሁና ማሞ ውድነህን እናገኛለን ። እውቅ ዲፕሎማቶች ፣ የታወቁ የጦር ጀግኖች በዚህ ስፍራ አሉ ። ዓለም ኃላፊ ነው ። አለሁ ያለም አንድ ቀን አይኖርም ። የሁልጊዜ ባለሥልጣንና ጀግናም አይኖርም ። ጠባቂ ሁሉ ሞትን መመለስ አይችልም ። ሐኪምም ለራሱ አያውቅም ። አገር እየቆረሰ ይሰጥ የነበረ በሦስት ክንድ ከስንዝር መሬት ተወስኗል ። መሬት ሊረግጥ ይጸየፍ የነበረ ከመሬት በታች ውሏል ። የወርቅ ልብስ ይለብስ የነበረ ድንጋይ ተጭኖታል ። ሲመጣ መንገድ ያዘጋ የነበረው አሁን አጠገቡ ልጆች ተቀምጠው ይጫወታሉ ፣ ማን መሆኑም አይታወቅም ። ጎብኚዎችም ብዙ ተነግሯቸው ማንነቱን መረዳት አይችሉም ።
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በቤተሰባቸው ያልተሰየመ ከተማ ፣ ያልተሰየመ ተቋም አልነበረም ። ዛሬ ግን አንዱም የለም ። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩንቨርስቲ አሁን አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተብሏል ። ተፈሪ መኰንን ይባል የነበረው ዛሬ እንጦጦ ቴክኒክ ት/ት ቤት ተብሏል ። የልዑል መኰንን መታሰቢያ ሆስፒታል ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተብሏል ። ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ዛሬ የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተብሏል ። ልዕልት ዘነበ ወርቅ ሆስፒታል አለርት ተብሏል ። ዐስበ ተፈሪ ይባል የነበረው ከተማ አሁን ጭሮ ተብሏል ። ዛሬ ላይ የምንኖርለት ስማችን ፣ የምንጋደልለት ክብራችን አንድ ቀን ይሻራል ። የደመቅንና የማንረሳ ሲመስለን እንረሳለን ። እንደ ነበረ ያለ ፣ እንዳለም የሚኖር ምንም ነገር የለም ። በዚህ ሁሉ ውሸት ውስጥ የደከመው ማንነታችን እውነት የት ነው ? ይላል ።
ለዘመናት የዘለቁ ፓርቲዎች የምዕራቡ ዓለም የልብ ኩራት ናቸው ። ሪፐብሊካንና ዲሞክራት የሚባለው የአሜሪካ ሁለት ፓርቲ ሦስተኛም ሲጨምር አይታይም ። ወጣትም አይመርጥም ። ታዲያ ሁለቱም ፓርቲ አንድ ዓይነት ሲሆን የተለያየ ጨዋታ ለአገሩ የሚጫወት ነው ። ያቺን አገር ማንም የዓለም ሕዝብ እንዳይወቅስ ዕዳውን ፓርቲዎቹ ይሸከማሉ ። አንደኛው የሚያስፈልገውን ስደተኛ በገፍ ያስገባል ፣ ሁለተኛው እያገደ ያበርዳል ። አንደኛው ብዙ ባጀት በመባጀት ገንዘብ ይበትናል ፣ ሁለተኛው ሲመጣ ይቆጥባል ። እንዲህ እያጫወቱ ይቀጥላሉ ። ታዲያ ለዘመናት የዘለቁ ፣ ተተኪ ፖለቲከኞችን ያፈሩ ፓርቲዎች ይፈራሉ ። በቻይናም የኮሚኒስት ፓርቲው የአገሩ ሕዝብ አምላክም ፣ ቤተ ክርስቲያንም ተደርጎ ይታሰባል ። እነዚህ ሁሉ ሐረገ ትውልዶች እውነትነት የላቸውም ። አንድ እውነተኛ አለ ። እርሱም ሐረገ ወይን ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል ። እውነት ነውና ደስ ያሰኛል ። እውነት ነውና ምዕራፍ ይሰጣል ። እውነት ነውና ከፍለጋና ከመንከራተት ያድናል ። ወይን ግንዱ አያምርም ፣ ቅጠሉና ፍሬው ግን ያምራል ። ባየነው ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት ያልነበረው ፍሬው ግን የጣዕም አውራ የሆነው ፣ ዘንካታው ፣ ከሰማይ እስከ ምድር የተዘረጋው የአብ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። የሚቆይ ነገር ለፈለጋችሁ የነበረውም የሚኖረውም እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
እርሱ ራሱ፡- “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ ፤ ገበሬውም አባቴ ነው ።” ብሏል ።
ተሸክመንህ የምንዞረው ወንጌል ኢየሱስ ፣ የተሸከምከን ኃያል መሢሕ ምነው እንዲህ በርተህ ፍጥረት አላወቀህም ? በገዛ ቤትህ ፣ በገዛ ዓለምህ እንደ ባይተዋር ለምን ተገፋህ ? አለሁ እያሉ ብዙዎች ጠፉ ፣ መጣሁ እያሉ ብዙዎች ቀሩ ። አንተን እውነት የሆንከውን ፣ ከምሰሶ ይልቅ ቤትን ያጸናኸውን አለመውደድ ምንኛ መበደል ነው ! አንተ የአብ ጸዳል እባክህ ብራ ፣ እባክህ አብራ ፣ እባክህ ፍቅር ይብራ ። ነፍስ ሁሉ አውቃህ በብርሃንህ ትጋረድ ። ለብሰን የተራቆትን ፣ አግኝተን ያልረካን ነንና አሁን አድነን ። እስክትመጣ እስክንመጣ በሰላም አኑረን ። አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም.