ከአባቱ ጋር የዘመን እኩያ የሆነ፣ እናቱንም የፈጠረ ልጅ ከክርስቶስ በቀር ማንም የለም። እንደ ተፈጥሮ ሥርዓት አብ ወልድን የወለደ አይደለም፣ አብርሃም ይስሐቅን ቢወልድ በዘመን ቀድሞ ፣ በክብር በልጦ ነው፤ አብ ወልድን በመውለዱ በዘመን አይቀድመውም፣ በክብር አይበልጠውም። እናቱንም የፈጠረ ልጅ ከጌታችን በቀር የለም። አብን አህሎና መስሎ ፣ በክብር ተካክሎ ዘላለማዊ ልደት የተወለደው፣ እኛን መስሎ ፣ ቤዛ ሊሆነን ከድንግል ተወለደ። ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች። በእናቱ እቅፍ ጡት እየለመነ በዚያው ቅጽበት ዓለምን ይመግብ ነበር ። ታናናሽ ጣቶች ያሉት ያ ሕፃን ዓለምን በመሐል እጁ የያዘ ነው። ሰማያውያን ሊያደርገን ምድራዊ የሆነ፣ ድህነታችንን ተካፍሎ ባለጠጋ ሊያደርገን የመጣ አንዱ ክርስቶስ ነው።
ከእግዚአብሔር ሳንለምን የምንቀበለውና ለምነን የምንቀበለው ነገር አለ። ድንግል ማርያም ያለመነችውን ተቀበለች። የአምላክ እናት ለመሆን ለምና አታውቅም። እርሱ ግን እናቱ ትሆን ዘንድ መረጣት። በዚህም ሁለት ነገርን ማየት እንችላለን፦ የመጀመሪያው እግዚአብሔር የለመነውን ይሰጠናል፣ እንደ ሰውነታችን ብንለምን እንደ አምላክነቱ ይሰማናልና ከለመነው በላይም ይሰጠናል። እግዚአብሔር ከዚህ በላይ ያለመነውን ይሰጠናል። ለምነን ከምንቀበለው ይልቅ ሳንለምን በምርጫው የሚሰጠን እጅግ ትልቅ ነው። ድንግል ማርያም መሢሑን ከሚጠብቁ መካከል ብትሆንም መሢሑን ግን እኔ ልውለድ ብላ ለምና አታውቅም። ሁለተኛው እግዚአብሔር የማይደገም ነገር ይሰጣል። ከእርስዋ በፊትም ከእርስዋ በኋላም አምላክን ለመውለድ የተመረጠች ሴት የለችም፣ አትኖርም። እግዚአብሔር የሰጠን ነገር ሌላ ቦታ የማይገኝ ልዩ ነገር ነው።
በመልኩና በአምሳሉ መፈጠራችን ያለመነው ልዩ በረከት ነው። ከሰማይ ወደ ምድር እንዲወርድ ፣ መልካችንን መልኩ እንዲያደርግ ያስገደደው የራሱ ፍቅርና ፈቃድ ነው። ውሉደ እግዚአብሔር፣ የሰማይ ቤተሰቦች የሆነው ያለመነውን በሚሰጥ በእግዚአብሔር ነው። ሰው ሆነን መፈጠራችን፣ ከእንስሳት ወይም ከእጽዋት አንዱን ሆነን አለመገኘታችን የእግዚአብሔር ምርጫ ነው። እግዚአብሔር የመረጠልን ነገር ለራሳችን አስበን ከምንለምነው የላቀ ነው። ሺህ ጊዜ ለራሳችን ብናስብ እልፍ ጊዜ ብንጸልይ እርሱ የመረጠልንን አያህልም። የምንወለድበትን ዘመንና ቦታ፣ የሚዛመዱንን ቤተሰቦች የመረጠው እርሱ ነው። ከዚህ በፊት ባያውቁንም ስንወለድ በደስታ የሚቀበሉንን ሰዎች ያዘጋጀ እርሱ ነው። የለፉበትን የሚያወርሱን ፣ ያላቸውን የሚሰጡን፣ በይቅርታ የሚቀበሉን ወላጆች የሰጠን፣ ለእኛ አንጀታቸው ስስ የሆነ አባትና እናት ያዘጋጀልን እግዚአብሔር ነው ። እርሱ ያለመኑትን ይሰጣል፣ ሁልጊዜ በሥራው ትክክል የሆነው ፣ በመጥራቱ የማይጸጸተው ጌታ ውድ ነገርን አዘጋጅቶልናል።
ምድራውያን የሚያጩን ለምድራዊ ነገር ነው፣ እግዚአብሔር ግን ለሰማያዊ ነገር ያጨናል። የበረታች ነፍስ የደከመን ሥጋ መሸከም ትችላለች ፣ ነፍስን የሚያበረቱ አገልጋዮች ያስፈልጋሉ። ለአገልጋይነት መመረጥ ትልቅ ዕድል ነው። ቃሉን መስማት ማንም የማይቀማው በጎ ዕድል ነው ከተባለ ቃሉን ማሰማት ደግሞ የበለጠ ዕድል ነው። እግዚአብሔርን ለማገልገል ጥሪና ምርጫ ከሰማይ ሲመጣ ከምድር ደግሞ የባለቤቱ ፈቃድና ትጋት ያስፈልጋል። ጥሪው ማቅረቢያ ሲሆን ምርጫው ጸጋህ ይህ ነው መባል ነው። እግዚአብሔር አስፈቅዶ የሚያድን ፣ በቤቱ የሚሾም አምላክ ነው። ፈቃደኝነት ከሰው ይጠበቃል። ትጋት ጸጋን ያቀጣጥላል፣ ያበዛል። ጸጋ እሳት ነው፣ እሳት ቆስቁሱኝ የሚል ነው። ጸጋ ከሰነፍ ላይ አይበዛም፣ ሊወሰድም ይችላል። ሌሊትና ቀንን፣ ክረምትና በጋን የሚያፈራርቀው አምላክ ሰነፍ ልጆች የሉትም። ሳይዘናጋ ፍጥረቱን የሚጠብቀው ጌታ ቸልተኛ ልጆች የሉትም። እግዚአብሔር ያለመነውን ይሰጣል።
እግዚአብሔር ለሚሰጠን ጸጋ፣ ለሚሾመን መንበር አስቀድሞ ያዘጋጃል። ዮሴፍ በእስር ቤት ለቀጣዩ ሥልጣን እንደ ተዘጋጀ እግዚአብሔር በማይጠበቁ ስፍራዎች ሳይቀር እያዘጋጀን ሊሆን ይችላል። መጪውን ነገር በማሳወቅ ያዘጋጃል፣ በመከራ ውስጥ በማሳለፍም ያዘጋጃል፣ በትምህርት ያዘጋጃል ፣ የመምህራን ደቀ መዝሙር በማድረግም ያዘጋጃል። ያለ ዝግጅት የመጣ ሀብት እብድ ያደርጋል፣ ሞትንም ያፋጥናል። እንዲሁም ባካናና ጠፊ እንዳንሆን እግዚአብሔር ያዘጋጀናል።
ደስታችንን መመሥረት ያለብን ከምድር ሳይሆን ከሰማይ በሆነው ነገር ላይ ነው። ምድራዊ ነገር ሕልም እልም ነው። ታይቶ ጠፊ ፣ አብቦ ረጋፊ ነው። ልደትን ሞት ይከተለዋል፣ ሹመትም በሽረት ይለወጣል። ከደስታው ዘመን የኀዘኑ ዘመን ይበልጣል። የሰው ልጅን የደስታ ጥም ሊያረካ የሚችል የማይለወጠው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
ምናልባት በጓደኞቻችን፣ በጎረቤቶቻችን ራሳችንን እየለካን እናዝን ይሆናል። ከእነርሱ ይልቅ የተባረክን እኛ ልንሆን እንችላለን። በረከታችንም ራሱ እግዚአብሔር ነው። በዚህ ደስ ሊለን ይገባል። ደስታን የሚቀማን ከሌሎች ጋር ራስን ማነጻጸር ነው። እኛ ጋ ያለው ማንም ጋ የለም። እግዚአብሔር በተፈጥሮአችን ፣ በመልካችን ልዩ አድርጎ ፈጥሮናል። ሰውነታችንን፣ ጾታችንን መቀበል አለብን። የደስታ መንደርደሪያ የሆነው መቀበል ነው። የሆነውን ያልተቀበለ ሰው በጥያቄ ይኖራል። ዓለም ክፉ ነውና የሆንከው ትክክል አይደለም በማለት እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር እንድናርም ይገፋፋናል። ውጤቱ ግን ሕይወትን መጥላት ይሆናል።
ሳንለምን በተቀበልነው፣ ያለ ልፋት በጸጋ በተቸርነው ነገር ከውዳሴ ከንቱ መጠበቅ አለብን። መደንገጥ ያለብን ሲረግሙን ሳይሆን ሲያመሰግኑን ነው። “ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና ” ይላል (ሉቃ. 6፣ 26 )። ሞት ወደ ዓለም የገባው በውዳሴ ከንቱ በርነት ነው። የሆንኩትን የሆንኩት በእግዚአብሔር ነው ፣ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን ማለት ተገቢ ነው ። አስደንጋጩ ነገር መመስገን እንጂ መነቀፍ አይደለም። ዓለም አስብቶ አራጅ ነውና ሲያመሰግኑን ጌታ ሆይ እርዳኝ ማለት፣ ምስጋናውንም ለባለቤቱ መመለስ አለብን። ይህች ዓለም ሆሳዕና ብላ አመስግና ይሰቀል ብላ የምትገድል ናትና።
በዚህ ዓለም ላይ የምናገኛቸው ነገሮች ሁሉ ፍርሃትን የሚያመጡና የሚጨምሩ ናቸው። የእግዚአብሔር ስጦታ ብቻ፣ የእርሱ መሆን ብቻ ከፍርሃት ያድናል። የመረጠልን ከመረጡልን ይበልጣል። ያለመነውን የሰጠን የምንለምነውን አይከለክለንም። ምስጋና ወደር ለሌለው ስጦታው ! አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 6 ቀን 2018 ዓ.ም .