የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እግዝእትነ – እመቤታችን

አዳምና ሔዋን ከገነት በወጡ ቀን ስለ አንቺ ሰምተዋል (ዘፍ. 3 ፡ 15) ። አዳም ስለሚወለደው ወንድ ልጅ አሰበና የእኔን በደል እርሱ ይክሳል አለ ። ሔዋንም አንቺን አሰበችና የእኔ ውርደት ይሻራል አለች ። በሴት በኩል ሞት መጣ ፣ በሴት በኩልም ሕይወት ተገኘ ። ከዔድን ገነት ጀምሮ አንቺ ታስበሻል ። ሙሴ ነገረ ተዋሕዶን በደብረ ኮሬብ በራእይ አይቷል (ዘጸ. 3 ፡ 2)። መለኮት ኃይሉን ፣ ሥጋም ውስንነቱን ሳይለቅ በተዋሕዶ ጽንዐት እንደሚኖር ተመልክቷል ። ኢሳይያስ ስም ጠርቶ ስለ አንቺ ተናግሯል (ኢሳ. 7 ፡ 14)። ከኢሳይያስ እስከ ልደተ ክርስቶስ ሰባት መቶ ዓመት አልፏል ። ሰባት መቶ ዓመት አንቺ ትታሰቢ ነበር ። አንቺም ቅዱሳት መጻሕፍትን ትወጃለሽና ይህችን ድንግል ትናፍቂያት ነበር ። ድንግል ፣ ድንግልን ትወዳትና ትናፍቃት ነበር ። ይገባኛል ብትዪ አትወልጂውም ነበር ። ራሱን የሸለመ ንጉሥ አይሸልመውም ። ራሱን ራስ ፣ ደጃችማች ያለ የንጉሥ እውነተኛ ሹመት ያልፈዋል ። እኔ ለዚያ የበቃሁ አይደለሁም ያሉ ግን ብቃት ላይ ይደርሳሉ ። አንቺም የዚህች ድንግል ገረድ መሆንን ስትመኚ በአማን ወላዲተ አምላክ ሆንሽ ። የጌታው እናት ነሽና እመቤታችን እንልሻለን ። እመቤት በረከሰበት ፣ ሁሉ እመቤት ተብሎ በሚጠራበት ዘመን ፣ አንቺን እመቤቴ ለማለት የሚፈተኑ ምስኪኖች ብዙ ናቸው ። የተባረከ ልጅ ሳይወልዱ አምላክን የወለደችን የሚንቁ አያሌ ናቸው ።

አምላክ ሰው ሆነ እንጂ ፣ ሰው አምላክ አልሆነም የሚሉ በክርስቲያን ስም የሚጠሩ አሉ ። ዛሬ በመንበረ ሥላሴ የእኛን ሥጋ ለብሶ የተቀመጠው ኢየሱስን ካመኑ እርሱ በተዋሕዶ አንድ አካልና አንድ ባሕርይ ካልሆነ በሥላሴ መንበር ላይ አራተኛ አካል ፣ ሁለተኛ ፈቃድ አለ ማለታቸው ነው ። ደግሞ ሰው አምላክ ካልሆነ በመንበረ ሥላሴ እንዴት ሊቀመጥ ይችላል ? በተዋሕዶ የማይቻለው ተችሏል ። የሚከብደው የአምላክ ሰው መሆን ፣ የማይቻል የሰው አምላክ መሆን ተችሏል ። ሥጋ አምላክ ካልሆነ እግሩን ይዘው የሰገዱለት ፣ ጨርቁን እየዳሰሱ የዘመሩለት ጣዖት አምላኪዎች ሆነዋል ። ሰብአ ሰገልም፡- “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት ፥ ወድቀውም ሰገዱለት ፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት” ተብሎ ተጽፎላቸዋል ። ሕፃኑ ስግደት የተቀበለው ሰው አምላክ ስለሆነ ነው ፣ አሊያ ሕፃን ብቻ ከሆነ ሰብአ ሰገል ጣዖት አምልከዋል ፣ በዕድሜም በሀብትም በጥበብም ከእነርሱ ለሚያንስ በመስገዳቸው ራሳቸውን አዋርደዋል ። ደግሞም ነገሥታት ከገበሩለት የነገሥታት ንጉሥ ነው ፣ ሲወለድ አልጋ ወራሽ የሚባል እንጂ ንጉሥ የሚባል ከክርስቶስ በቀር ማንም የለም ። ሰው አምላክ ባይሆን ንጉሥ ተወለደ ተብሎ ነገሥታት ባልገበሩለት ነበር ።

እመቤታችን ሆይ ! እመቤት ተብሎ መጠራት ምድራዊ ቋንቋ ነው ። በሥላሴ ምልዕተ ጸጋ ተብለሻል ። ይህንንም ገብርኤል ገልጦልሻል ፣ መልእክተኛ ነውና ሳይጨምር ሳይቀንስ ነግሮሻል ። ልጅ ለመውለድ አሳብ አልነበረሽም ፣ አምላክን እወልዳለሁ የሚል ትዕቢትም አልተጠጋጋሽ ። የድንግልና ኑሮሽ ሳይፋለስ ፣ አምላክ ካንቺ ሰው ሆነ ። ሔዋን ነጻ ፈቃድዋን ተጠቅማ እንደ ሳተች ፣ አንቺም ነጻ ፈቃድሽን ተጠቅሞ አምላክ አደረብሽ ። ክቡር ያከብራልና አከበረሽ ።

እመቤታችን ሆይ ልጅሽ በምድር አባት ቢኖረው ኖሮ መልአኩ ወደ ዮሴፍ በተላከ ነበር ። ኤልሳቤጥን ትቶ መልአኩ ለብሥራት ወደ ዘካርያስ ሄዷል ። ዮሐንስ የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ልጅ ነው ። የወለድሽው ግን በምድር አባት የለውምና መልአኩ ወደ አንቺ መጣ ። በሰማይ ልደቱም እናት የለውምና አንቺ አንድ እናቱ ነሽ ። በምድር አባት ቢኖረው በሰማይ አብ አባቱ ፣ በምድር እገሌ ወላጁ ይባል ነበረ ። አንድ ልጅ ነውና አንድ አባት አለው ። ደም እንዲደርቅ ልጅ እንዲወለድ ይደረጋል ። ከተዋለዱ በኋላ በቀል የለምና ። አንድ ልጁን ወደ ዓለም የላከው ሊበቀለን ሳይሆን ደምን ሊያደርቅ ነው ። ተዛምደናልና የእኛ ጉዳይ በችሎት ሳይሆን በቤተሰብ ጉባዔ የሚታይ ነው ። እመቤታችን ሆይ ! ይህን ምሥጢር በቅርበት ለማየት ተመርጠሻልና ደስ ይበልሽ! ልጅ የተሾመላቸው እናቶች እንኳን ደስ አላችሁ ይባላሉ ። ያንቺ ልጅ ግን የማይሾሙት ንጉሥ ፣ የማያበድሩት ባለጠጋ ነው ። እግዚአብሔር ተጠቅሞ የሚጥል አምላክ አይደለም ። አንቺንም ተጠቅሞ እንደ ጣለሽ የሚያስቡ ስተዋል ። እንዲህ ከሆነ ለእኛም ዋስትና የለንም ። በአብርሃም ቃል ኪዳን እስራኤል እስከ ዛሬ ይታሰባሉ ፣ ጥሎ አይጥሌው ከአብርሃም የምትበልጪውን አንቺን እንዳከበረሽ ይኖራል ። አንቺን አብነት ያደረጉ ደናግላን ፣ ትውልድሽ ናቸውና ይጠብቃቸዋል ።

እመቤታችን ሆይ አንቺ አምላክን ፀንሰሽ ፣ ዮሐንስን የፀነሰችውን ኤልሳቤጥን ለመጎብኘት ወጣሽ ። የበለጠ ቢኖርሽም ኤልሳቤጥን አከበርሽ ። በሌላው ደስታ ለመደሰት ቅንነት ሀብትሽ ነው ። የኤልሳቤጥን መፅነስ ማንም አልነገረሽም ፣ ሰማይ ምሥጢሩን ገለጠልሽ ። ቅዱሳን ሳይነጋገሩ ይግባባሉ ። ኤልሳቤጥም አንዱን መንፈስ ጠጥታ ፣ አምላክን መፅነስሽን አወቀች ። ዮሴፍ በዓይኑ አይቶ ያላወቀውን ፣ ዓይኖችዋ የደከሙ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ አይታ ተናገረች ። መጠጥ ያናግራልና ቅዱስ ውኃ አንቺን ትንቢት አናገረ ፣ ኤልሳቤጥንም አስፈከረ ። የተከበረችው የጌታዬ እናት ያለችሽን እኛም እመቤታችን እንልሻለን ። እመቤቶች ወርቅ የሰበሰቡ ናቸው ፣ አንቺ ግን ወርቅ ኢየሱስን የወለድሽ እመቤት ነሽ ። እመቤቶች ባሪያ አስገባሪ ናቸው ፣ አንቺ ግን ለተጨነቁ የምታዝኚ ነሽ ። እመቤቶች ባለ ርስት ናቸው ፣ አንቺ ግን የሰማይ ባላገር ነሽ ።

እመቤታችን ላንቺ ሰላምታ ይገባሻል ፣
ከሴቶች ሁሉ ተመርጠሻል !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ