መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ኧረ ተወኝ ጌታዬ ! » ኧረ ተወኝ ጌታዬ ! -1

የትምህርቱ ርዕስ | ኧረ ተወኝ ጌታዬ ! -1

አምጣው ብዬ እለምንሃለሁ ፣ መጥቶ ሲያስጨንቀኝ ምኞቴን እጠላዋለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ሕይወትን በዋጋው ፣ ኑሮዬን በልኬ እንድይዘው እርዳኝ ። ሮጬ ፣ ሮጬ የገደል አፋፍ ስደርስ ፣ ፈቃድህን ትቼ የእሳት ባሕር ላይ ስቃረብ ኧረ ተወኝ ጌታዬ መቃብሩን ምሰህ አውጣኝ ። መቃብር ሁሉ ሦስት ክንድ ከስንዝር ነው ፣ የምኞት መቃብር ግን እጅግ ሰፊ ነው ። ሬሳ ሁሉ በመቃብር ሲወሰን ጠበበኝ አይልም ። ተወዛዋዥ ሬሳ የሆንኩት እኔ ግን ዓለም ጠቦኛል ፤ ኧረ ተወኝ ጌታዬ ኖሬ እንድመጣ እባክህ እርዳኝ ። በዛሬው የትላንቱን እጠላዋለሁ ፣ በአሁኑ የቅዱሙን ወዳጅ እሸኘዋለሁ ፣ የቅጽበት ደስታ በዘላለም የሚባዛ ይመስለኛል ፤ ኧረ ተወኝ ጌታዬ ሰውነቴን አንተ አትርፋት ። ከራሴ አምባጓሮ ሲገጥመኝ አስታራቂ አጣለሁ ፣ ከሰው ጋር ግብግብ ስገጥም ሰሚ እቸገራለሁ ፣ መልሼ ራሴን አፍረዋለሁ ። የእኔ ነገር ሰጥቶ መንሣት ፣ ሰዶ ማሳደድ ፣ ስሞ መንከስ ፣ አፍቅሮ መክሰስ ነው ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ከሰማይ የወረደ ለምድር አይከብደውም ፣ እኔን ግን ከብዶኛል ፣ በቸርነትህ አግዘኝ ።

ላይቀር ሞት ምን ያስጨንቀኛል ? ይላል የሰው ልጅ ። ይህ ዓለም ግን ሞት እንግዳው ፣ ችግር አዲሱ ነውና ሁልጊዜ ያውካል ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ እንደ ፈላስፋ ብኖር እንኳ እንደ ክርስቲያን መሞትን አትንሣኝ ። ፍትሕን እፈልጋለሁ ፣ ቸርነትንም አስሳለሁ ። ሰዎችን በፍርድህ ፣ እኔን በምሕረትህ አግኘኝ እላለሁ ፣ በቅዱሳን ጉባዔ ዕራቁቴን እንዳልቆም ኧረ ተወኝ ጌታዬ አንድ ቀን እንኳ የማገልገል ጥበብ ስጠኝ ። ትንሹ ትልቅ ሁኖ ሲታየኝ ፣ ብናኙ ተራራ መስሎ አላሳልፍ ሲለኝ ፣ ለሰው የማይሰማ ድምፅ ለእኔ እየተሰማ ሲያውከኝ ፣ ልጄንና ወዳጄን በአሳብ እየገደልሁ ስባንን ኧረ ጌታዬ ምን ልሆን ነው ? እባክህ ለራሴ አትተወኝ ። የያዝሁትን ሳላጣጥመው ሌላ ያምረኛል ፣ ሳሙኤል ልቤ ኤልያብን እየመረጠ ያሳስተኛል ፣ ሰውን በኑሮው ቀርቶ በረቀቁ ቃላቱ መመዘን ጎድቶኛል ፣ ለአገር ያጨሁት ባለቁመና ለራሱም የማይሆን ሲሆን ነቢይነቴ ይህን አያውቅም ወይ ? ብዬ ራሴን እታዘባለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ያንተን ዓይን ስጠኝ ፣ መልክን ሳይሆን ልብን ማድነቅ ይሁንልኝ ።

ዳግም ላንገናኝ ብዬ ክፉ ማድረግን ለምን መረጥሁ ? ዳግም ለማያገኙት ያለችው የደግነት ዕድል ዛሬ ብቻ መሆኗን እረሳለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ዓይኔን ላጠፋ ዓይን ላጥፋ ማለትን ከእኔ አርቀው ። የእርሱ ዓይን ቢጠፋ ሁለት ዕውር እንሆናለን እንጂ የእኔን ጨለማ አያበራውም ። ግዙፍ ዓለምን ሳስስ በረቂቁ ምሥጢር ላይ ቸልተኛ ሆኛለሁ ። ሥጋዬን ሳደልብ ነፍሴን ረስቻለሁ ፣ የልቤን በልቤ ይዤ ወዳንተ እቀርባለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ የምትወደውን ባሪያህን ለሚጠላው አሳልፈህ አትስጠው ። በቃላት የማይገለጸውን ፍቅር ፊደልና አንቀጽ ከምሰበስብለት ፣ በተግባር እንድፈጽመው እርዳኝ ። ሲፈልጉኝ ውለው ሳያገኙኝ የሞቱትን ሳስብ አዝናለሁ ። እኔን ቢያገኙ ሞት ይቀርላቸው ነበር ወይ ? ብዬ ከሄደ ነፋስ ጋር እታገላለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ቀሪ ዘመኔን ከጸጸት እንድትጠብቀው እማልድሃለሁ ። አምላኬ ሆይ ዕንባ ዕንባ ይለኛል ፣ ለማልቀስም ጉልበት አጣለሁ ፤ ሳቅ ሳቅ ይለኛል ፣ ለመሳቅም ጊዜው ነው ወይ ? እላለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ከዚህ መልክ የለሽ ዘመን እኔን አትርፈኝ ።

በራሱ የሞተ ባንተ የሚድንብህ ፣ የማለዳው ብሥራት ፣ አንተ የንጋት ኮከብ ፣ በዚህ ጭው ባለው በረሃ ዓለም ላይ እኔን ለማን ተውከኝ ? የመንፈስህ ምስክርነት አምላክህ ካንተ ጋር ነው ሲለኝ የጠላት ክስ ደግሞ ብቻህን ነህ ይለኛል ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ በደግ ሥራ የሚጸጸቱበት ዘመን መጥቷል ፣ ያዘሉት ካልተንጠለጠልሁ ይላል ። ከዚህ ቅርንጫፉን ሲይዙት ከሚገነጠለው ዓለም አውጣኝና ወይነ አብ በሆንከው ባንተ ግንድነት አጽናኝ ፣ አማጽነኝ ። ኑሮዬ ትርጉም ፣ ሞቴም አድራሻ ያለው እንዲሆን ለንስሐ አብቃኝ ። ብቻዬን መንገዱን አላውቀውም ፣ ጠላቴንም አልችለውም ፤ እረኛ ደግሞ አልፈልግም ። እየደጋገመ ከሚመታኝ ያለ ማወቅ እንቅፋት እባክህ አትርፈኝ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ በመቻልህ አስችለኝ ።

ሥልጣን ካላሰለጠነ ፣ ሹመት ሺህ ሞት ካልሻረ ምን ይረባል ? ልጅ በሌለበት አባት መባልስ መቼ ይገባል ? ከፍታን ስመኘው ሕዝቤን ከፍ ለማድረግ ይሁንልኝ ። ስፍራውን ለለቀቀው ፣ ችግር የቅርብ ዘመዱ ለሆነው ፣ ስሜቱ ለሚለዋወጠው ፣ በብልጦች ብልጠት ለሚዘረፈው ወገኔ አስባለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ሳልዋጋ ጎፈሬ ያምረኛል ፣ እቶኑ ቀርቶ ወላፈኑ ይጥለኛል ። ለጫጩት ልቤ የፈተናው ስም ያርደኛል ። እውነተኞችን ደረቅ አልሁኝ ፣ አታላዮችን ጠላሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ የምመርጠውንም አላውቀውምና ይቅር በለኝ ። የደጎች ግፍ አለብን ፣ የሚወዱንን ጠልተናል ። ስለዚህ በሚጠሉን መጫወቻ ሆነናል ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ እስቲ ልኑርበት ፣ መልካም ያልሁት ቅብ መልካም አይሁንብኝ ። ላዩም ውስጡም አልማዝ የሆነ ሕይወት ስጠኝ !

ሰው ነው ብለህ አትፈትነኝ ፣ አንተ እንደምታነሣኝ ታውቃለህ ፣ ተፈትኖ አለማለፍ ግን የእኔ ሰቀቀን ነው ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ የቅዱሳንን ልብ አድለኝ ፣ የሃይማኖት ጀግኖች ከዋሉበት አውለኝ ። በአማኑኤል ስምህ በፈሰሰው ደምህ ። አሜን !

ግንቦት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ