የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከልቤ እንዳይወስዱህ …

ሚሊየኖችን ለድጋፍ ሰልፍ የሚሹ ፣ ስለ አንድ ነፍስ መጥፋት የማይረበሹ ፣ እነርሱ ሲዘፍኑ ትክክል ተብለው ሌላው ሲዘምር የሚተቹ ፣ ከቤትህ ሊነቅሉኝ የሚታገሉኝ ፣ በአንተ ስም ምድርን ሊወርሱ የሚሹ ከልቤ እንዳይወስዱህ ጌታዬ እባክህ እርዳኝ ። ተናግሮ አናጋሪዎች ዝም የማለት መብትንም የሚገፍፉ ፣ አሳቃቂ ሁነው አንገት እያስደፉ ፣ ወገኔ የማይሉትን እያጠፉ መኖር የለመዱ ከልቤ እንዳይወስዱህ እባክህ ጌታዬ እርዳኝ ። ቤትህን የግላቸው ንብረት ያደረጉ ፣ በጉንጫቸው ስድብ የተሞሉ ፣ በኅብረ ቃል ታናሽነቴን ሲያብራሩ የሚውሉ ከልቤ እንዳይወስዱህ ጌታዬ ጠብቀኝ ። አንገታቸው የማይቀለስ ፣ ልባቸው የማይመለስ ፣ እኛ ከጠላን ማን ይወደዋል ? እኛ ካረከስን ማን ይቀበለዋል ? ብለው ሲያጥላሉ የሚውሉ ከልቤ እንዳይወስዱህ እባክህ ጌታዬ እርዳኝ ።

ወንድማቸውን ሰቅለው ስለ ስቅለትህ በእንባ የሚያወሩ ፣ የሌላውን ክብር እየገፈፉ መራቆትህን የሚተርኩ ፣ ራሳቸውን ነዋሪ ሌላውን አኗኗሪ ያደረጉ ከልቤ እንዳይወስዱህ እፈራለሁ ጌታዬ ጠብቀኝ ። ጥላሸት የሚቀቡ ፣ የሰውን ስም ለማጉደፍ ለዘመናት ጭቃ ይዘው የቆሙ ፣ የራሳቸውን ከሀዲ ፈላስፋ የሚያደርጉ ፣ የሌላውን አማኝ መናፍቅ የሚሉ ፣ ብዙኃንና ሕግ አለሁ የሚላቸው ፣ ብቸኛን ማጥቃት ሥራ የሆነላቸው ከልቤ እንዳይወስዱህ እፈራለሁ ጌታዬ ጠብቀኝ ። ኢየሱስ ኢየሱስ እያሉ በአደባባይ ጥብቅና የሚቆሙልህ ፣ ሰይጣንን በዕድሜ አንሰው በተንኮል የሚበልጡ አዎ እነርሱ ከልቤ እንዳይወስዱህ ፣ መልካምነትህን እንዳይጋርዱብኝ እሰጋለሁ ። ጠላቶቼን እኔ እጠብቃለሁ ፣ አማኝ ነኝ ከሚሉ ጨካኞች አንተ እንድትጠብቀኝ እለምንሃለሁ ። ንጹሑ ምንጣፍ ላይ ከነጭቃቸው የቆሙ ፣ በጽዱ ልብስ አውሬነታቸውን የሸፈኑ ከልቤ እንዳይወስዱህ እለምናለሁ ።

አንተ የሠራኸውን ሲያፈርሱ የሚውሉ ፣ በንስሐ የተመለሰን የሚከስሱ ፣ በይቅርታ የማያምኑ ፣ ለታሪካቸው ሲሉ ያንተን ሕማም መከራ ገደል የጣሉ ከልቤ እንዳይወስዱህ እሰጋለሁና ጌታዬ ጠብቀኝ ። ለምድርም ለሰማይም እኩል የሚታዘዙ ፣ መድኃኒትም መርዝም የጨበጡ ፣ ማሊያ እየለዋወጡ የሚጫወቱ ፣ ለበረታው የሚዘፍኑ ፣ ቃላቸውን በመለዋወጥ የትውልድን ልብ የሚያመረቅዙ ከልቤ እንዳይወስዱህ እሰጋለሁና ጌታዬ ጠብቀኝ ። ገድለው የሚያለቅሱ ፣ ዝናብ እየተቀበሉ ጠል ለመስጠት የማይፈቅዱ ፣ ሕይወቱን የሰጣቸውን እየናቁ ፈገግታቸውን ውለታ አድርገው የሚያስከፍሉ ፣ የሚሹትን እስኪያገኙ እንደ ድመት ለስላሳ የሆኑ ፣ ካገኙ በኋላ ጥፍራቸውን የሚሞርዱ እነርሱ ከልቤ እንዳይወስዱህ እፈራለሁ ጌታዬ ጠብቀኝ ። ወድቀው በወደቀ የሚስቁ ፣ ሰውዬው የሚያመሰግንበትን ጉድለት እየነቆሩ ለምሬት የሚያነሣሡ ፣ የእነርሱን ኃጢአት ጽድቅ የሌላውን እውነት ሐሰት የሚሉ ፣ ሌላው ሲናገረው እውነቱን እየነቀፉ እነርሱ ግን ሲሉት ትክክል ነው የሚሉ ፣ ሚዛን ጥለው ሚዛን የሆኑ ፣ ለአገር ለሃይማኖት እኛ ብቻ ነን የሚሉ እነርሱ ከልቤ እንዳይወስዱህ እሰጋለሁ ።

ሳልናገር የሚናገሩኝ ፣ ሳልነካ ድንበሬን የሚጥሱብኝ ፣ ዝም ስል ዝም አትልም የሚሉኝ ፣ የመኖርና የመሞት መብቴን የነፈጉኝ ፣ የማዘን አዳምነቴን ረስተው ስሜት እንደሌለው ሰው በጭካኔ የሚወጉኝ አንተን ከልቤ እንዳይወስዱህ እፈራለሁ ። ለመዱ ሲባል አውሬ የሚሆኑ ፣ ሰው ሳይሆኑ ራሳቸውን መልአክ ነን ብለው የሚስሉ እነርሱ ከልቤ እንዳይወስዱህ እሰጋለሁ ። የሰውን ሥራ እያየሁ ያንተን ደግነት ስረሳ ፣ በምድር ሆኜ የገነትን ኑሮ ስሻ ፣ የማይታየውን መንግሥትህን ዘንግቼ በሚታየው ስታወክ ፣ ተስፋህን ረስቼ በእምነት ስወድቅ ፣ ያለውን የመጨረሻ አድርጌ የሚመጣውን ሕይወት እንደ ባዶ ተስፋ ስመለከት ፣ ያደረጉልኝን ሳይሆን ያደረጉብኝን ሳስብ ፣ ከክፉ ነገር ውስጥ ያወጣኽልኝን በጎ ነገር ስረሳ ያን ቀን ከልቤ እንዳላጣህ ፣ እንደ መግደላዊት ማርያም “ጌታዬን ወስደውታል” ብዬ የማትወሰድ መሆንህን እንዳልዘነጋ ፣ በትንሣኤ ቀን እንዳላለቅስ እባክህ ጌታዬ ድረስ ። “እነርሱ በክፋታቸው ምን ሆኑ ?” ብዬ በኃጢአት ቦምብ ኳስ እንዳልጫወት የተነሣኸው ኢየሱስ ክርስቶስ ልቤን መልስ ። በአሳቡ ተናውጦ ባንተ የረጋ እርሱ አሜን ይበል !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ