የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከሐፍረት መዳኛችን

“ጌታ ሆይ ፥ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው ።” ዳን. 9 ፡ 8 ።

ጌታ ሆይ ! ያሉትን ደጎች እየገደልን የሞቱትን ደጎች እናከብራለን ። ታማኝነትን ጥለን ታማኞችን እንናፍቃለን ። ዕድላችንን ለዓለማዊነት ሰጥተን ልጆቻችንን ለመንግሥተ ሰማያት እናጫለን ። የተረፈንን ለመስጠት ተቸግረን ዋናቸውን ለምን አልሰጡም ? ብለን በሌሎች ሀብት እናዝዛለን ። የራሳችንን ድሆች ባዕድ እንዲረዳልን እንከጅላለን ። የደስታ እንጂ የመከራ ወዳጅ መሆን አቅቶን የታሰሩትን ወዳጆቻችንን እንሸሻለን ። እንዳይኖሩ የፈረድንባቸውን እንዲያስቡ እንመኛለን ። የራሳችንን ፈተና ወድቀን ለሰዎች መፈተኛ ገደል እናዘጋጃለን ። ያየናቸው ሕፃናት ላይ ጨክነን አዲስ ልጆችን ወደ ዓለም ለማምጣት እንሻለን ። እንዲሁ መካድ ስንችል የፖለቲካውን እሳት ለማግኘት ምለን እንክድሃለን ። ለመመስከርም ምለን ፣ ለመካድም ምለን እንዴት እንችለው ይሆን ?

ከኃጢአት በመመለስ ፣ ጽድቅን በመከጀል እኛም ተምረን ፣ አንተም መሐሪ ትባላለህ ፤ አሁን ግን ወንድ መባል በልጦብን ፣ ዲያብሎስን ለመምሰል መጸጸትን ጠልተናል ። ጽድቁ ያለው አንተ ጋ ሳለ በሰው ላይ በመፍረድ ተጠምደናል ። “እገሌማ ካልተቀጣ እኔ አልጠየቅም” ብለን በክፉዎች ትከሻ ተከልለን ለመትረፍ እንሞክራለን ። እውነትን በመላምቶች ተክተናል ። አየር አስገብተን እስክናስወጣ በመርዶ ዜና ተይዘናል ። እባክህ ጌታ ሆይ ፈጥረህ ላልፈጠሩን ጨካኞችና አዋቂዎች አሳልፈህ አትስጠን ።

ዓለም መራራ ብትሆንም በአገራችን ሰማይ ላይ የሚወጣው ፀሐይ እጅግ ያሳርራል ። የዘመን ፍጻሜ ላይ ብንሆንም የመከራችን ልክ ግን መስመር አጥቷል ። የሰው ደግነት ከሚታደገው በላይ አልቃሾቻችን በዝተዋል ። ታተርፈናለህ ብለን ወደ አንተ መጥተናል ። የዘመድ ገራፊ የሚያመውን ቦታ ስለሚያውቀው እጅግ ያሳምማል ። ከራስ እስከ እግር ያለው በሐፍረት ተመትቷል ። አንተን የሚያህል አምላክ ፣ እኛን የሚያህል ደካማ የለምና በዓይነ ምሕረት ተመልከተን ። ዓለም ሲጨልም ዓለማችን በሆንከው ፣ ሞተህ ዓለምን ባዳንከው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለሙ አሜን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ