“በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው” (ሉቃ.2፥7)
ጨካኙ ዓለም እስካሁን ለእርጉዞችና ለወላዶች ይራራል። በሰለጠነው ዓለም በሕዝብ መጓጓዣ አውቶብስና ባቡር ውስጥ የእርጉዞች ወንበር አለ። ሕይወትን የተሸከሙ ፣ ትልቅ ስጦታ የሆነውን ልጅ የያዙ ናቸውና ሁሉም የሰው ልጅ እንክብካቤ ያደርግላቸዋል። በግፍ ስለ ተገደሉ ሴቶች ሲነገር እገሌ እርጉዝ ነበረች ተብሎ እንደ ሁለት ሞት ይተረካል። ሁለት ነፍስ ነው የያዘችው በማለት ለእርጉዝ ያማራትን መስጠት፣ ምቹ ቦታ ላይ ማስቀመጥ የአገራችን ባሕል ነው። ድንግል ማርያም ግን ያውም የመውለጃዋ ሰዓት ተቃርቦ ማንም አላዘነላትም። ፊቱን የሚያፈካላት፣ ቤቱን የሚከፍትላት፣ ደጁን የሚያከራያት አላገኘችም።
አማኝ ስንሆን የተለየ እንክብካቤ የምናገኝ ይመስለናል። እግዚአብሔር ግን የጠራን ለምቾት ሳይሆን ለራእይ ነው። ሃይማኖት የመዝናኛ ስፍራ ሳይሆን የመሥዋዕትነት ቦታ ነው። እንደውም ክርስቲያን ስንሆን ለማንኛውም ሰው የሚደረገው ማኅበራዊ ክብርና ጥቅም ሊቀርብን ይችላል። ድንግል ማርያም ድርስ እርጉዝ ሁና ይህን አላገኘችም፣ የመውለጃዋ ወራት ተቃርቦ ዓለም ለእርስዋ ስፍራ አልነበረውም።
በጤና መርጃ ተቋማት ሊወልዱ የተቃረቡ ሲመጡ ሁሉም ባለ ሙያ ወደ እነርሱ ይሮጣል። በየባሕሉ ምጡ ሲፋፋም እሳት አቀጣጥለው ፣ ከበው ማርያም ማርያም ይላሉ። ማርያም ራስዋ ግን ይህን አላገኘችም። የእግዚአብሔር መሆን ላለመነካት ዋስትና አይደለም፣ የመስቀሉ ወዳጅ ሆኖ በዓላማ መጽናት ነው። ብዙዎችን ያጽናና እርሱ ግን አይዞህ ባይ ሊያጣ ይችላል። ያች በምጥ የተያዘች ሴት ማርያምን አስቢ እያሏት ነው። አንድ ቀን መከራችን ለሌሎች የብርታት ድምፅ ይሆናል። አንቺስ ተከበሽ ነው ፣ ማርያም ሁሉ በሩን ዘግቶባት ጎረቤት ሳይደርስላት እንደ ወለደች አስቢ እያሏት ነው። በእውነት ቡሩካኑ በተጨነቁበት ዓለም እኛ ክፉዎቹ ብንጨነቅ ምን ይደንቃል?
በአይሁድ ባሕል አንዲት ሴት ለመውለድ ስትቃረብ የዜማ ሰዎች የዜማ መሣሪያዎችን ይዘው ቤቱን ከበው ይጠባበቃሉ። የመውለድዋ ዜና ወደ ውጭ ሲወጣ የተወለደው ወንድ ከሆነ ዜማው መሰማት ይጀምራል። ታላቅ ደስታም ይሆናል። ያ ቤት ብቻ ሳይሆን መላው እስራኤል ወንድ ልጅ እንደ ተጨመረለት ይቆጠራል። መሢሑ ሲመጣ ዓለምን እንገዛለን የሚል አሳብ ስለ ነበራቸው ያ ወንድ ልጅ እንደ ባለሥልጣን ይታይ ነበር።
ድንግል ማርያም የመውለጃዋ ሰዓት ሲቃረብ ማደሪያ አጣች። ማንም የማይፈልገው የከብቶች በረት አገኘች። በበረቱ ውስጥ ዘመድ አዝማድ ጎረቤት አልነበሩም፣ ከበረቱ ዙሪያ መሣሪያ የያዙ ሙዚቀኞች የሉም። ታላቅ ፀጥታ የሰፈነበት፣ መገፋትና ብቸኝነት ያጠላበት ይመስላል። ዮሴፍ በዚያ የድካም ዘመኑ ምን ማድረግ ይችላል ? ረዳትዎችዋ አረጋዊው ዮሴፍና ወጣትዋ ሰሎሜ ናቸው። እነርሱስ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? በለመዱት በናዝሬት ቢሆን ይሻል ነበር ። የሚያውቃቸውና የሚያስጠጋቸው በሌለበት ፣ በብርድ ወራት፣ የመውለጃዋ ወራት ሲቃረብ፣ በሩ ሁሉ ለእነርሱ ዝግ ሲሆን፣ በበረት መውለድን ሲያዩ ምን ያህል ይሰማቸው ይሆን?
ለዓለሙ ጌታ እንዴት በሮች ዝግ ሆኑ? ሁሉ የእርሱ የሆነው እንዴት ሁሉን አጣ? የሰውን ያህል እንኳ አቀባበል እንዴት አላገኝም? ይህ ሁሉ ጥያቄ በዚያ በረት ውስጥ ከሰው ሕሊና አስተጋብቶ ይሆናል። በዚህ ጊዜ የሰማይ መላእክት ሰማይና ምድርን በዝማሬ አናወጡ። እረኞችንም በረት ውስጥ የከብቶቻችሁ ማደሪያ ውስጥ የተፈጸመውን ታላቅ ነገር እዩ ተባሉ። ሳያውቁት በረትን ለጌታ ለቀዋልና ለልደቱ ተጋባዥ ሆኑ። በበረቱ ዙሪያ የዜማ ሰዎች ባይኖሩም የመላእክት ምስጋና ተሰማ።
እጁም ልጁም ያልሰጠውን ማን ሊክሰው ይችላል? ከሰማይ ግን መልስ አለ። አንዳንድ መገፋቶች ልክ የላቸውም። መከራው የሚያስጠጋ ወገን የታጣበት ፣ ደስታው የሚተባበር ወዳጅ የሌለበት ሲሆን ይረብሻል። ወገን ለወገን የሚያደርገውን ክብር ማጣት ያስቆጫል። በጌታችን ልደት ሳያውቁት በረት የፈቀዱት እረኞች ዋጋ ተቀበሉ፣ ብዙ ባለቤቶች ይህን ተግባር ቢፈጽሙ ኖሮ በከበሩ ነበር። ዛሬ ቤተ ልሔም የጌታን የልደት በዓል የሚያከብሩ ጎብኚዎችን በግዙፍ ሆቴሎች ትቀበላለች። ባለቤቱን ግን አልተቀበለችውም። ባለን ትንሽ ነገር ጌታን ስናገለግል ዋጋችን ከፍ ያለ ይሆናል። ምናልባት እነዚያ እረኞች እኛ በረቱን እንለቃለን እናንተ ግቡ ብለው ይሆናል። ማንም ያላየውንና ያልሰማውን ክብር ለማየትና ለመስማት በቁ ።
ስንቱ በጥባጭ ልጅ ሲወለድ የዜማ መሣሪያ ይዘው ይመጡ የነበሩት የሰላም አለቃ ሲወለድ ግን አልነበሩም። ለጌታ ሲሆን ልማዶች ቀሩ፣ እንደ አምላክ ሳይሆን እንደ ፍጡርም የሚቀበለው አልተገኘም። ክርስቶስ በምድር ላይ የተገኘለት ነጻ ቦታ በረትና መስቀል ብቻ ነበር። ከወገን ከዘመድ የምንጠብቀው እልልታ ፣ የደስታ ተካፋይነት ባይኖር የመላእክት ምስጋና በሰማይ ይሰማል። በመመለሳችን በአርያም ዝማሬ ይሆናል (ሉቃ.15:7)። ሰማይ አማኝነትን፣ ተነሣሒነትን ያከብራል። ወገን ሲርቅ እግዚአብሔር ወገን ሆኖ ከእኛ ጋር ቆሟል። ከላይ ተቀብለናልና አጣሁ ብለን መማረር፣ ከለከሉኝ ብሎ ሰው መውቀስ ሊበቃ ይገባዋል። ከሰው ብንቀበል ከእግዚአብሔር አናገኝም ነበርና።
የሚያስጠጋን፣ ለአንድ ቀን መከፋት የምንሄድበት የለንም ይሆን? ምጣችን አይዞህ ባይ ፣ ግፋ ወዳጄ የሚል አጥቶ ይሆን? ይህ ሁሉ በክርስቶስ ሆኗል። የእርሱ መከራ ለእናቱ ተርፏል። መጠላታችንን ጌታ ተቤዥቶታል። ደስታችን የሚያስደስተው ሰው የለም ብለን እናስብ ይሆን? ዕድሎቻችንን መደበቅ እንደ ዋስትና ቆጥረነው ይሆን? ጌታም ሲወለድ የተደሰተ ጎረቤት አልነበረም። ወንድ ልጅ ተወለደ ብሎ ያለ ዘመኑ ከሰባት መቶ ዓመት በፊት የዘመረው ኢሳይያስ ነው። በዘመናችን የተገፋን ፣ ያለ ዘመናችን የተከበርን እንሆናለን። ዓለም ህልውናችንን ካላከበረ መቃብራችንን ማክበሩ አይቀርም። አብሮን የሚደሰት ብናጣ ቅዱሳን መላእክት በምስጋና ሊተባበሩን ቆመዋል። እንደውም ስለ እኛ መዳን አስቀድመው ዜማ ጀምረዋል።
ከምድር የጎደለ ከሰማይ ይሞላል፣ የጎደለው ለበለጠ ክብር ነው። ሙዚቀኞች ሲቀሩ ቅዱሳን ዘማሪዎች ይመጣሉ።
ተመስገን !!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓ.ም