ክብርህን ጠብቅ
የሰው ልጅ ክብር ለማግኘት የሚኖር ብቻ ሳይሆን ክቡር ሆኖ የተፈጠረ ትልቅ ፍጡር ነው:: የሰው ልጅ አለማወቅ ፈተናው ቢሆንም ትልቁ ፈተናው ክብሩን አለማወቁ ነው (መዝ, 48 ፥ 20) ። የሰው ልጅ በክብር የተፈጠረ ክብርንም የሚጠብቅ ነው። ክብር የሰጠውና ክብር የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው:: እውነተኛ ክብር ከእግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር ያከበረውንም የሚያዋርደው የለም። ሰው በመፈጠሩ አርአያ ሥላሴ ክብሩ ሲሆን በሃይማኖት በምግባር በመጽናቱ ደግሞ የክብር ሽልማት የሚጠብቀው ነው:: የክብራችን ጀማሪና ፈጻሜው እግዚአብሔር ብቻ ነው።
በዓለም ላይ ያሉ ዝና፣ ከበሬታ፣ አንቱታ፣ ማዕረግ፣ ሽልማት በአብዛኛው ጉልበታቸውን ለበኣል ላንበረከኩ፣ ለሰይጣን ለሰገዱ ፣ የክፉው ማኅበር አባል ለሆኑ የሚሰጥ ነው። የላኛውን ሽልማት ላለማጣት የምድሩን ሽልማት መሸሽ የአማኝ ወጉ ነው። ለአንድ ነገር ሁለት ሽልማት የለም፣ በምድር የተቀበለ በሰማይ አይቀበልም። በምድር ያልተከበረ ሰማይ በታላቅ ክብር ይጠብቀዋል።
ዓለም የዜና ርእስ መሆንን ክብር ትለዋለች። በቀይ ምንጣፍ ላይ መሄድን ክብር ብላ ትጠራዋለች። እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር እንዳናይ ሰይጣን አስመስሎ የሠራቸው ማታለያ አሻንጉሊት ናቸው። የዓለም ክብር በገዳይነት፣ በደፋርነት፣ በነውረኛነት የሚገኝ ነው:: በብዙ ጥልፍልፍ ውስጥ አልፈው፣ ስንቱን ባልንጀራ ሠውተው፣ እውነተኛውን ታጋይ አጥፍተው የሥልጣን ማማ ላይ የሚቀመጡ የምድር ክቡራን ናቸው። ክቡር ተብለው መጠራታቸው የጉባዔ ውሳኔ እንጂ የቅድስናቸው ውጤት አይደለም:: መጽሐፉ እግዚአብሔርን የማያውቁ የምድር ነገሥታትን “አውሬ” እያለ የሚጠራቸው በሰማይ ክብር ስለሌላቸው ነው። በሰው ታሪክ በንግሥናቸው እግዚአብሔርን ያከበሩ ጥቂት ናቸው:: ብዙዎቹ አማልክት ነን ብለዋል፣ ያላሉም አማልክትነት ይሰማቸው ነበር ።
ደፍረው እኔ እንዲህ ነኝ ብለው ራሳቸውን የቀቡ ፣ ሕዝብ አያስተውልምና ተከታይ ያበጁ፣ ለምድራዊ ጥቅምና ክብር ብለው ኑፋቄን የሚፈበርኩ አሉ። ከዚያ አልፈው
አጋንንታዊ አስማትን እየተጠቀሙ በእግዚአብሔር ቤት የሚያታልሉ፣ ትርኢት የሚያሳዩ ብዙ ናቸው። የኑፋቄ አራማጆች የሥልጣንና የክብር ጥመኞች ናቸው። የክብር ጥማት ከአጋንንት ሳይቀር ግርማ ወሞገስ ያስናፍቃል።
ክብር ማለት ብዙ ዓይኖች እኛን ማየታቸውን ፣ ብዙ እጆች ለእኛ ማጨብጨባቸው አይደለም። ክብር ብዙዎችን ለአንድ ማንነት ማሰለፍ ሳይሆን ለብዙዎች መኖር መቻል ነው። አንዱ ሁሉ ሞተ የሚለው ታላቁን ክብር የሚገልጥ ነው:: ብዙዎች ለእኔ ይኑሩ ሳይሆን እኔ ለብዙዎች ልኑር የሚያሰኝ እርሱ ታላቁ ክብር ነው። የብሉይ ኪዳን ካህን፣ ካህን እንጂ መሥዋዕት አልነበረም፤ የሐዲሱ ኪዳን ካህን ግን መሥዋዕትም ነው። እርሱ ሊቀ ካህናት የተሰኘላቸው የሐዲስ አገልጋዮች ካህን ብቻ ሳይሆኑ መሥዋዕት መሆን ይገባቸዋል። ጥሪው ካህን አድርጎት ሊሆን ይችላል:: የራሱ ፈቃድ ግን መሥዕዋት ያደርገዋል ። ክህነት ጥሪ ሲሆን የሚፈጸመው በመሥዋዕነት ነው :: የክርስቶስ ትምህርቱ፣ ተአምራቱ ሳይሆን የመጨረሻው ማኅተሙ መሥዋዕትነቱ ነው ::
በብሉይ ኪዳን ድንኳን ውስጥ ሁሉም ንዋየ ቅድሳት ሲኖሩ ወንበር ግን አልነበረም። ክብርም ረጅም ወንበር ላይ ተቀምጦ አምኃ መቀበል አይደለም:: ክብር ሌሎችን ማገልገል ነው:: በዓለም ላይ የከበሩ ደፋር አላዋቂዎች፣ ብልግናን አቆንጅተው የሚያቀርቡ፣ ሀልወተ እግዚአብሔርን የማያምኑ ናቸው።
ሰዎች አብሮአቸው የሚበላ መሪ ይናፍቃሉ፣ አብሮአቸው ሲበላ ደግሞ ይንቃሉ:: ጌታችን አብሮ ቢበላ የዘማዊ የቀራጭ ወዳጅ ተባለ ። ዮሐንስ መጥምቅ ከሰው ርቆ በበረሃ ቢኖር ታላቅ ነው ብለው ሁሉም ፈሩት። የሰው ጠባይ አስቸጋሪ ነውና እንደ ጠባዩ ክብራችንን መጠበቅ የግድ ነው:: በሮም ሲኖሩ እንደ ሮማውያን ይባላል። ከመናገር በፊት ማደመጥ፣ ከመጻፍ በፊት ማሰብ፣ ከመሞት በፊት መኖር ያስፈልጋል።
አንተ ወዳጄ ክብርህን ጠብቅ። ሰውን አራት ነገሮች ያዋርዱታል:-እነርሱም ንግግር ፣ ዘማዊነት ፣ መጠጥና ብልጠት ናቸው። ሕይወትም ሞትም በምላስ ላይ ተቀምጧል። የምላስ አቀማመጥ ወደ ደጅ ገደል ወደ ውስጥም ገደል ነው። “አፍ ያለው ካፋፍ ነው ላቹም ታቹም ገደል” እንዲሉ:: ዘማዊነት ከወጣት እስከ ሽማግሌ ያዋርዳል፣ የመሥራት አቅምን ይይዛል። መጠጥም ክብርን ያሟጥጣል። አሁን እንጠጣዋለን ቀጥሎ እርሱ ይጠጣናል። በቅርቡ በተደረገ ጥናት ጠጪዎች ከማይጠጡ ሰዎች ዕድሜአቸው በ15 ዓመት ይቀንሳል ። መጠጥ ገዳይ ነው። ሰው ከፍሎ የሚሞተው መጠጥ ላይ ነው። ጠላት ያለበት አይጠጣም፣ ከጠጣም አይቆይም። የመንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች አይጠጡም፣ ከጠጡ የመንግሥታቸው ምሥጢር ይወጣል። በብዙ ኤምባሲዎች የመጠጥ ግብዣ የሚደረገው የአገራት ምሥጢር በመጠጥ ውስጥ እንዲወጣ ለማድረግም ነው። ሞኙ በነጻ የተገኘ መስሎት ሲልፈው ይላፋል::
ክብርን ለመጠበቅ:—
ብዙ አለመናገር ፣ በሁሉ ቦታ አለመገኘት፣ ፊት ፊት አለመታየት ፣ በወቅታዊ ርዕስ ላይ አለመናገር፣ ወገን አለመያዝ፣ ላሸነፈ አለመዝፈን፣ ያለ ቦታው ገንዘብን አለመበተን፣ ድንበርን አለማስደፈር፣ ከባለጌዎች ጋር አለመቃለድ፣ ለሁሉም ነገር መልስ አለመስጠት፣ ባልተማረ ማኅበረሰብ ዘንድ በጣም ቅርብ አለመሆን፣ ከሰዎች አለመጠበቅ ፣ ልሂድ ያለን አለመለማመጥ፣ ከተማሪ ጋር ብዙ አለማሳለፍ፣ ሁሉን ለሁሉ አለማሳየት፣ የከበሩትን ማክበር ፣ በመጠን መኖር፣ ጉቦን መጸየፍ ፣ ሁሉን ማክበር ፣ ሰው ቤት ብዙ አለማዘውተር፣ በቀላሉ አለመገኘት ፣ ራስን ማጣጣልን ማቆም ፣ ሳይጠይቁን ምክር አለመስጠት ፣ አፍን ማከም ፡ በልክ መብላት ሆዳም አለመሆን— አስፈላጊ ናቸው። እነዚህን ሁሉ ለመተንተን ጊዜ ያጥረናል ::
እግዚአብሔር ነገሠ ፣ ክብርንም ለበሰ ::
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም.