መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -12

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -12

እገሌን  በጣም እወዳለሁ አትበል

በኢትዮጵያ ውስጥ በቀደመው ዘመን ወላጆች ልጆቻቸውን እንደሚወዱ ሲናገሩ ተሰምቶ አያውቅም። ወላጆች ግን ለልጆቻቸው የተግባር ፍቅር ነበራቸው። ምንም ትዳራቸው ምቹ ባይሆንም ልጆቼ እንዳይጎዱ በማለት መስቀል ተሸክመው ኖረዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን መሳም፣ ትክ ብሎ ማየት አይወዱም:: በዚህ ምክንያት ፍቅር የለሽ እንደሆኑ ይታሰብ ይሆናል። ፈረንጆች ልጆቻቸውን መሳም፣ እወድሃለሁ እወድሻለሁ ብለው መናገር ያዘወትራሉ። ለልጆቻቸው ግን የሚከፍሉት ዋጋ ራስን በማይጎዳ መልኩ ነው። ልጁ አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላው ከቤት ለቆ ይወጣል። የእኛ አገሩ ባለ አሥራ ስምንት ዓመት እናቱ ገላውን ታጥበዋለች :: ያ ልጅ ወዶ ፈቅዶ ኑሮ ይዞ እስካልወጣ ድረስ ወላጅ እስከ ዕድሜ ልክ የእኔ ዕዳ ነው ብሎ ያስባል ። ከዚህ በላይ ፍቅር የት አለ?
በርግጥ የወላጆች ስስ መሆን ልጆች እንዳይጠነክሩ አስተዋጽዖ ያደርጋል። ፍቅሩም ተግሣጹም በልክ መሆን አለበት። ወላጆች ልጆቻቸውን አይስሙም ፣ አዎ ቀደም ያሉት ልጃቸውን በሙሉ ዓይናቸውም አያዩትም። ምክንያቱም ከሳሳሁ ፣ ልጄ ከሌለ  ምን እሆናለሁ ? ካልሁ ያኖረኝን  እግዚአብሔር አስቀይመዋለሁ ፣ ልጄ ጣዖት ሆኖብኝ ከእግዚአብሔር እለያለሁ፣ ልጄንም አስቆርጠዋለሁ ፣ እግዚአብሔር ጣዖት የሆነብንን ነገር መስበር ልማዱ ነው ብለው ስለሚስጉ  ልጆቻቸውን በጣም አያዩም ። አዎ ዛሬ ላይ ከሌሎች ተውሰን ልጆቻችንን መሬት አይንካችሁ ብንልም በሱስ እየተሰበሩ፣ በተስፋ መቍረጥ እየደቀቁ ነው። የድሮ ልጅ ሙት ተብሎ የማይሞት፣ በገመድ ታስሮ፣ በበርበሬ ታጥኖ የሚቋቋም፣ ወላጁን የማይቀየም፣ ለእናቴ ለአባቴ ይህን አድርጌ ተመርቄ የሚል፣ ወላጅንም የሚጦር፣ አንቱ እያለ በጌቶች ክብር አባቱን የሚጠራ ነበር ። የዛሬው ትውልድ ግን ፣ በመሳም እወድሃለሁ በሚል ሙዚቃ ያሳደግነው ፣ ያልፈለግሁትን ጫማ ገዛችሁልኝ ብሎ ራሱን የሚያጠፋ፣ ለወላጆቹ ፍቅር የሌለው፣ መብልና ኢንተርኔት እንዳይቋረጥ ብቻ ቤተሰቡን የሚፈልግ ፣ ደስታው ጣዖት የሆነበት፣ የማያዝን ፣ ወላጆቹ ላይ ፖሊስ የሚጠራ ፣ ሰላም ለማለት የሚሰለች፣ ከስልኩ ጋር እንጂ ከማንም ጋር ማውራት የማይፈልግ፣ ዘመናዊው ዓለም ያበጀው የሚተነፍስ ሮቦት ነው ። ራስን ሲጥሉ ልጅም አይወድምና ብዙ ራስን መጣል ተገቢ አይደለም። ልጁን የሚወድ ወላጅ ራሱን መጠበቅ አለበት። ሞኞቹ ወላጆች ከልክ በላይ ተሸክመው ልጅ ደርሶ ሊጦራቸው ሲል በሕይወት አልተገኙም። ወላጅም ልጅም የነበረው በቀደመው ትውልድ ነው ብንል አልተሳሳትንም :: አብሮ የተቸገረና ያለቀስ ነውና በቀላሉ የሚለያይ አልነበረም። የአሁኑ ትውልድ ግን ሕይወትን በመስተዋት ውስጥ ሆኖ የሚያይ ፣ ወላጆቹ የሚያጥኑለት ጣዖት  ነው።

ወላጆቻችን በኑሮ ኮሌጅ ፣ በሕይወት ዩንቨርስቲ የተማሩት ነገር ዓይን ዓይኑን ያዩት ነገር እንደማይበረክት ነው:: ስለዚህ ልጆቻቸውን በጣም አያዩም ነበር። ይህ በጥላቻ ሳይሆን በጣም በመውደዳቸው በስስት ነው:: በገጠሩ ወንድ እየሞተ ሲያስቸግራቸው ቀሚስ አልብሰው ፣ በሴት አንቀጽ እየጠሩ ያሳድጉታል፣ ስሙን አክፋፍተው ጥጆ ፣ ውሾ እያሉ ይጠሩታል። ልጅን ለማሳደግ ዋናው ነገር በጀት ሳይሆን ሃይማኖት ነው::  ዛሬ ዓይን ዓይናቸውን የምናያቸው፣ ዶክተር መሆን አለብህ፣ ሳይንቲስት መሆን አለብሽ፣ እገሌን መተካት አለባችሁ ብለን ስናሳድጋቸው ራሳቸውን መሆን አቅቷቸው ከመስመር ወጥተዋል፣ የወላጄን ምኞት አላሳካውም ብለው በአጉል ጸጸት በሽተኛ ሆነዋል :: ዘመድ እንዳያውቁ፣ ከእኛ ተለይተው መታጠቢያ ቤት እንኳ እንዳይሄዱ ያደረግናቸው ልጆች ዓላማችን የእኛ ቁስ ዕቃ እንዲሆኑ ነበር ፣ አልፈን አባታቸውን እንዲጠሉ፣ የእናታቸውን ክፉነት እየነገርን ያሳደግናቸው ለግል ፓርቲአችን ደጋፊ እንዲሆኑ ነበር ። ልጆቹ እምቢ ብለው እግዚአብሔር የሰጣቸውን ነጻነት ሲያውጁ ልፋቴ   ገደል ገባ ብለን ተስፋ እንቆርጣለን።

ልጆቻችን ተፈጥሮአቸውን፣ ተሰጦአቸውን እንዲሆኑ መፍቀድ አለብን። ኬጂ ተመረቁ ብለን አምስት ኮከብ ሆቴል ላይ  የምንደግሰው ታማሚ ስለሆንን ፣ የከረመ ስቃይ ስላለብን ነው:: ልጆቹ ግን ዕድሜ እንዳያገኙ ሀብታችን እንቅፋት ሆነባቸው::  ድሮ ዘመቻ ወጣቱን ፈጀ፣ ዛሬ አጉል ሀብት ወጣቱን ጨረሰ። ይህ ሁሉን የሚወክል ንግግር ላይሆን ይችላል።  የድሮ ወላጆችን መውቀስና የእኔ አስተዳደግ ልዩ ነው ባይ ስለበዛ ውጤቱን ለማሳየት ነው።

ሰው እንዴት ሚስቱን እንደሚወድ በቴሌቪዥን ይናገራል? እቤት ለራሷ አይነግራትም ወይ? ፍቅር ማስታወቂያ ከተሠራበት ዕድሜው አጭር ነው። መፍራት ያለብን ፍቅራችን መነጋገሪያ ርእስ ሲሆን ነው። በጣም እንዋደዳለን እያሉ በአደባባይ የሚያወሩ አብዛኛዎቹ ለመለያየት ሰው ፈርተው የተቀመጡ፣ በሕይወታቸው ድራማ የሚሠሩ ናቸው።

እገሌን እወደዋለሁ እያልን ስናወራ ሰዎች ያንን ሰው በቅናት መመልከት ይጀምራሉ። እገሌን እወደዋለሁ ብለን ስናወራ ለእነርሱ የሚሰማቸው ድምፅ እናንተን እጠላችኋለሁ የሚል ነው። ስለዚህ እገሌን ከእኛ ለመለየት መሥራት ይጀምራሉ ። እገሌን ከእኛ  በላይ በመውደድ የተውኔት ተግባር ይጀምራሉ:: አንተን አንቺን  ስለሚሰማ፣ ስለሚወዳችሁ፣ ስለምትወዳችሁ እንዲህ ብላችሁ ምከሩ በማለት ወደ እኛ መላክ ይጀምራሉ፣ እናንተን ቢወዳችሁም ይህ ጥፋት እኮ አለበት በማለት ያሳምኑአቸዋል ። እኛም ያ የምንወደው ሰው በዓይን እያየን እንዴት በጆሮው ለካን? በሚል ማዘን እንጀምራለን። ፍቅራችን ነፋስ ይገባዋል። እነዚያ ቀናተኞች ያንን ሰው ከእኛ ከለዩት በኋላ ዳግም አይፈልጉትም፣ በጀታቸውም ይታጠፋል። ከወዳጆች የሚለዩን አጠገባችን ያሉ ያላወቅናቸው ቀናተኞች ናቸው። አጠገባችን ያሉት እገሌን እወዳለሁ ስንል ተቀናቃኝ የመጣባቸው ይመስላቸዋል::  ስለዚያ ሰው ክፉ ወሬ በማውራት ልባችንን ያሻክሩታል፤  የሰማነው ክፉ ወሬ ስላለ የዚያ ሰው ትንሽ ጉድለት ሲመጣ ደምረን እንጠላዋለን።

ጌታችን ምጽዋትን በድብቅ እንድናደርግ ያዘዘን የሰጠነው ሲያመሰግነን ያልሰጠነው ጠላት እንዳይሆነን ብሎ ነው። ራሱ ጌታን በሽተኞችን ፈውሶ ለማንም እንዳይናገሩ ያዝዛቸው የነበረው ያለ ጊዜው ላለመሞት፣ ጠላትን ላለማነቃቃት ነው። ፍቅራችንን ለባለቤቱ መንገር በቂ ነው። ደግሞም ፍቅር ተግባር እንጂ ቃል አይደለም።

በአደባባይ የተመሰጋገኑ ፣ ወርቅ የተሸላለሙ፣ ከእገሌ በፊት ያድርገኝ ያሉ፣ እንደ ጴጥሮስ ራሳቸውን ብቸኛ ወዳጅ ያደረጉ ዛሬ ተጠፋፍተዋል። ፎክረው የካዱ ጴጥሮሶች አሉ። እገሌን ፍራ እንጂ እኔማ አልከዳህም ያሉ ኃይላቸውን ፉከራ ወስዶባቸዋል።

አቤቱ ብልሃቱ አልገባንምና  አግዘን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 25 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ