መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -13

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -13

ፍጹምነትን አትፈልግ

ሁልጊዜ ላለመደስት ቆርጠው የተነሡ ፍጹምነትን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። ፍጹምነትን የሚፈልግ ከራሱና ከሰዎች ጋር የማያቋረጥ ጠብ ውስጥ ይገባል :: ዓለም ጎዶሎ ነው፣ የሰው ሩጫ ሊሞላው አይችልም። ሰውም የብረትና የሸክላ ውህድ ነው ። ደካማ እንዳንለው ብርቱ፣ ብርቱ እንዳንለው ደካማ ነው። ሰው ያልቻለውና የማይችለው ጉድ የለምና ብርቱ ነው። የተሸከማቸው በሽታዎች፣ አሳቦች ፣ ችግሮች፣ ግፈኛ ነገሥታት እልፍ ናቸው። ሰው  ደካማ ነው፣ ብዙ አልፎ በትንሹ ነገር  ይፈራል። በዓይን የማይታዩ በሽታዎች ለሞት ያበቁታል። አራዊት በጉልበት፣ ዔሊ በዕድሜ ፣ ሚዳቋ በሩጫ ትበልጠዋለች፣ ግን የምድሪቱ ትልቅ ፍጡር ሰው ነው:: ፍጹምነትን መፈለግ ራስን አለማወቅ ነው። ዓለምንና የሰዎችን አቅም አለመረዳት ነው። የአእምሮ ሕመም ሁሉም የስሜት ሕዋሳቶቻችን ከመጠን በላይ መንቃታቸው ነው። ፍጹምነትን ፈላጊ በጣም ያያል፣ በጣም ይሰማል። በሁለት ዓይን እያዩ ከሰው ጋር መኖር አይቻልም፣ አንዱ ሲያይ ሌላው መጨፈን አለበት። በሁለት ጆሮ እየሰሙ ከሰው ጋር መኖር  አይቻልም፣ በአንዱ ሲሰሙ በሌላው ማፍሰስ ይገባል። ምንድነው  ወጡ? ምንድነው እዚህ ቤት የሚሸተኝ ? የሚል ወንድ ብዙም ትዳሩ አይበረክትም ወይም ሰላም አያገኝም። ምግብ ማብሰሉን በቀላሉ ተምሮ መጀመር፣ በሳምንት አንድ ቀን ጊዜ ሰጥቶ ቤቱን ማጽዳትና ማስተካከል ይገባል። በንግግር፣ በፀብና በንዴት ራስን ከማጣት አንዳንድ ተግባሮችን በራስ መከወን ይገባል። ደግሞስ ቤቱ የጋራ አይደለም ወይ? የባልን የተቀባውን ሽቶ መፈተሸ፣ ስልኩን መበርበር፣ መከታተል የጤና መታወክ የሚያመጣ ነው:: በጥቃቅን ነገሮች ጠብ መፍጠር በረከትን ያርቃል፣  ልጆችን ለአእምሮ ሕመም ይዳርጋል::  ቤቱ እንዲያስጠላን ያደርጋል። ካላለፍን አያልፍልንም።

ፍጹምነትን መፈለግ የማይበርድ ጠብ መጋበዝ ነው። ምክንያቱም ፍጹም ነገር ስለማይገኝ ሁልጊዜ ብስጩ መሆንን ይወልዳል:: የትኛውም ጥሩ ሰው የራሱ የሆነ ጉድለት አለው። አንተ ያንን ሰው የቀረብከው የሌለህን ነገር በእርሱ ላይ ስላገኘህ ነው። እርሱም አንተን ወዶ ፈቅዶ የቀረበህ አንተ የምትሞላለት ጎዶሎ እንዳለው አውቆ ነው። ጉድለታችን የሚያገፋፋን ሳይሆን የሚያፈላልገን ነው። ዐረብ አገራት መልክአ ምድራቸው በረሃ የፀነነበት ነው:: ነዳጅና ወርቅ ግን ዓለም ሁሉ እንዲፈልጋቸው ያደረገ ነው ። አውሮፓ ሰፊ መሬት፣ ነዳጅ የለም። እውቀት ፣ የአእምሮ ሀብት ግን አላቸው። ዐረቦች ኪነ ሕንፃውን፣ ሲስተሙን ለመዘርጋት፣ ቴክኖሎጂን ለማግኘት አውሮፓውያኑን ይፈልጋሉ። የማይሰጥና የማይቀበል በዓለም ላይ የለም። እኔ ያለ ወንድሜ፣ ወንድሜ ያለ እኔ ሙሉ አይደለም። የማያስፈልገው ሙሉ፣ የማይፈለግ ባዶ የለም። አለማወቅ ሆኖ እንጂ ሁሉም ሰው አስፈላጊያችን ነው። አረም ፣ አረም አይደለም። አረም ያላወቅነው መድኃኒት ነው። ጥቅም አልባ የሆነ አንድም ፍጥረት የለም። ይህንን ስንረዳ ለምርምር እንነሣለን። ሰዎችንም እንፈልጋለን። የተናቁ፣ የተወነጀሉ ሊሆኑ ይችላሉ፣ የታሰሩ፣ የተፈረደባቸው ቢሆኑ እንኳ የራሳቸው መልካም ነገር አላቸው።

የፍጹምነት ጥማታችን እንዳንረካ ያደርገናል። ቤታችን እንከን የለሽ፣ ዕቃዎቻችን ድርድር ጥርስ እንዲመስሉ እንፈልጋለን። ይህ መልካምና ቤታችንን እንድንወደው የሚያደርገን ነው:: ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ቤታቸው ነውና የትዳር አጋርና ልጆች እንዲዝረከረኩ መፍቀድ አለብን። ቤቱ የዜና ማወጃ ስቱዲዮ አይደለምና በጣም መጨነቅ የለብንም። ቤት ቤት ሲመስል እንጂ በቢሮ ልክ ከሆነ ይሰለቸናል፤ ለማረፍም አያስችለንም። ራሳችንንም በቤታችን ውስጥ ነጻነት ማሳጣት እንጀምራለን። ፍጹም ማለት ሙሉ አይደለም ፣ ልክ የሚባለውን ያህልም አይደለም። ፍጹም እንከን የለሽ፣ በእግዚአብሔር ከፍታ ያለ ማለት ነው። ልጆች እንደ እውቀታቸው መጠን፣ እንስሳትም በመጠናቸው መታየት አለባቸው:: አንዳንዴ ከሰው የሚጠበቀውን ከእንስሳት እየጠበቅን ሲያጠፉ መቅጫ አለንጋ እንመዛለን። እንስሳትን በአእምሮ ካልበለጥን ማስተዳደር አንችልም።
አለባበሳችን ምንም እንከን የሌለበት እንዲሆን እንጨነቃለን። ብዙ ልብሶች ጊዜያችንን ያባክናሉ፣ የቱን ልልበስ ስንል ሰዓቱ ይሄዳልና። በታወቁ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ የሚሠሩ ኃላፊዎች አንድ ዓይነት ልብስ ስድስት ሰባት ይገዛሉ። የሚያስቡት ስለ ንጽሕናው እንጂ ስለ ዓይነቱ አይደለም። በጣም ሽቅርቅር ስንሆን ሰዎች እንከን እየፈለጉብን ይመጣሉ:: ለውበት ማሰብ መልካም ነው። ራስን ሲያዩ መዋል ግን ጣዖት ማምለክ ነው።

መለስ ቀለስ ብላ አየችው ቀሚሷን ፣
ረሳችውና ከአፈር መለወሷን ::

ልጆች እንዲሳሳቱ ካልፈቀድን አፍ አይፈቱም። ቋንቋ የሚያስተምሩ ተማሪዎቹ እንዲያስተካክሉ ሳይሆን እንዲያበላሹ መምከር አለባቸው። ቋንቋው ይሰበር፣ የእናቱ ማድጋ  አይደል። ሠራተኞች ሥራ የሚለምዱትና የሚሠሩት በማበላሽት ነው። ከዚያ በኋላ ጎበዝ እየሆኑ ይመጣሉ:: ንግድ መነሻው ኪሣራ አለው:: የኪሣራ በጀት መያዝ ተገቢ ነው። ስብከት የሚጀምር ሰው ንግግሩ የተቆራረጠ ነው። ቍጣ ሊያበዛ ይችላል፡ ቀስ እያለ ግን ርቱዕ እየሆነ ይመጣል። መኪና የሚነዳው ሲጀምር ፈሪ ነው። አንዳንዱ ፍርሃቱ የሚለቀው በጥቂቱ የተጋጨ ቀን ነው። እኛም ስንጀምር ፈርተናልና የሌሎችን ፍርሃት ማገዝ አለብን። ሰው ለምን ፈራህ? አይባልም ፣ ከፍርሃት የሚወጣበትን መንገድ ማመልከት ግን የቅኖች ወግ ነው ።

ሁለተኛ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የሚናገሩትን ባለ መረዳት ልንቀየም እንችላለን። እያንዳንዱን ቃል ማዳመጥ አይገባም። ሰዎች ከእኛ ጋ ሲያወሩ የቋንቋ ፈተና እየተፈተኑ አይደለምና ጥርት ያለ ቋንቋ ባይናገሩ አሳባቸውን መረዳት አለብን። ቃላትን በሚመለከት በጣም ስስ  የሆነ ማኅበረሰብ ላይ ነን። በቃላት ምክንያት ሰዎች ይጋደላሉ። በልኩ አንጣላም። ፍጹምነትን የሚፈልግ ኣገር አያድግም:: የአገራችን ሕዝብ ትልቅ ችግሩ ፍጹምነትን መፈለግ ነው። ተቺ፣ ነቃፊ፣ ተሳዳቢ የሚበዛው በዚህ የፍጹምነት ፈተና ነው። ሰዉ የሚደነቀው ሥራው  ሳይሆን ሙከራው ነው።

ፍጹምነትን መፈለግ እንኳን ከሰው ከራስም መለየትን ያመጣል። ደግሞም ግብዝነት ነው። ለራሳችን ጥፋት እየሳቅን የሰዎችን ጉድለት ስናወራ መኖር የለብንም። አንድ ዕቃ ሰንሰብር “እንኳን እኔ አልሆንኩ” ብለው ሰዎች ይደሰቱብናል። የፍጹምነት ጠባያችን ሰዎች ሰህተታችንን እንዲጠባበቁ ያደርጋል። አንዲት እናት ብዙ ወንዶች ወልዳ ዕቃውን ሲሰብሩት “ተዉ አድጋችሁ እናንተዉ ናችሁ የምትገዙት ትላቸው ነበር። ታዲያ ልጆቹ  አድገው እናታቸውን አንቀባረው የሚያኖሩ ሆኑ። ዛሬ ያበላሹ፣ አጥፍተው ይቅር ያልናቸው ነገ ላይ የሚጠቅሙን እነርሱ ናቸው። ጌታ የሾመው ያልበደለውን ዮሐንስ ወንጌላዊን ሳይሁን የበደለውን ጴጥሮስን ነው፡ ፡

የሚጎዳን ከሰዎቹ በደል በላይ የእኛ መጠበቅ ነው። አንዳንዴ ቅድመ ሁኔታ እናስቀምጣለን። መፈተኛ ማስቀመጥ ሰይጣንነት ነው። ሁሉም ነገር የራሱ ችግር አለው፣ ማግኘትም ማጣትም ችግር አለው፡ ፡ ከጉድለት ነጻ የሆነ ነገር መጠበቅ አይገባም።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ