መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -3

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -3

ወቃሽ አትሁን

ወዳጅ ይወቅሳል፣  ጠላት ይከስሳል። ሁልጊዜ መውቀስ ግን መራራቅን  ያመጣል። ሰዎች ከምናደርግላቸው ነገር በላይ ያሉበትን ሁኔታ እንድናውቅላቸውና እንድናዝንላቸው ይፈልጋሉ። መድኃኒት ቢሆንም በጭካኔ መርፌ የሚወጋቸውን ሐኪም አይፈልጉም። ሰዎች ስላሉበት የሕይወት ስብራት አስቀድመን ማጥናት ያስፈልጋል። አሁን የሚያሳዩት ጠባይ ከአስተዳደግ ችግር ፣ ከኑሮ ውጣ ውረድ ፣ ከእውቀት ማነስ፣ ከበሽታ የመጣ ነው ወይ ? ብሎ መመርመር ይገባል። ሁለት መኪና የያዙ ሹፌሮች ሲሰዳደቡ ብናይ የማይተዋወቁ ናቸው ፣ ያገናኛቸውም መንገድ ብቻ ነው፣ ቆይታቸውም ቅጽበታዊ ነው። ይህ ስድብ ሊሰድቡት የሚፈልጉት የሚያውቁት ሰው አለ፣ እርሱን ቢሰድቡ ዋጋ ይከፍላሉ፤ ስለዚህ ታምቆ  የኖረውን ስድብ የማያውቁትና ዋጋ የማያስከፍላቸው ፣ ነገም የማይወቅሳቸው ሰው ላይ ይለቁታል። የሰዎችን ብስጭትና ቍጣ መረዳት ያስፈልጋል። ምክንያቱም እያሸነፉ  ሳይሆን እየተሸነፉ መሆኑን አመልካች ነው። ብስጭታቸውም ተዉኝ የሚል ግልግል እንጂ ድል ለማድረግ ማሰብ አይደለም። ሰዎችን ከመርዳት በፊት መረዳት አለብን፣ ያ ባለ ድል ያደርገናል:: አሸንፈን ብንገባ ወንድማችንን ግን ብናጣ ተሸንፈናል፣ ተሸንፈን ወንድማችንን ማትረፍ ግን ይበልጣል። ፍቅር ከድል በላይ ነው:: የተሰበረ አጥንትን፣ የወለቀ ጉልበትን በጥበብ እንጂ በኃይል መመለስ አይቻልም።

አንድን ምክር ከሰጠን በኋላ ጊዜ መስጠት ያስፈልጋል። የእኛ ምክር ብቻውን ይለውጣቸዋል ብለን ማሰብ የለብንም። የሰው ቍ ጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራም ተብሎ ተጽፎአልና (ያዕ.1፥ 20) ።  እኛ ስለ ተቆጣን ክፉውን ጥለው ደጉን አይዙም። ኃይለ መንፈስ ቅዱስ ያስፈልጋቸዋል። ችግሩን በችግርነቱ ለመረዳት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል:: ወቀሳዎቻችን ለራሳቸው ያላቸውን ግምት እንዲጥሉና እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ መሆን የለበትም። ለራሱ ያለው ግምት የወደቀበት ሰው የመኖር ፍላጎት የለውም። የተሸማቀቀ ሰውም አደባባይ ለመውጣት ጉልበት ያንስዋል ፣ በሱስ ውስጥም ይደበቃል ። ከጥፋቱ በላይ የእኛ ተስፋ የለሽ ወቀሳ የበለጠ ጉዳት ውስጥ ሊከተው ይችላልና መጠንቀቅ አለብን ። ቃላት ከዱላ በላይ የመጉዳት አቅም አላቸው።

አንዳንድ ምክሮች ውስጣቸው መርዛማ ይሆንና የመጉዳት አቅም አላቸው። “በርትተህ ተማር” ማለት መልካም ምክር ነው። ቀጥሎ ግን:-  “የድህ ልጅ መሆንህን አትርሳ” የሚለው ምክር ግን ያን ሰው ከመስመር የሚያወጣ ነው። ከምክሮቻችን በፊት ራሳችንን ማረጋጋት ያስፈልጋል። እሳትን በእሳት ማጥፋት አይቻልምና። ከምክር በኋላ ዝምታ ጥሩ ነው። የጠለለ ውኃ ፊትን እንደሚያሳይ ዝምታችንም ሰዎች ራሳቸውን እንዲያዩ ያደርጋቸዋል።

እነዚህ ሰዎች ለመነሣት አንድ ጉልበት አላቸው፤ እርሱም በእነርሱ ላይ ያለን ተስፋ ነው።   አንተ እኮ መድረሻህ መልካም ነው፤ አንቺ እኮ ቡሩክ አእምሮ ተቀብለሻል ስንላቸው ያንሰራራሉ ። ከመጠን በላይ ተስፋ መጣልና እዚህ መድረስ አለባችሁ የሚለው ምክርም ሊጉዳቸው ይችላል። እነርሱ የሚሆኑት ራሳቸውን ነው:: እኛ ያላሳካነውን ድል በልጆቻችን ለማሳካት መሞከር ትውልድን ገዳይ ሊሆን ይችላል። እገሌን መሆን፣ እገሌን መተካት አለብህ ስንላቸው ፈጽሞ መዳከም ይጀምራሉ:: ስለ እገሌ ታሪክ ሰሙ እንጂ የእገሌን ውስጡን አያውቁትም። እነዚህ ልጆች ለቤተሰባቸው ሲሉ መማርና መኖር እየሰለቻቸው ይመጣል። ለከፍተኛ የጭንቀት ሕመምም ይጋለጣሉ። ሰዎችን አርአያ ማድረግ እንጂ ሙሉ በሙሉ እነርሱን ካልሆንኩ ማለት ተፈጥሮአችንን ማባከን ነው ። እውቀትም አያድግም። የአገራችን እውቀት ባለበት የሚኖረው መምህሩ የራሱን ሰጥቶ ያንተን ጨምርበት ስለማይል ነው።

አድናቆታችንም በተግባራቸው ላይ እንጂ በመልክና በቁመናቸው ላይ ባይሆን መልካም ነው። ሳጥናኤልን ለመውደቅ ያበቃው የውበት ትምክሕት ነው:: በምድር ላይ መልከ ቀናዎች ምግባረ ቀና የማይሆኑት ትምክሕት ስላለባቸው ነው። ደግሞም እግዚአብሔር ቁመተ መለሎ ፣ መልከ ፀሐይ፣ ጥርሰ በረዶ ፣ ዓይነ ጨረቃ የሆነውን ኤልያብን ትቶ ዳዊትን መርጧል። አቤሴሎም የፀጉሩ ውበት ልዩ ነበር፣ አባቱን በማዋረዱ አጉል ሞት ሞቷል:: ሰዎችን ላለፉበት መልክና ቁመና ሳይሆን ለለፉበት ትምህርትና አገልግሎት ማድነቅ የተሻለ ነው።

ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት በሁሉም ነገር ወቀሳ ማብዛት ወዳጅነትን ይጎዳል። አንዳንዱ ጠባያቸው ራሳቸው እንኳ የማይፈልጉት ነው፣ ሌላው ጠባያቸው ጎጂነቱ እስካሁን ያልታያቸው ነው። በዘዴ እየመከርን፣ በጸሎት እያገዝን ፣ አብረን እየከወን ይህን ሕንፃ ሥላሴ መፈጸም አለብን። የዚህ ዋጋ ከሰማይ ነው:: ብልህ ካህን ጾም ጸሎት ለልጅ ሲያዝዝ አብሮ ይጾማል ፣ ምእመኑም ለእኔ ችግር እርሳቸው ከጾሙ እኔማ መለወጥ አለብኝ ብሎ ይነሣሣል ።

መድኃኒትን በብሩህ ፊት የሚወስድ የለም፣ እያባበሉ ግን ይሰጡታል። ይልቁንም ሰው ሲያመው ምግብ ያስጠላዋል፤ ምክርና ቃለ እግዚአብሔር ካስጠላው ታሟልና በትንሽ በትንሹ አጣፍጠን መስጠት ይገባናል:: በሽተኛው ምግብ እምቢ ሲለው ጥለውት አይሄዱም።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ