ይቅር በላቸው
ሰዎች ባያስቀይሙህ ኖሮ የዛሬው ደረጃ ላይ አትደርስም ነበር። በደርግ ዘመን ክፉኛ ጨፍጫፊ የተባለ ሰው ነበር። ይህ ሰው የሚያደርገውን ግፍ ሸሽተው ብዙዎች ከአገር ወጥተዋል። አሁን ላይ ዕድሜ ለእርሱ፣ እርሱ ባያሳድደን ኖሮ እዚህ አንደርስም ነበር ሲሉ ይሰማሉ። ይህ ሰው ዐሠርት ዓመታት እስሩን ጨርሶ ሲወጣ መኪናና ቤት ሊገዙለት ሲያስቡ ነበር። የቆየ ጠላት ወዳጅ ይሆናል። እነዚያ ዓመታት እግዚአብሔር ክፉውን ወደ በጎ እንደሚለውጥ ትምህርት ተገኝቶባቸዋል። እግዚአብሔር ከፍ ያለ ቦታ የሚያወጣን በገፊዎች ተጠቅሞ ነው። ታዲያ ከፍታ ላይ ከደረስን ገፊዎችን የሸከማ መክፈል አለብን። ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ከሰው ጎደለብኝ የሚል አላዋቂ ነው። ዓመታት ሲረዝሙ እንኳን ጠላት ገጠመኝ እንላለን። የእናት ፍቅር ያስደስታል እንጂ አያሳድግም። የጠላት ጭካኔ ግን ለኑሮአችን ጨካኝ ሆነን እንድንለወጥ ያደርገናል።
ጣሊያን ከወጣ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለዳግም ወረራ የዳረገን ነገር ምንድነው? ብሎ ሲመክር ያገኘው የወቅቱ መልስ “የተማረ ኃይል አለመኖሩ ነው” የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች ተቋቋሙ። ጣሊያን በአየር ላይ ውጊያ ስለመጣ አየር ኃይሉ ተጠናከረ። የጣሊያን መምጣት ትምህርት እንዲስፋፋ ፣ ዘመናዊ የጦር ኃይል እንዲጠናከር ምክንያት ሆነ ። ዘወትር የምንጸልየው ጸሎተ ሃይማኖት ድንቅ የሃይማኖት መግለጫ ነው:: አርዮስ ባይነሣ 318 የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አይሰበሰቡም ነበር፤ ይህን ጸሎትም አናገኘውም ነበር። ጠላት ያሳድጋል ፣ ራስን ያስችላል እንጂ አይጎዳም። ያስቀየሙን ሰዎች ክፍተታችንን እንድናይ፣ ምኑ ጋ ነው የተሳሳትኩት ? እንድንል አድርገውናል። እነርሱ ቢሄዱ እንኳ ከቀጣዩ ወዳጅ ጋር በማስተዋል እንድንጓዝ አድርገውናል:: ትምህርት በነጻ አይገኝምና አስተምረውናል። እንዴት ሰው መምህሩን ይቀየማል? እነዚያ ክፉ አከራዮች ይህ ሁሉ ሰው ቤት እንዲሠራ አድርገዋል። በፋሲካ የገባች ሠራተኛ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል እንዲሉ ተከራይም ሲደላደል ቤቱ እየመሰለው ይኖራል፤ እግዚአብሔር ምንጣፉን አንሥቶ እሾህ እንዲወጋው በማድረግ ያነቃዋል። ምቾት ማጣት ከቤት እንድንወጣ ፣ ራሳችንን እንድንችል ያደርጋል። አሊያ የደለበ ባሪያ ሆነን፣ በሆድ ደመወዝ የምንኖር ምስኪን ሰዎች ተብለን እንቀራለን። ታላላቅ ፈጠራዎችን ያስገኙ ሰዎች ከትምህርት ቤት የተባረሩ ናቸው። በዚህ ምክንያት ለዓለም ትልቅ አስተዋጽዖ አደረጉ። ያበረሩን ባለ ውለታዎች ናቸው።
ቶማስ ኤዲሰን ከትምህርት ቤቱ የተሰጠውን ወረቀት ለእናቱ አደረሰ። እናቱም ስታነበው እንባዋ ታገላት። ልጁም አፍጥጦ ሲያያት። “ይህ ደብዳቤ የሚለው ልጅሽ የምጡቅ አእምሮ ባለቤት ነውና የእኛ ትምህርት ቤት ሊያስተምረው አይችልም። በቤትሸ አስተምረው” የሚል ነው አለችው ። እርስዋም የተባረረውን ልጅ በቤት ውስጥ አስተማረችው ። ይህ ልጅ የኤሌክትሪክ መብራትን ለዓለም አበረከተ። ዛሬ በድሀና በባለጠጋ ቤት የሚገኘው አምፑል የቶማስ ኤዲሰን ፈጠራ ነው። ዓለምንም ከጨለማ ወደ ብርሃን አሸጋገረ። ቶማስ ኤዲሰን መገፋቱ ለትልቅ ስኬት አበቃው:: መጽሐፍ ጠላትህን ውደድ የሚለው ጠላት አሳዳጊ ስለሆነ ነው።
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ይቅር ማለት የሕይወት ዘይቤአችን ሊሆን ይገባዋል። ያለ ድልድይ መንገድ እንደማይታሰብ ሁሉ ያለ ይቅርታ ግንኙነት አይታሰብም። ይቅርታ የትላንትን ስህተት መካስ ፣ ሰዎች እንዲለወጡ ዕድል መስጠት ነው። ይቅር እንዲባልልን የምንፈልገው ጉድለት ስላለን እኛም ሌሎችን ይቅር ማለት አለብን። ሙት ነክሶ የሚቆይ ቀጥሎ ሟች ነው ፣ የበደሉንን ሰዎች ሙት ሥራቸውን ነክሶ መኖር ሁለንተናዊ ውድቀት የሚያመጣ ነው። ለአጭር ዕድሜ መቀየም ከንቱ ነው ። ስንቱንስ ሰው ተቀይመን እንችለዋለን?
ይቀጥላል
ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም.