ድረስላቸው
አገሬ ላይ ቆሜ ናፈቀኝ አገሬ፣
ሰው ከማን ይኖራል ሁሉም ሆኗል አውሬ ፤
ሰው ከሰው ተፈጥሮ ሁሉም ከሆነ አውሬ ፣
እንዳሻኝ ልራመድ ወደ መራኝ እግሬ ፤
ምነው ሰዉ ሁሉ አንዱ አንዱን አይመስል ፣
የበሰለው ያርራል ጥሬውን ሲያማስል ።
አንዳንድ ቀኖች እውነተኛ ወዳጅ ተለይቶ የሚታወቅባቸው የፈተና ቀኖች ናቸው ። በዚያ ቀን ላይ አንሶ መገኘት ትልቅ ውርደት ነው። ደስታ ብዙ አጃቢ ሲያገኝ መከራ ግን ብቸኛ ያደርጋል። ሰው በመከራ ውስጥ ሲሆን ፍሙ እርሱን ሲበላው ወላፈኑ ወዳጆቹን ይነካቸዋል። ከመርዳትና ከመረዳት መፍረድ ይቀናቸዋል:: የሚፈርዱበት ምክንያት በሰበብ ለመራቅ መፈለጋቸው ነው። ሰዎች የቆመ እንጂ የተንገዳገደና የወደቀን ሰው አይፈልጉም። የወዳጅነት ልኩ ሲንገዳገዱ መደገፍ ሲወድቁ ማንሣት ነው። ከሥራ የመባረሩን ዜና ሲሰሙ እርዳኝ የሚላቸው ይመስላቸውና ይሸሹታል። ትዳሩ ሲፈርስ እቤትህ ልመጣ ነው የሚላቸው እየመሰላቸው ወገን ይይዛሉ ። ቀድሞ ሳይመክሩት አሁን ኃጢአቱን እያበዙ ፣ ፍርድ እየቆረጡ ይናገራሉ። ሁልጊዜ ለሰዎች በክፉ ቀናቸው ላይ እንዳንከፋባቸው እርዳኝ ብለን መጸለይ ይገባናል ።
አስቸጋሪ ቀን ባለቤቱ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ፍቅር ይፈተንበታል። ያ የመከራ ቀን የክርስቶስ የመከራ ቀን ነው ። ስደታችን ስደቱ ነውና። በዚያ ቀን እግዚኣብሔር ከእኔ ጋር ይቆማል ወይ ? ብሎ ያየዋል። አስቸጋሪ ቀኖች ወዳጆች እውነተኛ ፍቅራቸው የሚለካበት ነዉ። ለዚያ ቀኑ ዓርብ ስቅለት ለሆነበት ሰው አለሁ ስንል የዓርቡን መከረኛ የክርስቶስን መስቀል እንዳገዝን ይቆጠርልናል። ትግል ውስጥ የሚያልፍ ሰው ጋ ስንሄድ የምናገኘው ሰውን ሳይሆን ባለ መስቀሉን ኢየሱስን ነው:: በመጨረሻው ቀን ዓለም አቀፍና ዘመን አቀፍ ፈተና ይታረማል። እነዚህም ስድስቱ ቃላተ ወንጌል የሆኑት ናቸው። ብራብ አብልታችሁኛል ፣ ብጠማ አጠጥታችሁኛል — የሚሉት ናቸው፡ ፡ አዎ ክርስቶስ በክብር ዙፋኑ ነው ፣ ክርስቶስ ግን እርቦት በበራችን ላይ ቆሞ እየለመነ ነው:: እነሆ በበር ቆሜ እንኳኳለሁ የሚለውን በአካል ወርዶ የሚመጣ መስሎን ከሆነ ተሳስተናል። ሥጋ ማርያምን ለብሶ እንደ መጣ በድሆች ላይ አድሮ ይመጣል። ስንት ቀን መጥቶ ስንት ቀን መልሰነው ይሆን? ክርስቶስ አብረቅራቂ ልብስ ከለበሱት ሳይሆን የወየበ ልብስ ከለበሱት ጋር ነው። ክርስቶስን ምነው ባገኘሁት ብለን የግብዝ ጥያቄ ማንሣት የለብንም። ክርስቶስ ርቦት፣ ጠምቶት፣ እንግዳ ሆኖ፣ ታሞ ፣ ታስሮ አለ። አሁን ወጥተን ማግኘት እንችላለን። ሃይማኖትን ውስብስብ ማድረግ የአስመሳዮች ጠባይ ነው። የማይፈታ ቅኔ አድርጎ ማቅረብ፣ የምዕራብና የምሥራቅ ቲዎሎጂ እያሉ የቃላት ብሎን ሲያጠብቁ መዋል ከእውነቱ ለመሸሸ ማሴር ነው። ሃይማኖት እግዚአብሔር አለ ብሎ ማመን፣ ለሰዎች ዋጋ መክፈል ነው።
ሰዎች የእኛን እርዳታ በሚፈልጉበት ቀን መዘግየት አይገባም። ችግሩ ባይፈታ እንኳ ፈጥንን መገኘታችን፣ አብረን ማልቀሳችን፣ መፍትሔ ማፈላለጋችን ልባቸውን ያበረታዋል። አለኝታ ማግኘት፣ ብቻዬን አይደለሁም የሚል ኩራት የመሻገር አቅም ይሆናቸዋል። ወዳጅነት ለመቼ ነው? አንድ ጎበዝ ሐኪም ነው፣ የሚገኘው በወረፋ ነው፡ ፡ ታዲያ አሜሪካን አገር ላልተወሰነ ጊዜ እንደሚሄድ ነገረኝ። እርሱ ከሄደ ክሊኒኩ ይጎዳል። የሰጠኝ መልስ:— “ጓደኛዬ ታሟል ፣ ሕ መሙ ብርቱ ነው። ስለዚህ ይህን ጊዜ ከእርሱ ጋር ካላሳለፍኩ ማረፍ አልችልም። እዚህ ካለኝ ትርፍ በላይ ነው፣ እርሱ ለእኔ ብዙ ዋጋ ከፍሏል” አለኝ። ለብዙ ወራት ሥራውን፣ ትዳሩን ትቶ አስታሞ፣ ቀብሮ ፣ ቀጣዩን ነገር አስተካክሎ መጣ። ደስተኛነቱ ግን እየቀነሰ፣ በጓደኛው ሞት እየተጎዳ አይቻለሁ።
ስንጠራቸው ቶሎ አቤት የሚሉልን እነማን ናቸው? እነርሱ የእኛ መላእክት ናቸው። ድምፃችን አቅሙ ሲወርድ የሚደነግጡልን እነማን ናቸው? ታመምን ሲባል ዕለቱን የሚመጡ ፣ ያላቸውን ነገር ጥለው የሚደርሱልን፣ እንደ አንደኛ ሰዋቸው የሚያዩን እነማን ናቸው? እኛም ለእነርሱ መኖር አለብን። “ለገቢህ ተንገብገብ” ይባላል። ገቢህ ማለት ዘው ብሎ ለሚገባልህ፣ ስትጮህ ለሚደርስልህ ከአንጀትህ አስብ፣ ከውስጥህ አልቀስ ማለት ነው።
የዮናታንና የዳዊት ወዳጅነት ከሥጋ ቋጠሮ በላይ ነው። ዮናታን ከአባቱ ጋር ሳያድም ዳዊትን ከሳኦል ሰይፍ ለማዳን ይተጋ ነበር። ንግሥናን ለወዳጁ ለቀቀ። ጥሩ ሰው አይበረክትምና ዮናታን ሞተ። ዳዊት ግን ለቤተሰቡ ውለታ መለሰ። ደግ ሰው እንዳማይቆይ አውቆት ነው ደግ የሚሆነው። ክፉዎች ለዘላለም የሚቆዩ ስለሚመስላቸው ክፉ ይሆናሉ። ወዳጅ አይለወጥም። ዛሬ አስቀየመ ተብሎ አይሸሹትም። የእናትህ ልጅ ስንት ንብረትህን እያወደመ፣ በክፉ ቃላት እየነደፈህ አብረህ ትኖር የለም ወይ? በእግዚአብሔር የተዛመዱት በሥጋ ከተዛመዱት ይበልጣል። ደግሞም አይቡን አይተው አጓቱን ይጠጡታል ይባላል ። የዛሬውን መኮምጠጥ ሳይሆን የትላንቱን ጣፋጭነት ማሰብ ይገባል።
የገንዘብ ጥያቄ ያለበትን ወዳጅ በአቅማችን መደገፍ መልካም ነው:: ማዳመጥ፣ አብሮነት፣ ማጽናናት እነዚህ ሁሉ ከገንዘብ ተመን በላይ ናቸው። ይህ ማለት እነዚህን በገንዘብ ተምነን ሲረበው ሁሉም ያልፋል እያልን እንድናጽናናው አይደለም። ሁሉም ያልፋል የሚለው ማጽናኛ ጊዜ ለሚሰጥ ችግር ነው። ረሀብ ጊዜ አይሰጥም። ሌሎችን መርዳት፣ ለወዳጅ መድረስ መቻል ዕድል ነው። ሰው ሁሉ በአንድ ነገር አንደኛ ቢወጣ ይመኛል። በደግነት አንደኛ መውጣት ፣ በደራሽነት ቀዳሚ መሆን የት ይገኛል? እስከማውቀው ጓደኛ ሲያስታምም፣ ወዳጅ አብሮ መከራ ሲቀበል “እንኳን በዚህ ሰዓት አብሬህ ሆንኩኝ፣ እንኳን ክፍተትህን ሌላ ሰው አላየው” ሲባል ነው። በዓለም ላይ ስምንት ቢለየን ሕዝብ ሳለ አንተ ጋ ድረስ ተብሎ ከተደወለ ከስምንት ቢሊዮን ሕዝብ አንደኛ ወጣህ ማለት ነው። ልጨምርልህ የዓለም መሪ ሆንህ ማለት ነው! ኵራት ኩራት አይልህም ወይ? የመድኃኔ ዓለም ሎሌ አይደለህም ወይ?
እባክህን ለወዳጅህ ድረስለት ! የአገራችን ገጣሚ ሆድ ቢብሰው ፣ ወዳጅ ቢያፈርሰው እንዲህ አለ።
አገሬ ላይ ቆሜ ናፈቀኝ አገሬ፣
ሰው ከማን ይኖራል ሁሉም ሆኗል አውሬ ፤
ሰው ከሰው ተፈጥሮ ሁሉም ከሆነ አውሬ ፣
እንዳሻኝ ልራመድ ወደ መራኝ እግሬ ፤
ምነው ሰዉ ሁሉ አንዱ አንዱን አይመስል ፣
የበሰለው ያርራል ጥሬውን ሲያማስል ።
ከማዕረግ ስሞች የሚበልጥ የክፉ ቀን ወዳጅ የሚለው ነዉ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም