መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -6

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -6

አትቀልድባቸው

ሰዎች በራሳቸው ተፈጥሮ፣ በራሳቸው ስህተትና ገጠመኝ ቢቀልዱ ደስተኛ ይሆናሉ። ሲቀለድባቸው ግን ሊያዝኑ ይችላሉ። የማይረባ ጠባይ ካላቸው እነርሱን አቁመን ለሌሎች ስንነግር በችሎት ፊት መልስ እንዳጣ ተከሳሽ ይሆናሉ:: ምናልባት መክረን ዘክረን እንቢ ብለውን ከሆነ ሁነኛና ከእኛ የተሻሉ ሽማግሌዎችን ጠርቶ ማነጋገር የጉዳዩን ክብደት እንዲረዱት ያደርጋል። መጽሐፋዊ መንገድም ነው። ብስጭታችንን ለመወጣት በዚያ ሰው ጓደኛ ፊት መናገራችን እኛን ቢያስተነፍስም ያን ሰው ግን አይለውጠውም። “ጓደኛህን እስቲ ምከረው” ማለት፣ ያንንም ሰው እነ እገሌን አታይም ወይ? ብሎ መናገር አነሣሽ አይሆንም። እግዚአብሔር ይረዳሃል፣ ብዙ ጥሩ ነገር አለህ በዚያ ላይ ይህን ብታደርግ የበለጠ ሙሉ ሰው ትሆናለህ ብሎ መምከር ይገባል። ከሁሉ በላይ በጸሎት ማሰብ አስፈላጊ ነው። እኛም የሆነውን መልካም ነገር የሆነው ፣ እግዚአብሔር ረድቶን ነው።

ሰዎች ወደ ተወለዱበት አካባቢ መሄድን ብዙ ጊዜ አይፈልጉም። ይልቁንም በግድ የሚያስኬዳቸው የአባትና የእናት መኖር ሲሆን እነርሱ ከሌሉ ጭራሽኑ እንኳን ሊሄዱ ወደዚያም ዞረው አይተኙም። እየበሰሉ ሲመጡ ግን ያደጉበትን ቦታ በማየት መነሻቸውን ያስባሉ፣ ትዝታቸውን፣ የማይመለሰውን ልጅነት ያጣጥማሉ፣ ድሮ የሚያውቃቸውን ሰው ማግኘት ፣ ከፕሮቶኮል ውጭ መጫወት ይፈልጋሉ። ይህ በአእምሮ መብሰል ሲኖር የሚደረግ ነው። በርግጥ ድህነት የሚታገለው ከሆነ ምን እሰጣለሁ? ብሎ ወዳደገበት መመለስን ይፈራል። ሰዎች ወደ ተወለዱበት ስፍራ መሄድ የማይፈልጉት የትላንት አስቂኝ ታሪካቸው እንዳይወራ ስለሚፈልጉ ነው።

ጓደኞች በየጊዜው ይቀያየራሉ። ሰዎች የልጅነት፣ የትምህርት ቤት፣ የሥራ ጓደኞችን ያበጃሉ። ቤት ሠርተው አንድ ስፍራ ላይ ሲረጉ የጎረቤት ጓደኛ ይይዛሉ። አብሮ አደጎቻቸውን የሚሸሹት ዛሬ በሚያከብራቸው ሰዎች ፊት የትላንት አስቂኝ ታሪካቸው እንዲነገር ስለማይፈልጉ ነው። ልዩ ማስጠንቀቂያ ልስጣችሁ፦ አገር እየመራ ወይም በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያለ ሰው አብሮ አደጋችሁ ቢሆን እንኳ አውቀዋለሁ፣ ያን ጊዜ እንዲህ ነበረ … አትበሉ። ሰዎች ሥልጣን ላይ ሲወጡ እንዲነገር የማይፈልጉት ታሪክ ካለ የሚያወራውን አብሮ አደግ በማጥፋት ሊጀምሩ ይችላሉ። ሁላችንም ብንሆን እንዳይነገርብን የምንፈልገው ታሪክ አለን። ሰው ታሪኩን ራሱ ያውራው፣ ስህተቱን ራሱ ይቀልድበት እንጂ እኛ መናገር አይገባንም።

በአስቂኝ ታሪክ ውስጥ ሰውዬው ለትዳሩ የደበቀው ምሥጢር ሊወጣ ይችላል። ይልቁንም ለልጆች የወላጆቻቸውን አስቂኝ ታሪክ ስናወራ መጠንቀቅ አለብን። ለዚያ ልጅ የዓለሙ ንጉሥ የእርሱ አባት እንደሆነ ይሰማዋል። ትልቁን አባቱን አሳንሰን ስናወራ የልጅ ስሜትና ከፍታ ይጎዳል። “ከአብሮ አደግ አትሰደድ” ይባላል። አብሮ አደግ የሚያውቀው ያ ሰው፣ እንደዚያው የቀረ ይመስለዋል። ዛሬ ላይ ተጠያቂ ሊቅ፣ አዛዥ ሹም፣ ባራኪ ጳጳስ ሆኗል። ምንም እንኳ ትላንት አንተ ብሎ የሚያወራ ከሆነ አሁን አንቱ ማለት አለበት። አይሆንም እንደ ቀድሞህ ጥራኝ ካላለው በቀር ወንበሩን መዳፈር የለበትም። ያ ሰው ራሱን ሳይሆን እግዚአብሔርንና ሕዝብን ወክሎ የሚኖር ነው። ስለዚያ ሰው ያለን ትንሽ እውቀት እንቅፋት ሊሆነን አይገባም። ሰው እንደ ልጅነቱ አይደለም። የዛሬ የውበት ተወዳዳሪዎች ትላንትና በልጅነት ዘመናቸው ቢያፀዱአቸው መልሰው የሚቆሽሹ ፣ የአፍንጫቸው ቆሻሻ ምርት የሚመስል ሊሆኑ ይችላሉ። የዛሬው ጀግና ትላንት በጣም ፈሪ የነበረ ሊሆን ይችላል፡ የዛሬውም ቢሊየነር የትላንት ለምኖ ጎራሽ ሊሆን ይችላል። እገሌን አውቀዋለሁ ማለት ዋጋ ያስከፍላልና መጠንቀቅ ይገባል። “ከነገር እንጃ፣ ከእህል ዐጃ” ይባላል።ደግሞም  “አላውቅም አስገድሎ አያውቅም” ይባላል።

ጓደኛህ ቀልድ የማይወድ ከሆነ አትቀልድ፣ አትቀልድበትም። የሰው ልጅ ከራሱ ጋር የማያቋርጥ ስብሰባ የሚቀመጥ ፣ ከአሳቡ ጋር የሚታገል ፍጡር ነው። ራሱ ለራሱ እያነሰበት በሚቸገርበት ጊዜ ስንቀልድበት ሊጎዳ ይችላል። ይልቁንም በሌሎችና በሚያከብሩት ሰዎች ፊት መቀለድ ግንኙነትን ይጎዳል። ለብቻ ፣ በር ዘግቶ መቀለድ ቢያኰርፍ ለመለማመጥ ይረዳል::

ግንኙነት ሁልጊዜ ኮስታራ፣ ውይይትም ወረቀትና ብዕር ይዞ ሲሆን ኮሚቴ እንጂ ወዳጅነት አይደለም። ከተለመደው ኑሮ ወጣ እያሉ መጫወት መልካም ነው። ቀልድ ግን ዋነኛ ዓላማው ማሳቅ ብቻ ነው። ማንም ሰው ደግሞ መሳቂያ መሆን አይፈልግምና ሊከፋው ይችላል። ደግሞም ሁለታችን ብቻ የምናውቀው ምሥጢር እንዴት ወጣ? ብሎ ሊያዝን ይችላል። ቀልድ እያሳሳቀ ምሥጢር ያወጣልና::

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐ ምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ