የሰዎችን ጠባይ ተረዳ
ሰዎች አንዱን ጌታ ከመምሰል ሲወርዱ ብዙ ጠባያትን አዳብረዋል። በዚህ ምክንያት ከልጅነት አንሰው፣ ከመላእክት ወዳጅነት ወርደው፣ ባሕርየ እንስሳን ነውርን አለመደበቅ፣ ባሕርየ አራዊትን በጭካኔ ብዛት አለቃ መሆንን፣ ባሕርየ ሰይጣንን ራስንና ቍሳዊ ነገርን ማምለክ ገንዘብ አድርገዋል። ይልቁንም የመጀመሪያው ኃጢአት በመጨረሻው ዘመን ላይ ይደገማል። ከብዙ በጥቂቱ የሰዎች ክፉ ጠባይ፦
ራሳቸውንና የተፈጠረውን ማምለክ ፦
እኔ ፣ እኔ ማለት፣ ክብር ለእውቀቴ ብሎ መመጻደቅ ፣ ገንዘብንና የዚህ ዓለም ሥልጣኔን ማምለክ ጠባያቸው ሆኗል:: “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” የሚለው የዚህ ዘመን ሰው ነው። መንገደ ሰማይ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን ዘንግቷል። ሰው መንገድን ሲይዝ እውነተኛው መንገድ ነው ወይ ? ብሎ ያረጋግጣል። የመድረሱ ዓላማም ሕይወት ወይም መኖር ነው። መንገድ፣ እውነት ፣ ሕይወት ክርስቶስ ነው ።
አለመርካት :-
ሰዎች አስቀድመው አንድን ነገር ለማግኘት ብርቱ መሻት አላቸው። ካገኙ በኋላ ደግሞ እርካታ የላቸውም። እጦታቸው የሚፈልገው አንድን ነገር ነው፣ ካገኙ በኋላ ግን መምረጥ እያቃታቸው ውዝግብ ውስጥ ይገባሉ። የተመኙትን ወዳጅም ትዳርም አግኝተዋል። አለ መርካት ግን ቀዥቃዣ ያደርጋቸዋል። በዚህ ምክንያት ሊያስቀይሙን ሜዳ ላይ ትተውን ሊሄዱ ይችላሉ።
ሰበበኛነት፦
ከአንድ ዕቃ ጋር አብሮ አጠቃቀሙን የሚገልጥ ጽሑፍ እንደሚኖር ከኃጢአት ጋርም አብሮ ምክንያት ይኖራል። ራሳቸውን ነጻ አድርገው እኛን የስህተቱ ጀማሪና ፈጻሚ ለማድረግ ይጥራሉ። አንዳንዴም እግዚአብሔር የፈጠረብኝ ማንነት ነውና ልለውጠው አልችልም ይላሉ። በዚህም እግዚአብሔርን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
በሌላው ሞት ላይ ለመኖር ማቀድ፦
የእነርሱን ተቀባይነት ያሳጣው የዚያ ሰው መኖር ይመስላቸዋል። ያንን ሰው በማጥፋት ታዋቂ ነፍሰ ገዳይ እንጂ ታዋቂ ሠራተኛ አይሆኑም። ቅናት ግን ያሳውራቸዋል።
ዓለምን ጠባብ ያደርጉታል፦
አብሮ መኖር ካልተቻለ ተማምኖ መለያየት ይቻላል። ዓለም ያሉበት አካባቢ ብቻ፣ አጠገባቸው ያለውም ብቸኛው የዓለም ሰው ይመስላቸዋል። በዚህ ምክንያት እልፍ በማለት ሕይወታቸውን ማትረፍ ሲችሉ ሕይወትን በንብረት ይለውጣሉ፤ ለእኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን በሚል እሳቤ የወደዱትን ይገድላሉ።
ተለዋዋጭ ማንነት፦
ሰዎች የሚፈልጉትን ስለማያውቁ የሚፈልጉትን ቢያገኙትም ፍለጋ ይቀጥላሉ። በመንፈሳዊና በሥጋዊ መሪዎቻቸው ላይ ያጉረመርማሉ:: ከዛሬው የትላንቱ ጥሩ እንደነበር ያስባሉ። ትላንት ግን በትላንትናው ሲማረሩ እንደ ነበር ይዘነጋሉ። ሁልጊዜ የዘንድሮው ከባድ ነው ይላሉ። ይባስ አይምጣ ቢሉም በአሁኑ አያመሰግኑም።
የትላንቱን ይረሳሉ፦
የትላንቱ ማንነታቸውን የሚገልጥ መረጃም ሆነ ሰው እንዲጠፋ ያደርጋሉ። እንዳለሁ ያለሁ ነኝ ለማለት ይሞክራሉ። ወዳጄ እንዴት ያሳድደኛል ? እንዳላሉ ወዳጃቸውን ያሳድዳሉ ፣ ያጠፋሉ ።
ተውኔት ይሠራሉ፦
በፊታችንና በኋላችን የሚናገሩትና የሚያደርጉት የተለያየ ነው። እንደሚወዱንና እንደሚያከብሩን ለማስመስል ይሞክራሉ:: የምንፈልገውን ዜማ ያዜማሉ፣ የምንፈልገውን ነገር ሰጥተውን እንደ ሕፃን በአሻንጉሊት ለማታለል ይሞክራሉ። ስንናገር አዎ አዎ ይላሉ፣ በልባቸው ግን ይሰለቻሉ፤ ለእኛ የሠሩት እንዲመዝገብላቸው ይፈልጋሉ። ፍቅርን ሥራ ያደርጉታል።
ሲፈልጉን ብቻ ይፈልጉናል፦
እኛ ስንፈልጋቸው ላይገኙ፣ እነርሱ ሲፈልጉን ግን አሁኑኑ የሚሉ ይሆናሉ። ፍቅር ባሪያ ሲያደርገን እንዳነስን አድርገው ይቆጥሩናል። እስከ መቼ እንደሚቆዩ በጊዜ ልኬት አብረውን ይሆናሉ። ሲሄዱ አይነግሩንም።
እነዚህ በእኛ ላይና በሰዎች ላይ የሚታዩ ክፉ ጠባያት ናቸው ። ብንችል ሦስት ነገሮች ያላቸውን ወዳጅ ማድረግ መልካም ነው።
ፈሪሀ እግዚአብሔር :-
ሰውን ደግ የሚያሠራው፣ ቢሳሳት እንኳ የሚመልሰው እግዚአብሔርን መፍራት ነው።
ቅንነት፦
ቀና ያልሆነ ሰው መልካም ለማድረግ ሳይሆን የተደረገለትን መልካም ነገር በጥሩ መመልከት አይችልም። ቅንነት ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ተቀባይ ለመሆንም ያስፈልጋል።
ገራምነት፦
ብልጥ ሰው ብልጠቱ ቶሎ ይታወቃል። ስለዚህ ሁሉም ሰው እየሰለቸውና እየሸሸው ይመጣል። በፍቅር የሚያገኘውን ነገር በብልጠቱ የሚያጣ ብዙ ነው። ብልጠት የእኔ ለእኔ ፣ የእነ እገሌ የእኔ ነው ብሎ ማሰብ ነው። ዕድሜን የሚያረዝም ገራምነት ነው። ገራሞች ገራም የሆኑት ብልጠትን ስለማያውቁ ሳይሆን ስለ ናቁት ነው።
እስቲ ሰው አድርገን!
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም.