መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? » ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -8

የትምህርቱ ርዕስ | ከሰዎች ጋር ለመኖር ምን እናድርግ? -8

ፈጥነህ አትፍረድ

ሰዎች ምክንያታቸውን ሲነግሩህ እንዳታፍር ፈጥነህ  አትፍረድ። ስልካቸውን የዘጉት ብድር እንዳትጠይቃቸው መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፣ በድንገተኛ እስር ቤት ገብተው ነው።  ረጅም ጊዜ የጠፉት አሁን ውጭ አገር ስለ ሄዱ ኰርተውብህ አይደለም፣ ታመው ሆስፒታል ስለ ነበሩ ነው። አንተን ለማናገር የሚሸሹት ከጠላቶችህ ጋር አድመው ሳይሆን የእናታቸውን መርዶ ሰምተው አንተን  ካገኙ ሆድ እንዳይብሳቸው ነው ፣ ሰዉ ሁሉ እኛ የማናውቀው ውስጣዊ ትግል እያካሄደ ነው ። ከቤትህ የጠፉት፣ ወዳጅ ሲያረጅ በጓሮ ይሄዳል ብለህ የተረትህባቸው የአንተን ኑሮ ላለመበጥበጥ ብለው  እንጂ በቤትህ ባሉት ሰዎች ተሰድበው ነው ። የቅርብ ሰዎችህን የተናገሩት አንተን ንቀው መስሎህ ተበሳጭተሃል፣ ዘመዶችህ ሊያጠቁህ እንደሆነ አውቀው ላንተ እየተጣሉልህ ነበር ። አንድ ቀን እውነት ስታበራ  የፈረድህባቸው  ልክ እንደ ነበሩ ይገባሃል።

የራቁህ ተገደው፣ ዝም ያሉህ እንዳታዝን፣ ቆይ የሚሉህ የእግዚአብሔርን ጊዜ እየጠበቁ ስለሆነ ነው። ከሰርግ ከልቅሶ ገለል የሚሉት ማኅበራዊ ኑሮ ስለሚጠሉ አይደለም፣ በቂ ልብስ ስለሌላቸው ይሆናል። እቤታቸውን የማያሳዩህ አንተ ግልጽ እነርሱ ድብቅ ስለሆኑ አይደለም፣ የሚላስ የሚቀመስ ስለሌላቸው ነው ። የትዳር አጋራቸውን የማያስተዋውቁህ ክፉ ዓይተህና ሰምተህ እንዳትጎዳ ነው። ከጓደኞቻቸው ጋር ሲሆኑ ስልክ የሚያነሡልህ እነዚያ ሰዎች ላንተ ጥሩ አመለካከት ስለሌላቸው ስምህ በክፉ እንዳይነሣ ነው። እየከለሉህ ሳለ እያፈሩብህ ይመስልሃል። በጣም መልካም ስትሆንላቸው የሚርቁት “እኔ መጥፎ ሰው ነኝ እንዳላስቀይመው” ብለው ራሳቸውን ፈርተው ነው። ችግር ውስጥ ስትገባ የሚርቁት ሁሉም ከዳተኞች ሆነው አይደለም፣ የወዳጄን ስቃይ ቆሜ ማየት አልችልም ብለው ነው። ጉንፋን ይዞህ ያልጠየቁህ እነርሱ በዚያች ሰዓት ካንሰር አለባችሁ ተብለው የበለጠ እንዳያስጨንቁህ ነው።

በምርቃትህ ቀን ስላልመጡ አዝነሃል፣ እነርሱ ግን ተጨማሪ የትምህርት ዕድልን እያፈላለጉልህ ነበር። በመውለድህ ያልተደሰቱ መስሎህ ቅር ብሎሃል ፤ እነርሱ ግን ጓደኛዬ ተጨናቂ ነው ፣ የበለጠ እንዳይጎዳ ብለው ነው። ውጭ አገር ያልጋበዙህ ቃላቸውን አጥፈው አይደለም፣ ራሳቸው የሚኖሩት ሰው ጋ ተጠግተው ስለሆነ ነው። ብድር የከለከሉህ ጨክነውብህ አይደለም፣ በዕዳ ተከሰው ፍርድ ቤት እየቆሙ ስለሆነ ነው።

አገር ለቀው የጠፉት ዘርፈው አይደለም፣ ተዘርፈው ሊሆን ይችላል። ሰው በቃን ብለው የከተማ መናኝ የሆኑት ራስ ወዳድ  ስለሆኑ አይደለም፣ ስንዴ ዘርተው እንክርዳድ ማጨድ ስለ ሰለቻቸው ነው። የትዳር ጥያቄህን ያልተቀበሉት ስለ ናቁን አይደለም፣ ተላላፊ በሽታ ውስጥ ስላሉ ላንተ አስበው ነው። በቋንቋህ ስታወራቸው የማይመልሱት በቋንቋው ስለማይኰሩ አይደለም፣ ቋንቋውን የማይሰሙ ሰዎች ስላሉ ዘረኛ እንዳይሉህ ብለው ነው። ከግብዣህ ላይ ውልቅ  ብለው የሄዱት ስለ ተናደዱ አይደለም፣ ሆዳቸውን ስላመማቸው ነው። በጣም የማይቀርቡህ የማይለምዱ አውሬ ስለሆኑ አይደለም፣ በጣም ስለሚወዱህ  ሳስተውልህ ነው። በዚያ ኃጢአት ውስጥ ያሉት አመለኛ ሆነው አይደለም፣ መፈወሻውን ቢያጡ መደበቂያ ፈልገው ነው። የተለየ ሽታ የሚሸቱህ ስለማይታጠቡ አይደለም፣ በሽታ ገጥሟቸው ነው። ቃላቸውን ያልጠበቁት አባይ ስለሆኑ አይደለም፣ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሟቸው ነው። በችግርህ ትንሽ እንኳ ያልረዱህ ይህን እንዴት እሰጣለሁ ? ብለው አንሶባቸው ነው። ገንዘብህን ያልመለሱት ጨምሬ ቦታ አገዛለታሁ ብለው አልሞላ ብሏቸው ነው።

ፈራጁ ትክክል ፣ ተፈራጁ ስህተተኛ አይደለም። ከፍርድ ኃጢአት ለመዳን መታገሥ፣ ከባለቤቱ መስማት፣ ቅሬታን መግለጥ፣ ጌታ ሆይ ልቤን ጠብቅ ብሎ መጸለይ መልካም ነው። አንዳንድ ሰዎች የሚያሳዝኑን እኛን ለማስደስት ብለው መንገዱን ስላላወቁበት ነው። ፈራጅ አትሁን በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ፣ ምን ዓይነት መከራና ትግል እያሳለፉ እንደሆነ አታውቅምና። አንተ ፈገግ አላሉልኝም እያልህ ነው፣ እነርሱ ልሙት ልኑር በሚል ትግል ውስጥ ናቸው። ያንተ መደሰቻ አሻንጉሊት አይደሉም፣ ምን ሆናችሁ? ብለህ ትካዜአቸውን ተካፈል። ራስህን ብቻ አታዳምጥ ::  ያሳየኸውን ፊት አታጥቁር፣ የሰጠኸውን በረከት አትንካ። የዘረጋኸውን እጅ አትጠፍ ።  ሰው የተሰጠው መፍረድ ሳይሆን ማማለድ ነው። ሰው አማላጅ እንጂ ፈራጅ አይደለም። ቀን ሲጥል ፈራጅ ብዙ ነው።

ማኛ ጤፍ አጥግቦኝ ዝቆ ከጎተራው፣
ሆዴ ይታዘበኛል አፌ ባያወራው ፤

እንደ ተባለ የትላንት ሰጪነቱን አስብ። ደግነቱን አላወራህምና ጉድለቱን አትናገር። ምናልባት ስለ ወደቀ ቀኑ ያንን ሰው ስደበው ፣ ስደበው እያለህ ነውና ይህን ፈተና አሸንፈው :: ዓለም ሲነሡ ያለ ምክንያት ይክባል፣ ሲወድቁ ያለ ምክንያት ይፈርዳል። ዳኛ እንኳ ለመፍረድ ዐቃቤ ሕጉን ፣ ጠበቃውን ፣ ባለቤቱን ፣ ምስክሮችን ያደምጣል። ጊዜ ይሰጣል፤ ሕጉን ያገናዝባል። የጥፋተኝነት ውሳኔ መጀመሪያ ላይ ይሰጣል፣ ቀጥሎ የቅጣት ብይን ያሳልፋል። አንድ በክርስቶስ የዳነ አማኝ ከምድራዊ ዳኛ ማነሱ ያሳዝናል። በዓለም ላይ በአብዛኛው የፍርድ ቤቶች ሎጎ ሚዛን ነው። ሚዛናዊነት ከአጉል ፍርድ ያድናል።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 18 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ