ለሰዎች ሁሉን አትንገራቸው
የሰው ልጅ ከተወለበት ቀን ጀምሮ የሚመገብና የሚማር ፍጡር ነው። መዋለድ የተዋሕዶ ውጤት ነው፣ ወንድና ሴት በሥጋ ሲተዋወቁ ልጅ ይወለዳል። እንዲሁም መምህርና ተማሪ በጥበብ ሲዋሐዱ አእምሮአዊ ልደት ይገኛል። ውኃውና መንፈሱ ሲዋሐዱ ዳግመኛ ከማይጠፋ ዘር ይወለዳል። የሥጋ ልደት ከአባት ከእናት፣ የአእምሮ ልደት ከመምህራን፣ መንፈሳዊ ልደት ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይገኛል። በዕድገት ውስጥ ምግብ አስፈላጊ ሲሆን ወተት፣ ሥጋ ፣ አጥንት በየተራ የሚደርስባቸው የምግብ ዓይነቶች ናቸው። ወተት ለወጣንያን (ለጀማሪዎች) ፣ ሥጋ ለማዕከላውያን፣ አጥንት ለፍጹማን ወይም ለምሉአን የሚሰጥ ነው። እንዲሁም ለአዲስ አማኝ ብዙ የነገረ መለኮት እውቀት፣ ብዙ ጾም አይታዘዝም። በአቅሙ የቃል ወተትን እየጠጣ ያድጋል። የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ምሥጢር፣ በአስተዳደር ላይ ያሉ ክፍተቶች እርሱን አይመለከተውምና አያሳትፉትም። ምንም የቤቱ አባል ቢሆን ለአራስ ልጅ የትዳሩን ችግር አያዋዩትም። የሰው ልጅ ሥጋዊ ሸክሞችን ለመሸከም ዕድገቱና ጥንካሬው ይወስነዋል። እንዲሁም እውነትን ለመሸከም መንፈሳዊ ትከሻ ያስፈልገዋል። ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ:- የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም በማለት መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድ ድረስ እንዲታገሡ ነግሯቸዋል። (ዮሐ.16፥ 12 ) ክርስቶስን የሚያህል መምህር የለም፣ የደቀ መዛሙርቱ ዕድልም ልዩ ነው። ነገር ግን ሁሉን አልነገራቸውም። በሕይወት ውስጥም ዝርዝር መረጃ ማንም ሰው የለውም። ነገ፣ የሞት ቀን ምሥጢር ናቸው። ሰውን በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለ ማወቅም ያድነዋል።
ለሁሉም ምእመናን የማይነገሩ ትምህርቶች አሉ። የቤተ ክርስቲያን አባላትም በዓለም አደባባይ ወጥተው እርስ በርስ መካሰስ ሃይማኖት እንደ መካድ ይቆጠራል። ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ከደናግል ብቻ እንዲሆኑ የወሰነችው ከወራሽ ልጆችና ሚስቶች ጋር በየፍርድ ቤት መቆም ምስክርነትን እንዳያበላሽ አስባ ነው። እስከ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ያገቡ ቀሳውስት ጳጳሳት ይሆኑ እንደ ነበር ልብ ይሏል። በቤተ ክርስቲያን እውነት ቢሆንም ሁሉ ለሁሉ አይነገርም። ቤተ ክርስቲያን የምሥጢር ቤት መሆኗ አይዘነጋም። አጥንት የሚበሉ ወተት ቢጠጡ የበለጠ ይጠቅማቸዋል፤ ወተት የሚጠጡ ሕፃናት ግን አጥንት ቢበሉ ተቀርቅሮ ይገድላቸዋል። የወጣንያንን ትምህርት አዋቂዎች ቢማሩ እንደገና ይታደሳሉ። የመንፈሳዊ የልጅነት ዘመናቸው ትዝ ይላቸዋል:: ሕፃናት ስለ ሸምግልና ቢያወሩአቸው ግር ይላቸዋል።
ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ሁሉንም ነገራችንን ለሰዎች መንገር ተገቢ አይደለም። ሁሉን ለእግዚአብሔር የምንነግረው የመጀመሪያው እርሱ የማያውቀው ነገር ስለሌለ ነው፣ እኔስ የደበቅሁህ ፣ አንተስ የሳትከው ምን አለና ?! ፤ ሁለተኛ:- ሁሉን ቋጠሮ ሊፈታ ይቻለዋል፤ ሦስተኛ:- የሰማውን ምሥጢር አያሰማብንም። አራተኛ አይታዘበንም። ሰዎች ሊያውቁት የሚገባቸው ነገር አለ። ሁሉም ነገራችን አደባባይ ከሆነ ይህ የአእምሮ ሕመምና የማኅበረሰብ ቀውስ ምልክት ነው። ሰዎች የራሳቸው ችግር ስላለባቸው የሚሰሙን በተወሰነ መጠን ነው። የሚኖሩት እኛን ለመስማት አይደለምና ። ደግሞም እግዚአብሔር ካልረዳቸው የሚሰሙን በመታዘብና በመፍረድ ስሜት ነው።
ሰዎች ለጤና ባለሙያ ሁሉን መንገር አለባቸው፣ ያ ማለት ግን ሁሉን በሽታቸውን መንገር አለባቸው ማለት እንጂ ሙሉ ሕይወታቸውን መናገር አያስፈልጋቸውም:: ለመንፈሳዊ አባታቸው ግን ሁሉን መናገር መልካም ነው። መናገር በራሱ ቴራፒ ነው ። ሰዎች ውስጣዊ ስቃያቸው የሚድነው ለሚያምኑት ሰው ሁሉን ሲናገሩ ነው። አገልጋዩም አደራውና ጸጋው ሁሉን ለመስማትና ለመሸፈን፣ ለመጸለይና አብሮ ለመቆም ያግዘዋል። የእግዚአብሔር አገልጋዮች በምድር ላይ ባይኖሩ ኖሮ ብዙ ሕዝብ ጨርቁን ይጥል ነበር። ሰይጣን ምእመናንን የሚጥላቸው ለመንፈሳዊ አባት ድብቅ እንዲሆኑ በማድረግ ነው። ልጆች ለወላጆቻቸው ድብቅ ከሆኑ ይሞታሉ፣ ችግሩ የሚታወቀው መጨረሻ ላይ በመሆኑ ርብርቦሹ የማይጠቅም ይሆናል። በቅዳሴአችን ቋንቋ ብንናገር ያን ጊዜ እርዳታ ይሆናል፣ የማይጠቅም እርዳታ ነው። ከባዱ ነገር ጥሩ አድማጭ ማጣት እንጂ መናገሩ አይደለም።
ለሰዎች ሁሉን ስንናገር መሸከም ካቃታቸው እየሸሹን ይመጣሉ፣ ክፉ ስለሆኑ ሳይሆን አቅም ስላጡ ነው። ሰው አልችልም ካለ አልቻለም ማለት ነው ። ሁሉን ስንነግራቸው አውቀውን የጨረሱ ስለሚመስላቸው ሊንቁን ይችላሉ። እኛ ወዳጅ ብለን እንደነገርናቸው እነርሱም ወዳጄ የሚሉት አላቸውና ምሥጢራችንን ያባክናሉ። ደግሞም የትልቅ ሰው ልኩ ሁሉን አለመናገሩ ነው። ለሃይማኖት ተማሪዎቻችንም ሁሉን መንገር አይገባም። ቤተ ክርስቲያን ተከብራ የኖረችው ሁሉም ነገር ባለመነገሩ ነው። የካቶሊክ ፖፕ ምርጫ ዓለም በናፍቆትና በጉጉት የሚጠብቀው ምሥጢራዊ ስለሆነ ነው። ሰዎች ከበጣም ግልጽነት ምሥጢርን ያከብራሉ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም