“ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው፡- ስለ ምን ትተኛላችሁ ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው ።” ሉቃ. 22፡45 ።
ጌታችን ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል ፤ እንዲሁም ኑሮውን አብነት አድርጎልናል ። በመከራ ሰዓት ፣ ፈተና ሲቃረብ ፣ የጭንቅ ዋዜማ ሲመጣ ፣ ወዳጅ ሲለወጥ ፣ የታመነም ሲከዳ ፣ ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት እውነትን ተባብሮ ለመስቀል ሲወዳጅ … መፍትሔው ጸሎት ብቻ መሆኑን ጌታችን ሊያስተምረን በብርቱ ጸለየ ። ጸሎቱ የሚያስፈልገው ለደቀ መዛሙርቱ ነበር ፣ ደቀ መዛሙርቱ ተኝተው ግን ጌታችን ጸለየ ። መጸለይ የሚገባቸው ለጸሎት አልተጉም ። ሰይፍ ለመምዘዝ የተጋው ጴጥሮስም ለጸሎት መትጋት አልቻለም ። ጌታችን ከታላቅ የጸሎት ትጋት በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመጣ ተኝተው አገኛቸው ።
የፈተና ሰዓት ሲቃረብ ለመጸለይ አቅም የሚነሣ አዚም ይመጣል ። ሽብርና ወሬ ይነግሣል ። አእምሮም ፋታ አጥቶ ይበጠበጣል ። ግምትና መረጃዎች አየሩን ይቆጣጠሩታል ። እግዚአብሔርን ከማሰብ ወቅቱን ማግነን ይበረክታል ። በዚህ ግፋ በል በሚባልበት ፣ በለው በበዛበት ሰዓት የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሰው ሐሞት የሚያፈስስ ተደርጎ ይገመታል ። ጸሎት መግደል ባይሆንም መግደል ጸሎት ነው ተብሎ ይታመናል ። እገሌ ከዳ ፣ እገሌ ካደ የሚለው ወሬ ይበዛል ። ነፋሱን ለመስማት የሰላው ጆሮ ቃሉን ለመስማት ይፈዝዛል ። ለመጸለይ አቅም ያጣ ሰይፍ ለመምዘዝ አቅም ያገኛል ። በሊቀ ካህናቱ የተናደደ የባሪያውን ጆሮ ይቆርጣል ፤ በመስፍኑ የተበሳጨ ሎሌውን ካልገደልሁ ይላል ። “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” መደብደብ ይበዛል ። እየተጓዘ የሚጓዝና ተቀምጦ በአሳብ የሚጓዝ ብዙ ይሆናል ። ሁሉም ከውስጡ የሚያወጣው የተቃጠለ አየር ይሆንና ሕይወት የሚሰጥ ትንፋሽ የሚገኝበት ሰው ይታጣል ። አንዱ አንድ ሰው ሞተ ሲል ሌላኛው የበለጠ መርዶ ይዟልና አሥር ሰው ደግሞ እዚያ ጋ ሞተ ይላል ። ልውውጡ የበለጠ ክፋት እንጂ የደግነት ድምፅ አይደለም ። እግር ሳይያዝ አሳብ ይያዛል ። ጠላት ሳይመጣ በወሬ አገር ይፈታል ። የሩቅ ሲጠበቅ የቅርቡ ቀድሞ ይከዳል ። በዚህ ሰው ሳይጠጣ በሚሰክርበት ጊዜ እንደ ምንም ብሎ መጸለይ መቻል መታደል ነው ። ከሚነፍሰው ጋር ላለመንፈስ ፣ አየር እየጎሰሙ ከንቱ ውድድር ላለማድረግ ጸሎት ወሳኝ ነው ። ጸሎት ለሁሉ ነውና ስንጸልይ ጠላትን ሳይቀር የመውደድ አቅም እናገኛለን ። ያለፉትን ብቻ ሳይሆን እየመጡ ያሉትን ጠላቶችም ይቅር ብለን ለመጠበቅ ኃይል እናገኛለን ። ጸሎት ሁኔታን ሳይሆን እግዚአብሔርን ያያል ፤ ጸሎት ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን ያጸናል ። ስለዚህ ጌታችን ተግተው እንዲጸልዩ ቢነግራቸው ደቀ መዛሙርቱ ግን አብዝተው ተኙ ። አብዝቶ ሲነግራቸው አብዝተው ደነዘዙ ።
“ባለጌ የተመከረ ዕለት ፣ ቁንጫ የተጠረገ ዕለት ይብስበታል” ይላሉ ። ጸልዩ በተባለው ልክ ስድብ ከበረከተ ፣ ቃሉን መስማት በሚገባ ሰዓት ራስን መስማት ካየለ አስቸጋሪ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ መከራው የጌታ ሲሆን እነርሱን ግን ጣላቸው ። ፍሙ ሳይሆን ወላፈኑ ፈጃቸው ። “የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ” እንዲሉ እነርሱ በሚያበረቱበት ሰዓት መከረኛው ጌታ እያበረታቸው ነበር ። መጸለይ የሚገባቸው መከራ እንዳይመጣባቸው አይደለም ፣ መከራውማ የጌታ ነው ። የሚጸልዩት በስፍራቸው መገኘት እንዲችሉ ፣ በሚያቀል ቀን እንዳይቀሉ ፣ በዝምታ ዘመን እንዳይለፈልፉ ፣ ለታላቅ ሰራዊት ትንሽ ቢላዋ እንዳይስሉ ፣ ለመንፈሳዊ ውጊያ በሥጋ እንዳይጋጠሙ ነው ። የፈተና ሰዓት ጥቂት ነው ፣ ነገር ግን ለዘመናት የገነባነው የሚናድበት ፣ አለሁ ብለን በፎከርንበት ነገር የምንታጣበት ነው ። “ሊያልፍ ውኃ አደረገኝ ድሀ” እንዳለው ሊያልፍ ቀን ክፉ የሚያናግር ፣ ፍቅር አልባ የሚያደርግ ነው ። ልብ ከጸሎት ውጭ አጥር የለውም ። ክፉ ቀን ከጸሎት ውጭ መሻገሪያ ድልድይ የለውም ።
ጌታችን መለስ ብሎ ያያቸው ነበር ። እርሱ ለብዙዎች መከራ ቀድሞ የተገኘ ፣ ሲከሰሱ ጠበቃ ሁኖ የተናገረ ፣ ሲታመሙ ሐኪም ሁኖ የፈወሰ ነው ። በእርሱ የፈተና ሰዓት ግን ደቀ መዛሙርቱ ለአንዲት ሰዓት እንኳ መትጋት አቃታቸው ። ዛሬ በከንቱ የሚወገሩ ወዳጆች አሉን ፣ ነገር ግን እውነቱ ይህ ነው ብለን አንደበት ካልሆናቸው ፣ ዛሬ በከንቱ ለሚገፉት ጥግ ካልሰጠናቸው ፈተናው ከፈተነኞቹ ይልቅ እኛን እያበጠረን ነው ። በሰፌድ ላይ ያለ ስንዴ ቀሎ እንዲበጠር እንዲሁም ክፉ ቀን ያበጥራል ። “ክፉ ቀን አይምጣ ወዳጅ እንዳላጣ” የሚባለው ለዚህ ነው ።
“ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው፡- ስለ ምን ትተኛላችሁ ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው ።” ሉቃ. 22፡45 ።
በጸሎት እየተጋ ያለው ጌታችን ያልተጉት ወገኖቹ አሳሰቡት ። ከጸሎት ተነሥቶ ወደ እነርሱ መጣ ። እንኳን መኝታ ከንቱ ንቃት እንኳን በማያድንበት ሰዓት እነርሱ ተኝተው አገኛቸው ። የሆሳዕና እንጂ የዓርብ ወዳጅ መሆን ያልቻሉት ለዚህ ነው ። በሚያስፈልጉበት ቀን የሸሹት ፣ በደቀ መዝሙር ወግ ያልተገኙት ለዚህ ነው ። ወታደር በክፉ ቀን ለንጉሡ ይገኛል ። እናትም ከልጇ በፊት ለመሞት ትደራደራለች ። ደቀ መዝሙር ግን ለአንዲት ሰዓት በጸሎት መትጋት ካልቻለ የሚገርም ነው ። ስንቱ ወገን በፈተና ሰዓት መረጃ ያሯሩጣል እንጂ ልጸልይ አይልም ። ካልጸለይን መከራውን ዕድሜ እየሰጠነው ነው ።
ከኀዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸው ይላል ። ኀዘኑ የተወለደው ጌታ እንደሚሞት ስለሰሙና አጠገባቸውም ብዙዎች መንጠባጠብ ስለጀመሩ ነው ።ኀዘን ልቅሶ ስላለው ያስተኛል ። ሕፃን ልጅ አቅልሶ ፣ አልቅሶ እዚያው ፍንግል ብሎ ይተኛል ። ኀዘን በእንባ ጎርፍ ወደ እንቅልፍ ሸለቆ ይወስደናል ። ኀዘን ችግሩና ጉዳቱ ላይ መቆየት ስለሆነ ያደክማልና ያስተኛል ። ለሰሙት ችግር መፍትሔውን መፈለግ እንጂ ማዘን ብቻውን ጥቅም የለውም ። ኀዘን ፣ ኀዘን ወልዳል ። ኀዘን ካልራቁት ተጣብቆ ይኖራል ። ኀዘን በቃኝ ካላሉት ገና ለቀጣይ ዓመታት ይሻገራል ። ምን ማድረግ ይገባኛል ማለት ግን የኀዘን መድኃኒት ነው ። የኀዘን መፍትሔው ጸሎት ነው ።
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ አለ ። መከራው የጌታ ነው ፣ ፈተናው ግን የደቀ መዛሙርቱ ነው ። ፈተና በመከረኞች ላይ የሚኖረን አስተሳሰብ ፣ የቀለለ ሚዛን ነው ። ፈተና ከመከረኞች ጋር አብረን ለመቆም ድፍረት ማጣት ነው ። የጊዜ ሆያሆዬ የሚጫወቱ ለተጠቁት ለመቆም አቅም ያንሳቸዋል ። ከቀኑ ጋር ለመክፋትም ፣ ለክፋት አወዳሽ ለመሆንም ተላልፈው ይሰጣሉ ። ተግቶ መጸለይ ግን ሚዛናዊ ኅሊና ፣ የጸና አቋም ይሰጣል ።
እያዘንን ብቻ ከሆነ እንደክማለን ። መጸለይ ግን ላለፈው ስርየት ፣ ለሚመጣው ንጹሕ ልብ ይፈጥርልናል ።
አቤቱ በመልካም አስበን !
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ