የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከንስሓ መዘግየት

ቅዳሜ ታኅሳስ ፲፪/፳፻፮ ዓ/ም
(ማቴ.11÷20-24)
ትንሽ በጎ ሥራችንን ብዙ አድርገን እንናገራለን፡፡ ብዙ ክፉ ሥራችንን ግን ምንም እንዳልሆነ እናስባለን፡፡ የሌሎችን በጎ ሥራ የእኔ ብለን እናወራለን፤ ኃጢአታችንን ግን በግላችን እንደ ሠራን ማመን አንፈልግም፡፡ ሰዎች የበደሉንን መርሳት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ እንገምታለን፡፡ የእኛ ስህተት ግን እንደሚስተካከል እናምናለን፡፡ ለእግዚአብሔር የሰጠነውን አንረሳውም፤ ከእግዚአብሔርና ከሰዎች የተቀበልነውን ግን እንረሳዋለን፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ እንደሚያስፈልገን ከመቀበል እኛ ለእግዚአብሔር እንደምናስፈልገው መቀበል ይቀለናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ለኃጢአት ተገቢውን ስያሜ ስለማንሰጠው ከኃጢአት ለመላቀቅ ተቸግረናል፡፡
ሰዎች የኃጢአትን ኑሮ የሚመርጡት ውሳኔያቸው ስለሆነ ነው ብሎ መቀበል ይከብዳል፡፡ ኃጢአትም ሰላም ሰጪ ሆኖ ሰዎችን ይይዛል ማለት አይቻልም፡፡ ሰዎች በኃጢአት የሚቆዩበት የተለያየ ምክንያት አላቸው ከእነዚህ ጥቂቶቹን ብናይ፡-
1-     ሰላምን ለማግኘት፡- ለሃያ ለሠላሳ ዓመት ሲጋራ ያጤሱ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህንን ሱስ የጀመሩት በደረሰባቸው ጉዳት መፍትሔ ፍለጋ ይሆናል፡፡ ወደ ሲጋራ የከተታቸው ችግር ግን ዛሬ የለም፡፡ መፍትሔ የተባለው ነገር ግን ችግር ሆኖ ዛሬ አለ፡፡ አሁን ቃል የሚገቡትና የሚያፈርሱት ወደ ሲጋራ የከተታቸውን ችግር ለመተው አይደለም፡፡ መፍትሔ የተባለውን ችግር ለመጣል ነው፡፡ መጽሐፍ ‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም›› (ኢሳ. 48÷22) ይላል፡፡ ኃጢአት ጊዜያዊ መደበቂያ እንጂ ዘላቂ ሰላም አይሆንም (ዮሐ. 14÷27)፡፡
2-    ሥልጣን ያላቸው ስለሚመስላቸው ነው፡- ኃጢአት የሚሉት ጎረቤትን መንካት ነው፡፡ በራሳቸው ላይ ግን ሥልጣን ያላቸው ይመስላቸዋል፡፡ አንዳንዱ ኃጢአት ጎረቤትን ላይነካ ይችላል ግለሰቡንና እግዚአብሔርን ግን በግድ ይነካል፡፡ እኛ የእኛ አይደለንም፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ነን (1ኛ ቆሮ.3÷16፤ 6÷19-20)፡፡
3-   የተሻለ ነገር ስለማይታያቸው፡- ኃጢአት ሰዎችን ባሪያ የሚያደርገው ካሉበት ቦታ የተሻለ ነገር እንደሌለ በማሳየት ነው፡፡ ግን የተሻለ ነገር አለ፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡
4-   ትልቅና ትንሽ ኃጢአት በማለት ደረጃ ማውጣት፡- መጽሐፍ ትንንሹን ኃጢአት እንድንጠነቀቅ ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም የትልቁ ነገር መነሻው ትንሹ ነውና (መኃ. 2÷15)፡፡ የታወቁ የቆሻሻ ተራራዎች የጀመሩት ከአንድ ቅርጫት ቆሻሻ ነው ይባላል፡፡ ሱዳንና ግብጽን የሚያጠጣው የዓባይ ወንዝ መነሻው ትናንሽ ገባር ምንጮች ናቸው፡፡ ግዙፉን መርከብ ለመስጠም የሚያደርሰው በወለሉ ላይ ባለች ትንሽ ቀዳዳ በሚገባው ውኃ አማካኝነት ነው፡፡
5-   ኃጢአትን በስሙ አለመጥራት፡- የሚያመነዝሩት ከጓደኛዬ ጋር ፕሮግራም ነበረኝ እንጂ አመነዘርኩ አይሉም፡፡ ጫት የሚቅሙት ቀለል አድርገው ቀጭ ቀጭ እናደርጋለን ይላሉ፡፡ ሰክረው በድጋፍ የገቡት ማታ ስዝናና ነበር እንጂ ተዋረድኩ አይሉም፡፡ ሌቦቹ ቢዝነስ እሠራለሁ ይላሉ እንጂ እየሰረቅሁ ነው አይሉም፡፡ ኃጢአትን በስሙ ካልጠራነው ከኃጢአት መላቀቅ አንችልም፡፡
6-   ኃጢአትን በኃጢአት ለማጥራት መነሳት፡- ደም በደም አይጠራም ይባላል፡፡ ስህተትም በሌላ ስህተት አይሸፈንም፡፡ ኃጢአት የሚጠራው በንስሓ ነው፡፡
7-   ተሻሽሎ ለመምጣት ማቀድ፡- ወደ እግዚአብሔር መምጣት የሚፈልጉት ተሻሽለው ነው፡፡ ነገር ግን በወህኒ ያለ እስረኛ ራሱን መፍታት ይችላል? ሰው ራሱን ከኃጢአት ማውጣት አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ ጠርቷል፡፡ ክርስቶስም ለሰው ዘር ሁሉ የሕይወትን ዋጋ ከፍሏል (ዮሐ. 3÷16)፡፡
                                       ረጅም ዘመን እንደ ቀረህ በማሰብ ለንስሐ አትዘግይ!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ