መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ከውሻ እንማር

የትምህርቱ ርዕስ | ከውሻ እንማር

እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት ለፈጣሪነቱ ምስክር እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት፡- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” ባለው ይታወቃል ። /መዝ. 18፡1።/ ሰባኪ ዝም ቢል ፣ ዘማሪ ቢታክት እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር አልተወም የተባለው በወቅታት መፈራረቅ ነው ። “ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን ፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” /የሐዋ. 14፡17።/ ፍጥረታት አስተማሪዎቻችን መሆናቸውን ጌታችን ስለ መብል እንዳንጨነቅ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ ፣ ስለ ልብስ እንዳንጨነቅ የመስክ አበቦች ልብ አድርጉ በማለት ተናግሯል ። /ማቴ. 6፡ 26-28 ።/ ውሻ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተፋውን በመላሱ በአሉታዊ ተጠቅሷል ። ነገር ግን የተፋውን በመላሱ ርኵስ ነው አልተባለም ። የተፉትን ለሚልሱ ፣ በንስሐቸው ለማይጸኑ መናፍቃን ትምህርት እንዲሆን በምሳሌነት ተጠቅሷል ። ውሻ የሩቅ ዘመዶቹን እነ ተኩላንና ቀበሮን ትቶ ሰውን ወዶ በቤት የቀረ እንስሳ ነው ። ድመትም አጎቶቿን እነ ነብርን በዱር ጥላ በቤት ቀርታለች ። ውሻን እንደ ርኵስ የሚመለከቱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ፣ በፍጥረቱ ግን ርኵስ የሆነ ምንም ፍጥረት የለም ። ውሻን በጣም በመውደድ ደግሞ የታወቁ ሕዝቦች አሉ ። ዓመታዊ የውሾች በጀትም የአንድ ታዳጊ አገር በጀት የሚያህልበት አገር አለ ። 
ውሻ የሚያስተምረን ብዙ ነገር አለ ። በውሻ ላይ ካሉት ጠባያት፡-
1-  ያጫውታል፡- ስንጨነቅና ስንተክዝ ውሻ ሁኔታውን ለመለወጥ ጥረት ያደርጋል ። ንግግር ባልተለመደበት ቤት ውሻ ሲመጣ የቤተሰብ ወሬ ይጀመራል ። ውሻ የቤተሰብን ጸጥታ በመሻር መግባባትን ይፈጥራል ። የሰው ልጆችን ጭንቀት ለማቅለል ውሻን እንደ አንድ አጋር መጠቀም በሰለጠነው ዓለም እየተለመደ ነው ። 
2-  ፍቅርን ይሰጣል፡- ውሻ እስኪወዱት ጠብቆ ሳይሆን ቀድሞ ፍቅር ይሰጣል ። የሰው ልጅ ግን ከውሻ አንሶ እስኪወዱኝ አልወድም እያለ ይጠብቃል ። ፍቅርን ሰጥቶ ፍቅርን የመቀበል ጥበብን ከውሻ መማር ያስፈልጋል ። ልጆች ራስ ወዳድ እንዳይሆኑ ስለሌላው ማሰብን እንዲማሩ ዘመናዊ ዕቃ ገዝቶ ከመስጠት ውሻ ማሳደግ የተሻለ ነው ። ከዕቃ ጋር ያደገ ልጅ ዕቃ ወደ መሆንና ራስ ወዳድነትን ወደማቀንቀን ይሄዳል ። በመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ሚስቱና ልጆቹ ስሜቱ ሳይሰማቸው ውሻው ግን ጌታው እየመጣ እንደሆነ በማወቅ ዝግጅት ያደርጋል ። የሰውንም ስሜት በመጋራት የታወቀ እንስሳ ነው ።
3-  ታማኝነት፡- ውሻ አሳዳጊውን አይከዳም ፤ አንድ ቀን ያበላውን ዕድሜ ልኩን ይወደዋል ። ያ ሰው ቢጠላውና ቢያባርረው እንኳ የመጀመሪውን ቀን ደግነቱን በማሰብ ከአንጀቱ አይደለም ብሎ ይከተለዋል ። ጌታው ቢቸገር አብሮ በረሀብ ይሞታል ። የጌታው መቃብር ላይ ተኝቶ ዘመኑን ይፈጽማል ። ከጌታው ጋር እየሄደ ዙሪያውን በመቃኘት ጌታውን ይጠብቃል ። የጌታው ገዳይ ጠፍቶ የሚያገኘውና ደም የሚመልሰው ውሻ ነው ። ያበሉንን የምንነክስ የዛሬ ዘመን ሰዎች ታማኝነትን ከውሻ መማር ያስፈልገናል ። 
4-  ለሕገ እግዚአብሔር ዘብ ይቆማል፡- አትስረቅ የሚለው ሕግ የተሰጠው ለሰው ነው ። ሌባ ሲገባ ግን የሚጮኸው ውሻ ነው ። ውሻ ሕገ አግዚአብሔር ይከበር ሲል ሰው ግን የእርሱ ያልሆነውን ንብረት ይሰርቃል ። ውሻ ሊሰለጥን የሚችል እንስሳ ነው ። በዚህ ወንጀልን በመከላከል አመርቂ ውጤት እያስገኘ ነው ። አሸባሪዎችን ፣ ነፍሰ ገዳዮችን ፣ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በማደን ሥራ ውሻ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ። 
5-  ጌታውን ብቻ ያውቃል፡- “ውሻ ጌታውን እንጂ የጌታውን ጌታ አያውቅም” ይባላል ። ያንተ ውሻ አንተን ሲያውቅ አለቃህ ቢመጣ ግን ይጮኽበታል ። ውሻ አንድ ጌታ ነው የሚያውቀው ። እኛም አንድ ጌታ ክርስቶስን ስለማወቅ ልንማር ይገባናል ። 
ውሻ ለሰው የታመነውን ያህል ሰው ለእግዚአብሔር አልታመነም ። ውሻ በቁራሽ እንጀራ እንዲህ ሲታመን ሰው ግን የእግዚአብሔር ልጅ ሞቶለት አለመታመኑ ይደንቃል ።
ጌታ ሆይ ፣ ዘመናዊነት ከመሰለን ከዳተኝነት እባክህ አድነን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 
ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
እውነት 7
ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ይባርካችሁ !
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም