የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር . . .!!!

                                    የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ… ዓርብ፣ ሚያዚያ 10/ 2006 ዓ.ም.

                     

ለዚህ ጹሑፍ የመረጥኩት የእውቁ ሰአሊና ባለ ቅኔ የገብረ ክርስቶስ ደስታ ‹‹ጎልጎታ›› በሚል ርዕስ የሰጠው የጌታ ስነ ስቅለት ምስል፡- ገ/ክርስቶስ በትምህርትና በስደት ሕይወት ለረጅም ዓመታት በውጩ ዓለም በቆየበት ጊዜ በአውሮፓውያኑ ነጮች ዘንድ ለአፍሪካውያንና ለጥቁር ሕዝቦች ያላቸውን ዘረኝነትና ንቀት እንዲሁም ጥቁር በምንም ዓይነት ከነጮች ጋር በእኩልነት ሊመደብ የሚያስችለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊም ሆነ ፖለቲካዊ ስብእና የለውም በሚለው እሳቤያቸውና ከዛም አልፎ ‹‹እግዚአብሔር ነጭ›› እንደሆነ በድፍረት በሚሰብኩበት ሁናቴ በእጅጉ ልቡ ተነክቶ ነበር ይህን ጎልጎታ ብሎ የሰየመውን የጥበብ ስራውን ሊያበረክትልን የቻለው በዚህም ድንቅ የጥብብ ሥራው ገብረ ክርስቶስ ለአውሮፓውያኑ፡-
‹‹… እናንተ እናመልከዋለን የምትሉት እግዚአብሔር ግን አፍሪካዊም አውሮፓዊም ያልሆነ፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ነገድ የሌለውና ቀለም የማይለይ ሁለተናው በፍቅር ደም የተጥለቀለቀ፣ በፍቅር የቆሰለ፣ ደምግባቱና ውበቱ ደም የጎረፈበት፣ በደም የተረጨ፣ በደም የታተመና በክቡር ደሙ ፈሳሽነትም ለአባቱ ሰዎችን ሁሉ ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ የዋጀ ሕያው ፍቅር ነው፡፡ ይህ ፍቅር ደግሞ ዘር፣ ጎሳ፣ ቀለም፣ ዜግነት ሳይል ሁሉንም በእኩልነት የሚያፈቅር እንጂ እናንተ እንደምታስቡት እግዚአብሔር ነጭ አይደለም…፡፡›› ሲል ገ/ክርስቶስ ይህን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን ኢየሱስን የቀራኒዮውን ፍቅሩን በደም ጎርፍ፣ በደም ቀለም በሸራው ላይ በቡሩሹ ፍቅርን እንዲህ ተጠበበት… ‹‹ጎልጎታ›› የገብረ ክርስቶስ ዘመን አይሽሬ የሆነች በብዙዎችን ነፍስ አጥንትና ጅማት ድረስ ዘልቃ የፍቅርን ብርቱ ኃይልና ጽናት የምትገልጽ ሥራው እንደሆነች በሕይወቱ ዘመኑ ገልፆ ነበር፣ ዛሬም ድረስ በዚህ ክብሯና ሕያውነቷ ዘልቃለች ፍቅርን በደም እየተረከች፡፡


ይህም በደም የጸና የእግዚአብሔር ፍቅር ምሕረትን፣ ይቅርታን፣ በጎነትን፣ ቸርነትን፣ ርኅራኄን፣ ፍትህን፣ እውነትን፣ ፍርድን፣ ጽድቅንና በረከትን የተሞላ እንደሆነ በጎልጎታ ላይ ተገልጦ ለሁሉ ታይቷል፡፡ ይህ ፍቅር አሳልፎ ሊሰጠው በ30 ብር የተዋዋለውን ይሁዳን ሰላም ለአንተ ይሁን ወዳጄ ሆይ ብሎ በፍቅርና በርኅራኄ ተቀብሎ የሳመ ነው፣ ይህ ፍቅር ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ የካደውን የጴጥሮስንና ገንዘብ አምላኩ የሆነውን የይሁዳን እንኳን ሳይቀር በትህትና ዝቅ ብሎ እግራቸውን ሊያጥብ ያልተጸየፈና ያላመነታ ነው፣ ይህ ፍቅር ለጠላቶቹ፣ ለሚሳለቁበትና ለሚወጉት ሁሉ ምሕረትንና ይቅርታን የማለደ ነው፣ እንዲህ ሲል፡- ‹‹አባት ሆይ የሚሰሩትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው!›› ይህ ፍቅር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ በፍቅር ወንድሞቼ ብሎ ሊጠራን በእኛ በኃጢአተኞቹ ያላፈረብን ነው፡፡
ይህ ፍቅር የዘላለም ሕይወትን፣ ምሕረትን፣ ጽድቅን፣ ፍትህንና ፍርድን፣ ሐሴትንና ፍጹም ደስታን ለምድሪቱ ያጎናጸፈ ነው፡፡ በፋሲካ ሌሊትም በቤተ ክርስቲያን ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በማሕሌታቸውና በወረባቸው፡- ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፈሲካ ታሕፂባ በደም ክርስቶስ፡፡›› እያሉ ይህን ታላቅ የፍቅር ድል የምስራች ዜማ ለምድሪቱና ለፍጥረት ሁሉ በታላቅ ድምጽ ያሰማሉ፤ ‹‹ምድር ንጹሕ ክቡር በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ታጥባና ነጽታ በሐሴትና ፍጹም በሆነ ሰማያዊ ደስታ ፋሲካን ታከብረው›› ዘንድ ልዩ በሆነ ሰማያዊ ዜማ ፍቅርን፣ ሰላምንና ሕይወትን ያውጃሉ፡፡ ይህን ሕያው የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ዘወትር በመስበክ ቤተ ክርስቲያን ከኃይል ወደ ኃይል፣ ከክብር ወደ ክብር፣ ከድል ወደ ድል እየተሻገረች፣ የገሃነም ደጆችና የጨለማው ኃይላት ጭምር እንኳን ሳይቋቋሟት ሙሽራዋን ክርስቶስ ኢየሱስን በቅድስና እና በንጽህና ሆና በትዕግስት ጸንታ ትጠብቀዋለች፡፡
ይህን ጹሑፍ እያዘጋጀሁ ሳለ አንድ የጥንት ቅኔዎችን ስብስብ የያዘ መጽሐፍ ሳነብ ነበር፣ በዚህም መጽሐፍ ውስጥ የክርስቶስ ኢየሱስን ሞት የሚዘክር ድንቅ የሆነ በእጅጉ ከመሰጠኝና አእምሮዬን ካመራመረኝ ቅኔ ጋር ለደቂቃዎች ተፋጠጥኩ፣ ለዚህ ጹሑፍ ይሆነኝም ዘንድ መረጥኩት፣ እንዲህ ይላል ቅኔው፡-
ፍቅረ ብእሲት ወወይን ሞተ ናቡቴ፣          
ወለኦርዮ ቅትለቱ፡፡                           
ሞተ ወልድሰ የዋህ፣                          
እንበለ ክልኤሆን በከንቱ፡፡                   
እንበለ ክልኤሆን ሞተ፣                       
ከመ ኢንበል ባሕቱ፡፡                         
ቤተ እስራኤል ኅሩይ ዓፀደ ወይኑ፣
ወቤተ ክርስቲያን መርዓቱ፡፡ [1]  
                
ትርጓሜ፡- የናቡቴ ሞት የወይን ርስቱን ስለመውደዱ ነው
          የኦርዮም መገደል ስለ ሴት (ሚስቱን) ስለመውደዱ ነው፡፡
 የወልድ የዋህ ግን ያለሁለቱ በከንቱ ነው
ነገር ግን ያለሁለቱ ሞተ እንዳንል፡፡
        የየዋህ ወልድ ሞት ለተመረጠ የወይን ርስቱ (ለእስራኤል)
እና ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናን (ለሙሽራው) ነውና፡፡
(ዕዝል ክብር ይእቲ ቅኔ ዘአለቃ ተክለ ጽዮን)
ብዙዎች እንደሚስማሙበት ቅኔ በቤተ ክርስቲያናችን ለምስጋናና ለውዳሴ የሚውል ጥልቅ ምስጢርና ትርጓሜ ያለው ነው፡፡ እውቁ የማኅበረሰብ ሳይንስ ምሁር አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን Wax and Gold በሚለው መጽሐፉ:- ‹‹ቅኔ ለኢትዮጵያ ረቂቅ መንፈሳዊ ባሕሏ ነው፡፡›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡[2] በዓለማዊው የስነ ጹሑፍ መድረክም ቢሆን ቅኔ የረጅም ዘመን ታሪክና ክብር ያለው የስነ ጹሑፍ ዘርፍ ነው፡፡
በዚሁ የሀገራችን ሀብትና ሕያው ቅርስ በሆነው ቅኔ አባቶቻችን ጥልቅ የሆነ ምስጢርንና መልእክትን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር አስተላልፈውልናል፡፡ የጌታን ስቅለት፣ መከራውን፣ ሞቱንና ትንሳኤውን በምናስብበትና በምናከብርበት በዚህ ወቅት ከላይ በጠቀስነው በአለቃ ተክለ ጽዮን ቅኔ ውስጥ ልብን በሚመስጥ ሁኔታ የክርስቶስ ኢየሱስ ሞት በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩት ሁለት ሰዎች የአሟሟት ምክንያት ጋር ተነፃፅሮ የቀረበበት ቅኔያዊ ምስጢር በእጅጉ የሚደንቅ፣ ነፍስ ድረስ ዘልቆ የሚሰማ፣ አጥንትንና ጅማትን ሁሉ የሚሰረስር ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
እንደ ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ገለጻ እስራኤላዊው ናቡቴ የአባቶቼ ርስት የሆነውን የወይን ቦታውን አልሰጥም፣ እምቢኝ አሻፈረኝ በማለቱ በኤልዛቤል ምክርና ውሳኔ በግፍ ተገድሎ ደሙ በከንቱ እንዲፈስ ሆኗል፡፡ ሌላኛው በዚህ ቅኔ ውስጥ የተገለጸው እስራኤላዊው አርበኛ ኦርዮን ንጉሥ ዳዊት በሚስቱ ላይ በፈጸመው ዝሙት ምክንያት ይህንን ኃጢአቱን ለመሸፈን ሲል በወሰደው እርምጃ ከወድ ባለቤቱ ጋር እንዲተኛ ቢያስገድደውም ታቦተ ጽዮን በጦር አውድማ ባለችበት ሠራዊቱም ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ በሚተናናቅበት በዚህ ቀውጢ ወቅት ይህን አላደርገውም በማለቱ ከሚስቱ የተነሳ በንጉሥ ቀጭን ትዕዛዝ ለሞት እንዲዳረግ ሆኗል፡፡
ነገር ግን ይሉናል አለቃ ተክለ ጽዮን በቅኔያቸው፡- የየዋህ ወልድ (የእግዚአብሔር ልጅ) ሞት ግን ከእነዚህ ከሁለቱ ይለያል፡፡ የእርሱ ሞት ለተመረጡ የወይን ግንድ ለሆኑት ለቤተ እስራኤልና ሙሽራው ለምትሆን ለቤተ ክርስቲያን ወይም ለምእመናን እንጂ፤ በማለት ለሁሉ ድንቅ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት፣ የቀራኒዮውን ውለታ፣ ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲህ በሚደንቅና በሚጥም መልኩ ገልጸውታል፡፡ የጥበብ ሰው የሆነው ገ/ክርስቶስ በስዕሉ የተጠበበበትና አለቃም በቅኔያቸው የተራቀቁበት ዘር፣ ነገድ፣ ቋንቋ ሳይለይ ሁሉን በክቡር ደሙ ፈሳሽነት ቤዛ የሆነንን ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔርን ነው፡፡ ሙሽራው ለምትሆን ለቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ነፍሱን እስከመስጠት የወደዳትን ፍጹም መውደድ የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ዮሐንስ ወልድ ነጎድጓድ በቅዳሴው፡-
‹‹በአንተ ሞት ስለዳነች ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ፣ አንተም በቀራኒዮ በፈሰሰ በክቡር ደምህ ነጻ ታወጣን ዘንድ፡፡ ስለ ሙሽራህ፣ ቤተ ክርስቲያን ስትል በደምህ ፍጹም ነጻ ታወጣትና ቅዱስ፣ ንጽህትና የከበረች ታደርጋት ዘንድ በሸንጎ ተጸፋህላት፡፡ በመስቀልህ ትታጠር፣ በመስቀልህም ትጠቀም ዘንድ ከጥፋት መኻል ወጥታ በሰማይ ወዳለ ሠርግ እስክትገባ ድረስ፡፡››[3] በማለት እግዚአብሔር ሙሽራው ለምትሆን ለቤተ ክርስቲን የገለጸውን ፍቅሩን ሲያደንቅና ሲያመሰጥር ሌላኛው የቤተ ክርስቲያን አባት የሆነው ዮሐንስ አፈወርቅ ደግሞ፡- ‹‹ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው፣ ይህን ያህል ሰው ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የአምላክን ልጅ ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም ድረስ አደረሰው፡፡››[4] በማለት የእግዚአብሔር ስለ ሰው የመሞቱ ምስጢር ከዘላለማዊውና ሕያው ከሆነ ፍቅሩ የተነሳ እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል፡- ‹‹ነፍሱን ከወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም፡፡›› ሲል ለሰው ልጆች ሁሉ ያለውን የፍቅሩን ብርታትና ጽናት ገልጾልናል፡፡
በዕለተ ስቅለትም ሆነ በፋሲካ በዓላችን የምንዘክረው የታረደው የፋሲካው ቅዱስ በግ፣ የቀራኒዮው ባለውለታችን ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ፣ ነፍስና ሥጋችንን እንዲገዛው ስንፈቅድለት ከወዳጆቻችን የሚያልፍ ለሚጠሉንና ለጠላቶቻችን ሁሉ የሚተርፈረፍ ፍቅር በውስጣችን ይበዛልናል፡፡ ሕግ ሁሉ በእነዚህ በሁለቱ ትዕዛዛት ይጠቃለላሉ ይለናል ቅዱስ መጽሐፍ፡- ‹‹እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹምም አሳብህ፣ በፍጹም ኃይልህ ወደድ፡፡ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ወደድ፡፡›› ምዕራባውያኑ ክርስቲያኖች አንድ ድንቅ አባባል አላቸው እንዲህ የምትል፡- ‹‹The Love for God is the Root; the Love for your neighbour is the Fruit.›› በእውነትም መጽሐፍ እንደሚል፡- ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፣ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል፡፡›› በእውነተኛ ፍቅር እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በመካከላችን ይሆናል፤ ከክርስቶስ ኢየሱስ የተሰጠችን ፊተኛይቱ ትዕዛዝም ይህች ናት፡- ‹‹እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ፡፡›

የክርስቶስ መስቀል ለኃጢአተኛው ዓለም የተፈጸመ ታላቅ የእግዚአብሔር ማዳን ነው። ይህም በዓመታዊ ዝክር ብቻ የምናስበው ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ለመጠራት የተወለድንበት የምጥ ሥፍራ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጸመ ባለ ጊዜ የእኛ ነገር ፍጻሜ እንዳገኘና ሊነገር የነበረው ተስፋ (መዳናችን) እንደተፈጸመ ይገልጣል፡፡ በቤተ ክርስቲያን እንዲህ የሚል ዝማሬ አለ፡-  መድኃኔዓለም አዳነን በማይሻር ቃሉ፣ ደስ ይበለን  እልል በሉ አዳነን በማይሻር ቃሉ፡፡ ይህን ዝማሬ በማስተዋል እንዘምረው ይሆን? አይመስለኝም፡፡ ይኸውም ገና በሞትና በሲኦል ፍርሃት እየተመላለስን የመስቀሉ ሥራ እኛን ካላሳረፈን የክርስትናችን ትርፍ ምንድነው? ሐዋርያው ግን የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና፡፡ (1ኛ ቆሮ 1፣18) ይለናል፡፡
መዳናችንን እርግጠኛ ካልሆንበት መስቀሉ ለእኛም ሞኝነት ነው፡፡ በዝማሬአችን አዳነን እያልን ከምን እንደዳንን? እንዴት እንደዳንን ካልገባን ምስክሮች ሳንሆን ማስታወቂያ ሰራተኞች ነን፡፡ እርሱ ግን ለደቀ መዛሙርቱ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ በማለት ነገራቸው ለዚህ ነው ጌታችን ያደረግሁላችሁን ታስታውላላችሁን? በማለት ደቀ መዛሙርቱን የጠየቃቸው እነርሱ በምሴተ ሐሙስ (በጸሎተ ሐሙስ) በመካከላቸው የፈጸመውን ታላቅ ትህትና አልተረዱም ነበር፤ እኛም የሚበልጠውን የመስቀሉን ፍቅር፣ የእርሱን ቤዛነት፣ የእኛን ደኅንነት ካላወቅን ይበልጥ ያላስተዋልን አንሆንምን? የመስቀሉም መልእክት ይኸው ነው፡፡ ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?
                                                            በፍቅር ለይኩን
                       መልካም የፋሲካ በዓል!!!

[1] ይኄይስ ወርቄ (መምህር)፡- ንባብ ወትርጓሜ ዘቅኔያት፡፡ አዕማደ ምሥጢራት፣ ንግድ ማተሚያ ቤት፣ 1960፡፡
[2] Levine, D.N., Wax and Gold: Traditional and Innovation in Ethiopian Culture. Chicago: University of Chicago, 1965.
[3] ተሰፋ ገብረ ሥላሴ፡- ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ገጽ ፺፯፣ ቁጥር ፶፪-፶፫፣ ጸሎተ አኮቴት፡፡ ዓሥራ አምስቱ፣ መጻሕፍተ ቅዳሴ፡፡ ከነሥነ ሥርዓቱና ከነሐተታው፡፡ ኪዳንና ሊጦን፣ መስተብቁዕና ዘይነግሥ፡፡ በግዕዝና በአማርኛ፡፡ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም፡፡
[4] ዝኒ ከማሁ፡፡ የዮሐንስ አፈወርቅ ቅዳሴ፣ ገጽ ፻፲፪ ቁጥር ፶፪-፶፫፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ