የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከጣራዬ በታች አትግባ/2/

“ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- ‘እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ’ ብሎ ፈጣን መልስ ሰጠኝ ። ባሪያዬን እወደውና እንከባከበው የነበረው ዝናን ፈልጌ ፣ ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው ሰው ለመባል ወድጄ አልነበረም ። ፍቅር የመጣብንና የሚወድቅብን ነገር ነው ። ፍቅር ከመዐርግ ፣ ከኑሮ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ፍቅር ከሞት በላይ አሸናፊ ነው ። ፍቅርን ኃያል ያሰኛት የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ እንዲሆን ግድ ስላለችው ነው ፣ በዚህም አላበቃችም እስከ ሞት አደረሰችው ። ከልጅነቴ ጀምሮ ሰውን ልንመራው እንጂ ልንገዛው አይገባም ብዬ አስብ ነበር ። በታላቋ ሮማ ስልጣኔ ውሾች ወደ ቤተ መንግሥት ተጠግተዋል ፣ ከነገሥታት ግብር ላይም ውሾችን ማየት የተለመደ ነው ። እንዲነገርልን የምንፈልገው ግን እንኳን ለሰው ለውሻም መብት ቆመናል የሚለው ነው ። እውነቱን ግን ስናየው የሰውን ቦታ ለውሾች ሰጥተን ራሳችንን እያታለልን መሆናችን ነው ። ሮማውያን የሰውን ዘር ሳይሆን ሮማዊ ሰውን ብቻ ያከብራሉ ። እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው ሳይሆን በቋንቋና በቤተሰብ የሚመስላቸውን ብቻ ይወዳሉ ። ለዚህ ነው የባሪያ ፍንገላ በግዛታችን እየበዛ የመጣው ። ሰው እንደ ከብት ታጉሮ ሲሸጥ ከማየት የበለጠ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ ? ባሪያዬን የምወደው ፣ ያገለገለኝን የማገለግለው ፣ ልጄ ብዬም የምጠራው የነጻነት አስተሳሰብ ከእኔና ከቤቴ ስለሚጀምር ነው ። በአደባባይ ስለ ነጻነት የሚያወሩ ቤታቸውን ግን ቅኝ የያዙ ብዙ ሰዎች አሉ ። ስለ ሴቶች ነጻነት እያወሩ በቤት ሚስታቸውን የሚያስጨንቁ ፣ ሰው እኩል ነው እያሉ ባሪያ የሚፈነግሉ አያሌ ናቸው ።

ክርስቶስም ‘እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ’ ሲለኝ ታላቅ ነገር በውስጤ ተሰማኝ ። እቤታችን ትተናቸው የመጣናቸውን ሕሙማን በክርስቶስ ፊት በጸሎት ስናቀርባቸው ፈውስን ያገኛሉ ። ያልተቀበልነው ስላልጸለይን ነው ። እግዚአብሔር ለእኔ ብለው ከሚለምኑት ለእገሌ ብለው ሲለምኑት ፈጥኖ ይሰማል ። ፍቅር ነውና በፍቅር ይለመናል ። ስለ ሰው መጸለይ ምክንያቱ ፍቅር ብቻ ነው ። እኔ ስለ ባሪያዬ አደባባይ ወጣሁ ፣ ክርስቶስ ደግም ባሪያዬን ሊፈውስ ወደ ጓዳዬ እመጣለሁ አለ ። እርሱ በእልፍኝ የለመኑትን በአደባባይ ይመልሳል ፣ በአደባባይ የለመኑትን በእልፍኝ ይመልሳል ። ችግሬ ከቤት ሳይወጣ ሊፈውስልኝ ሲችል ለምን ዛሬ በአደባባይ ፈወሰው ? ብዬ አሰብሁ ። በአንዱ ችግር ብዙዎችን ለማስተማር ነው ብዬ በአንደኛው ልቤ መለስሁ ። በክርስቶስ ንግግር ውስጥ ብዙ ነገሮችን ተማርሁ ። ‘እኔ’ ብሎ በመናገሩ ሙሴን ‘እኔ ነኝ’ ያለው እርሱ መሆኑ ታወሰኝ ። እኛ እኔ ብለን ብንናገርም የተናገርነውና የሆነው የተለያየ ነው ፤ እርሱ ግን እኔ ባዩ እርሱ ነው ። ‘አንተ ግን ያው አንተ ነህ’ ብዬ ዝቅ አልኩኝ ። ‘መጥቼ’ የሚለው ቃሉ ደግሞ እኔ ባዩ እርሱ ትሑት መሆኑን አሳየኝ ። ‘እፈውሰዋለሁ’ በማለቱ ደግሞ እርሱ የሚሞክር ሳይሆን የሚያድን መሆኑን ፣ ማዳኑም ሂደት የሌለበት ቅጽበታዊ እንደሆነ ገባኝ ። እርሱ አምላክ ካልሆነ በቀር እንዴት እንዲህ ሊል ይችላል ? 
ሴቷ ጋዜጠኛ ንግግሩን አቋረጠችው ። ስሜት ውስጥ ገባች ። የእርስዋ የታመመ የቤቷ ነገር ትዝ አላት ። ቃለ ምልልሱ ስብከትና የናፍቆት ወሬ መሰለ ። ‘እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ ማለቱ የሚገርም ነው ። ማዳንና አለማዳናቸው ሳይታወቅ ሐኪሞች ካልመጣችሁ ይላሉ ። ሄደንም በፍቅር ለመቀበል ይቸገራሉ ። ምን ዓይነት ትሑት አዳኝ ነው’ አለች ። እርሱም ቆይ ልቀጥልልሽ በማለት ትረካውን ፣ የተደረገለትን ቀጠለ ። የሚናገረው ስለራሱ መዳን ይመስል ነበር ። ከታማሚው የአስታማሚው በሽታ ይበረታል ፣ ፈውሱም ከተፈዋሹ የአስታማሚው ፈውስና ደስታ ይበልጣል ። በሽተኛውስ የሰጠውን የሚችልበት ጸጋ አብሮት አለ ። አስታማሚው ግን እምነት ካልረዳው በአሳብ ይወዘወዛል ፣ በግምት ይሰቃያል ፣ እንዲህ ቢሆንስ እያለ በጥንቆላ አሳብ ይጨነቃል ። መቶ አለቃው የተሟላ ቁመናና ዲሲፕሊን ብቻ ሳይሆን የንግግር ችሎታም የነበረው ፣ እያስረገጠ የሚናገር ፣ እየመጠነ የሚሰነዝር ነበር ።
‘እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ’ ሲለኝ ለእኔ ታላቅ ክብር ቢሆንም ሁለት ነገሮች ትዝ አሉኝ ። የመጀመሪያው እርሱ ይገባበት ዘንድ ቤቴን ብቁ ሁኖ አላገኘሁትም ። ሁለተኛው እርሱ ቻይ ነው ። ቃል ቢናገር ብላቴናዬ እንደሚፈወስ እርግጠኛ ነበርሁ ። ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናዬም ይፈወሳል አልኩት ። በእርሱ የቅድስና ብርሃን ፊት ስቆም ማንነቴ ታየኝ ። ፍቅሩም ለንስሐ ጋበዘኝ ። ከማንም ሰው ጋር በቅድስናም በኃጢአትም እኩል ነን ብዬ አምን ነበር ። አሁን ግን ፊቱን ሳያጠቁር የተቀበለኝን ፣ በሥልጣን ቃል በትሕትና ያናገረኝን ፣ ለእኔ ሕይወት ፣ ለሞቴ ሞት የሆነውን እርሱን ወደ ቤቴ በድፍረት መጋበዝ አቃተኝ ። ከጣራዬ በታች ብዙ ጨለማ አለ ። በደጅ ምኩራብ ያሠራ ፣ ሕዝባችንን የሚወድ እያሉ የአይሁድ ራቢዎች ቢያሞግሱኝም እኔ ግን በቤቴ የረካሁ አልነበርሁም ። በደጅ ብስቅም በቤቴ ግን ያንን ለመድገም አቅም ያንሰኝ ነበር ። እንደ ማሽላ እያረሩ መሳቅ የእኔ መገለጫ ነበር ። ኑሮዬን ገነት ላደርገው እፈልጋለሁ ። ጥሩ ሰው መሆን ግን ላለመጎዳት ዋስትና አይሆንም ። እንደውም መልካም ሰው ስንሆን በብዙ ለመጎዳት ዝግጁ መሆን አለብን ። በዋጋ የሚያፈቅሩ በበዙበት ዓለም ነጻ ፍቅር ጥርጣሬ ውስጥ ይወድቃል ። ትዳሬ ከሰው ጋር ሳይሆን ከመልአክ ጋር የጀመርሁት ጉዞ አድርጌ ስዬው ነበር ። ከልኩ በላይ መጠበቄ ቤቴን የሁከት መድረክ አደረገው ። ከጣራዬ በታች ያሉ እንደ እኔ እንዲያስቡ እፈልግ ነበር ። እነርሱ ግን እንደ እኔ ሳይሆን እንደ ራሳቸው ናቸው ። እንደ እኔ እኔም አልሆንሁም ብዬ የምጽናናበት ጊዜ ብዙ ነው ።
ደግሞም የራሴን ትንሽ ሥልጣን አስታወስሁና ጌታዬን ለምን አደክመዋለሁ ? አልኩኝ ። እኔ መቶ ሰው የማዘዝ አቅም አለኝ ። ና የምለው ይመጣል ሂድ የምለው ይሄዳል ። ጌታዬም በደዌያትና በአጋንንት ላይ ሥልጣን አለው ። ቄሣር ሮም ተቀምጦ ሶሪያ የሚያዋጋን በመገኘቱ ሳይሆን በቃሉ ነው ። ቃል ይህን ያህል አቅም ካለው የመለኮት ቃልማ የበለጠ አቅም አለው ብዬ አመንሁ ። ጌታዬም ይህን እምነቴን ሲሰማ ተደነቀ ። በእስራኤልም እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም አለ ። በእርሱ ስደነቅ ልቤ ጠነከረ ፣ መንፈሴ ጎለመሰ ፣ የተጫነኝ ቀንበር ተሰበረ ። ጌታዬ አድናቂ ነው ። በሚሰድቡኝ ካዘንሁ በሚያደንቀኝ ጌታ መደሰት አለብኝ ። እርሱ ደግሞ ክቦ መናድ አያውቅበትም ።
ብላቴናዬም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ ። ከቤቴ ስወጣ ቤቴ በኀዘን ድባብ ተውጦ ነበር ። አሁን ግን የደስታ ብርሃን ተለኩሶበት ገጠመኝ ። ብላቴናዬ ተፈወሰ ። ዛሬ ወደ ሮም እየገባሁ ሳለሁ ብዙ የሮም ወጣቶች በመንፈስ እንደ ታመሙ ተሰማኝ ። ወልዶ የሚደሰተውን ያህል ወልዶ የሚሰጋ እንዳለ ሰረገላውን ያከራየኝ ነጂ ነግሮኛል ። የእኔ ብላቴና የተፈወሰው በጸሎት ነው ። እነዚህም ወጣቶች የሚፈወሱት በጸሎት ነው ብዬ አምናለሁ ።
ጋዜጠኞቹ ዓይኖቻቸው በእንባ ተሞላ ። በዓይነቱ ልዩ የሆነውን ተአምር ለመዘገብ በመብቃታቸው ደስታቸው ልዩ ሆነ ። ገና ቤቱ ሳይገባ ስላደከሙት ምስጋና አቀረቡ ። እርሱ ግን የጌታዬን ማዳን ባወራሁ ቊጥር ኃይሌ ይታደሳል ፣ ጉልበት የሚጨርስ የዓለም ወሬ ነው አላቸው ።
ተፈጸመ
ሰኔ 11 ቀን 2011 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ