የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከፍ ካለው በላይ

የመጣው ሄደ፣ የሄደውም አይመጣም። የነገሠው ተሻረ ፣ የተሻረው ዳግም አይቀባም። የተሞገሰው ተረገመ፣ የተወገዘው ስሙ ያው ሆኖ ቀረ ። ባለ ጠጎች ደኸዩ ፣ አለ የሚባል ጠፍቶ ነበር የሚል ቃል በምድር በረከተ። ጎዳናው ይወስዳል ይመልሳል፣ ሕይወት ግን ያንን ጓደኛ፣ ያንን ውብ ዘመን፣ ያንን ክብር፣ ያንን አንቱታ አትመልስም ። በዘመኑ ታላቁ እስክንድር ዓለም ፈራው ፣ ዛሬ ፈሪዎች አይፈሩትም። እግዚአብሔር ማነው ? ያለው ፈርዖን ሰጠመ ፣ እስካሁን ትንሣኤ አላገኘም ። አውሮፓ ዱር ሳለ ግሪክ አሰለጠነች፣ ዛሬ ግሪክ በዕዳ ተዘፍቃ ብዙ ረዳት ሊያቆማት አልቻለም ። የጰጰሱ ተሳሳቱ ሲባል ይወገዛሉ፣ አስኬማና በትረ ሙሴ መልሱ ይባላሉ ።

ቆንጆዎች ቆንጆ ነበርሁ ሲሉ ማን ያምናቸዋል? ያ ውበት ላይመለስ ጥላሸት ተቀብቷል ። ያ ተክለ ቁመና ፣ ያ እንደ ፀሐይ የሚያበራ ገላ ፣ ያ መሬት ለመርገጥ የሚጸየፍ እግር ዛሬ ጭቃ ላይ ተኝቷል ። ቤቱን ለደቂቃ የማያምነው ለዘላለም ጥሎት ሄዷል። የሚሳሳለትን ንብረት ዛሬ የማያውቀው ሰው ይጫወትበታል ። የሕይወት መንገድ መሄጃ እንጂ መመለሻ የለውም ። እኛ ወደ እነርሱ እንጂ እነርሱ ወደ እኛ አይመጡም። የዓለም ከፍታ በዝቅታ ፣ ዙፋን በመቃብር ፣ ዳኝነት በእስረኛነት ይለወጣል ። ያንተን ልዕልና ፣ አማኑኤል ሆይ ያንተን ክብር ካላሰቡ ልብን ያደክማል ።

ከፍታህ ዝቅታ የለውም፡፡ ነበረ ተብሎ ታሪክ አይነገርልህም። ሁልጊዜ ያው ነህ ። እንዳንተ የሸመገለ የለም፤ እንዳንተም አዲስ የለም ። መጀመሪያ ላይ ቆመህ መጨረሻውን ታውቃለህ፤ እያወቅህ ግን ዝም ትላለህ። ለድሀው እንጀራ ትሰጣለህ ፣ መልሶ ሲክድህ የሚያማልድ ሰባኪ ትልክበታለህ ። በልካችን አትከፍለንም ፣ በልክህ ታኖረናለህ ። መሰላል ላይ የወጡ ይወርዳሉ። በአየር ላይ የተንሳፈፉ መሬት ይናፍቃሉ ። ከፍ ካሉት በላይ ከፍ ያልከው አንተ ግን በማይነገር ቅድስና ትኖራለህ ። ለጠባይህ ዝቅታ ፣ ለዙፋንህ መናወጥ የለበትም ። የዛሬው አሸናፊ የሁልጊዜ አሸናፊ አይደለም ። የዛሬው ፈራጅ የሁልጊዜ ፈራጅ አይደለም ። የእኔ አምላክ ግን የማለፍን ሥርዓት ድል ትነሣለህ ። ሳትቀበል ትሰጣለህ ። ሳትሾም ትሾማለህ ። አዎ ከፍ ካሉት በላይ ከፍ ብለሃል ። ልዕልናህን ልዕልናህ ያመሰግናል ። በክረምቱ ዝናብ ነጠብጣብ ልክ ብትመሰገን ልክህ አይደለም ።

በምድር ላይ ያንተ ትልቅ ነገር እኛ ነን ። በሰማይና በምድር የእኛ ትልቅ አንተ ሁንልን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም .

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ