የትምህርቱ ርዕስ | ካልተመለሳችሁ

እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት አስቀድመን ስንፈጠር የተቀበልነው ስጦታ ነው ። ይህ መልክም በኃጢአት ቢጎሳቆል ጨርሶ የጠፋ አይደለም ። ይህ መልክ በሕፃንነት ዘመናችን ነበረ ። ኃጢአት ግን ከእኛ ጋር ያልተፈጠረ ፣ ቢያንስ አዳምና ሔዋን እስከ ሳቱበት ቀን ድረስ የማያውቁት ነው ። ኃጢአት በሕፃንነት ወራታችን የጎላ ፣ የደመቀ አልነበረም ። ሕፃናት ክንፎቻቸው የተደበቁ መላእክት ናቸውና ዘረኝነት አይታይባቸውም ። ስለዚህ በተፈጥሮአችን ቅዱሳን ነበርን ፣ በሐዲስ ተፈጥሮ እግዚአብሔርን ለመምሰል እንደገና በመስቀሉ ሥራ ተፈጠርን ። በሕፃንነታችን በቅድስና ጀመርን ። ላልተፈጠርንበት ኃጢአት ጉልበት ካለን ለተፈጠርንበት ቅድስና ጉልበት አለን ። ከሚፈታተነን ሰይጣን የሚረዳን መንፈስ ቅዱስ ይበልጣል ። ደግሞም ይህን የንጹሕነት ኑሮ በሕፃንነታችን ታይቶብናል ። ስናድግ ከረከስን አድገናል ማለት ያስቸግራል ። ሳይሰለጥን ደግ የነበረው ሲሰለጥን ክፉ ከሆነ ሰልጥኗል ከማለት ሰይጥኗል ማለት ይቀላል ። በርግጥ አድገናል ( በርግጥ ሰልጥነናል ( ብለን እንደገና መፈተሸ አለብን ። ያልተማረው በአንድነት እየኖረ የተማረው በዘረኝነት ጭስ ከታፈነ ፣ ለመጋደል ቀጠሮ ካስያዘ ተምሯል ማለት አስቸጋሪ ነው ። ትምህርት ያለው ሁልጊዜም የሚያንሱን ከሚመስሉት ነው ። ከሕፃናት ፣ ከደቀ መዛሙርት ፣ ከድሆች ትምህርት አለ ። የታሰሩት ፣ የታመሙት ፣ የተሰደዱት ብዙ የሚነግሩን ዕንቁ አሳቦች አሉ ። ከሚያንሱን ለመማር ትሑት መሆን አለብን ። “ምክር ከድሀ ነበርሽ ማን ቢሰማሽ” ይባላል ። ጌታችን፡- “እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” አለ (ማቴ. 18 ፡ 3) ።

መንግሥተ ሰማያት በማደግ ፣ ትልቅ ሰው በመባል ፣ አቅምን በማጠናከር አትገኝም ፣ በመመለስ እንደ ሕፃናት በመሆን ትወረሳለች እንጂ ። አካላዊ መመለስ ሳይሆን ምግባራዊ መመለስ ሊኖረን ይገባል ። ካልሆናችሁ አለ ፣ ካልመሰላችሁ አላለም ። የመሆን ሕይወት ነው ። በየዋሃን ከተማ ብልጥ መሆን ባይተዋር መሆን ነው ። መንግሥተ ሰማያት ልብሳቸውን በበጉ ደም ያጠቡ የየዋሃን ከተማ ናት ። በብልጠት ብንገባ እንኳ ፈጥነን እንወጣለን ። ስላጣናቸው ነገሮች በዝርዝር መናገር እንወዳለን ፣ በትልቁ ያጣነው የሕፃንነትን ቅንነት ነው ። ሕፃናት በሚናገሩትና በሚያስቡት መካከል ምንም ልዩነት የለም ። ማደግ ግን በምንታዌ ማንነት እንድንሰቃይና እንድናሰቃይ አድርጎናል ። በሕይወት ውስጥ ጭንቀት የሚከሰተው የዘላለሙን ነገር እንደ ጊዜው ፣ የጊዜውን ነገር እንደ ዘላለሙ አድርጎ በመያዝ ነው ። ሕፃናት ስለ ሰማይ ከነገርናቸው አሁን ሄደው ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ይመኛሉ ። ብዙ ቃለ እግዚአብሔር የሚሰሙ ሕፃናት ልጆች ሰው ሲሞት “ታድሎ ከእኛ ቀድሞ ክርስቶስን ሊያይ ነው ይላሉ” እንጂ አያዝኑም ። ያስተማርናቸው ግን ያኛውን ሕይወት አናምነውም ። የሚደንቀው ሳናምን ያስተማርነው ብዙዎችን ማሳመኑ ነው ። እውነቱ የእኛ አይደለምና ሁልጊዜ ያሸንፋል ።

የወፍ ድምፅ በጣም ጣዕም አለው ፣ መልካቸውም ውብ ነው ። አጠገባችን መጥተው ዓይናችንን ፣ ጆሮአችንን ይማርኩታል ። ልንይዛቸው ስንል ፈጥነው ይበራሉ ። ዓለም ማለት ይህ ነው ። ከሰጪው ከእግዚአብሔር ውጭ የተሰጠን ነገር ሁሉ ተመላሽ ነው ። በዚህ ዓለም ያለውን ፣ ትልቅ የሚመስለውን ነገር ወይም የተሰጠንን ጸጋ ወደ ውስጣችን ከማስገባት በር ላይ አስቀምጦ መጠበቅ የተሻለ ነው ። ሲለየን ከሚፈጠረው ስቃይ የምንድነው የእኛ የሆነና አይሄድም የምንለው ምንም ነገር አለመኖሩን ስናምን ብቻ ነው ። ነገርን በልኩ ማየት ከሚፈጠር አደጋ ይታደጋል ። ሕፃናት ሁልጊዜ የሚመርጡት ትንሹን ነገር ነው ። ፋብሪካ ብንላቸው ከረሜላ ይሰጠኝ ይላሉ ። መንግሥትነት ብንላቸው ቀሚስ ይሻለኛል ይላሉ ። አሁን የሚጠቀሙበትን ነገር እንጂ የማይበሉትን ሁሉ አያጋብሱም ። የሚታየውን ሳይሆን የማይታየውን ተመልከቱ ተብሏል ። ሰይጣን ያልሰጠንን ነገር “ብታጣውስ?” እያለ ያስፈራራናል ፣ እግዚአብሔር ግን ስጦታው ቢሄድ እኔ አለሁ ይለናል ።

ካልተመለሳችሁ የሚለውን ቃል አስምሩበት ። በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ሲናገሩ እንደምንሰማው “እናንተ ኢትዮጵያውያን ምን ሆናችኋል ? የክርስቲያን አገር አልነበረም ወይ ? አሁን የምንሰማው ከባድ ነው” በማለት የተለያየ አገር ዜጎች ይጠይቃሉ ። ካልተመለስን ፣ ወደ ቀድሞው አንድነትና ፍቅር ካልመጣን በምድር እንታወካለን ፣ በሰማይ ርስት እናጣለን ። እስራኤል በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ከኢራን ጋር በነበራት የ11 ቀን ጦርነት ወደ 12 ቢሊየን ዶላር ወጪ አውጥታለች ። በእያንዳንዱ ቀን አንድ ቢሊየን ዶላር ወጪ ነበራት ። ይህ ዋጋ የማይተመንለት የሰው ሕይወት ፣ የሚታወከው ዜጋ ሳይቆጠር ነው ። የሰላም ወጪው ትንሽ ነው ፣ የጦርነት ወጪ ግን ብዙ ነው ። እናንተ ኢትዮጵያውያን ምን ሆናችኋል? የሰላም ወጪው ትንሽ ነው ፣ ካልተመለሳችሁ አትድኑም እየተባልን ይመስላል ።

እናንተ ባለትዳሮች የሰርጋችሁ ቀን በጣም ታምሩ ነበር ። ለክርስትና ስንመጣ ፍቅራችሁ ያስቀና ነበር ። አንዳችሁ ላንዳችሁ የመሰከራችሁት ልዩ ነበር ። ምን ሆናችኋል ? ካልተመለሳችሁ …። አንተ ወንድሜ ደግ ነበርህ ፣ አንቺ እኅቴ ሰው ትወጂ ነበር ። አሁን ምን ሆናችኋል? ካልተመለሳችሁ…።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ