“ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።” (መዝ. 45፡2 ።)
የዓለምን ከንቱነት ለመግለጥ የአገራችን ሰዎች እንዲህ ብለው ይገጥማሉ፡-
ምን ጌታ ቢሆኑ ፣ ባለ ዋርዳ በቅሎ ፣ ባለ ማር እሸት ፣
አሽከር ቢያደገድግ ፣ ቀንና ሌሊት ፣
ድጓ ቢተረጎም ፣ ቢነበብ ዳዊት ፣
በቅሎ ቢያሰግሩት ፣ ተጎንደር ይፋት
መቅረቱን አይቀርም ክረምትና ሞት ።
ክረምት ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል ፣ ይቀራል ተብሎ አይታሰብም ። ሞትም እንደ ክረምት በጊዜው ይመጣል ። ቢዘገይም ይቀራል ተብሎ አይታመንም ። የትኛውም የኑሮ ደረጃ ሞትን አያስቀረውም ። ሁሉም ወደዚያው ነው ። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ውጭ ስሜ ትልቅ ነው ፣ ጀርባዬ ጥብቅ ነው ፣ ጎተራዬ ሙሉ ፣ አሽከሬ እልፍ ነው ብሎ መመካት አይገባም ። በማንኛውም ጊዜ ተነሥቼ ከአዲስ አበባ ኒውዮርክ ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የምበርር ነኝ ብለን ብንመካም ከሞት የሚሸሽግ ዋሻ እስካሁን አልተገኘም ። ክረምት የደረቀውን መሬት ያረሰርሳል ፣ ሞትም ጻድቃንን ከወዳጅ እግዚአብሔር ጋር ያገናኛል ። ያን ቀንም እንባ ከዓይን ይታበሳል !
በዚህ ዓለም ላይ ከሚያደናግሩ ነገሮች አንዱ የተራሮች መሰወር ነው ። ነቢዩ፡- “ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ብሏል ። በእስራኤል ዘንድ ትልቁ ተራራ ፣ የክብር ሰው ዳዊት ነው ። ዳዊትም ተራሮች ነበሩት ። ሰዎች “የእኔ ጀግና እገሌ ነው ፣ የእኔ ምሳሌ እገሊት ናት” ይላሉ ። እንደ ተራራ የገዘፉ ፣ ከሩቅ የሚታዩ ፣ ይጎድላሉ ተብለው የማይሰጉ ፣ የተጠለላቸውን የማያስነኩ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ። ተራሮች የሚሰወሩበት ጊዜ ግን ጥቂት አይደለም ። በጉቦና በሌብነት ምክንያት ተሠሩ የተባሉ ሕንፃዎች ይሰወራሉ ። በውኃ ጥም ሲሰቃዩ የነበሩ የገጠር ሰዎችን ለማርካት የተቆፈሩ የውኃ ጉድጓዶች ይሰወራሉ ። በእርዳታ የተቆፈረ አንድ የውኃ ጉድጓድን ለመመረቅ ሄደን “እዚህ ጋ ነበረ” ብለውን አዝነን ተመልሰናል ። ለሌለው ጉድጓድ ግን ከመጠን ያለፈ ገንዘብ ወጪ ሆኗል ። ያን ቀን የተሰማኝ ሐፍረት ፣ አየሩን ሳይቀር ፈርቼ ተመልሻለሁ ። የጋበዙኝም ጭው ብለው እነርሱን ለማጽናናት ሞክሬአለሁ ። ሕንፃ ሲሰወር ፣ የውኃ ጉድጓዶች ሲጠፉ “የት ነው ያለሁት ? በሕልሜ ነው ወይስ በውኔ ?” ያሰኛል ። ብዙ ያወራንለት ነገር ፣ ለምርቃት ሰው የጋበዝንበት የእጃችን ፍሬ ምትሐት ሆኖ ሲሰወር በሐፍረት አንገት ያስደፋል ።
የእንጦጦ ተራራን ሽቅብ ስናየው እንውላለን ። ይህ ተራራ ድንገት ቢሰወርና ከጀርባው ያለ ከተማ ቢታየን ከመደሰት እንደነግጣለን ። የከፍታዎች መለኪያ ሲጠራ “ከባሕር ጠለል በላይ…” ተብሎ ነው ። አሁን ግን ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ተሰወሩ ። ብዙ ሰው የገዛ አእምሮውን የሚጠራጠረው ፣ አለሁ ወይስ የለሁም ብሎ ራሱን የሚደበድበው ተራሮች ሲሰወሩበት ነው ። ቆይ መጣሁ ብለውን ገብተው ፣ በገቡበት ቤት በጓሮ በር የጠፉ ሰዎች ቆመን እንድንውል ፣ በኀዘን እንድንጎዳ አድርገውናል ። ለአገር ምሳሌ ፣ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑ ሰዎች ከስፍራቸው ሲታጡ ደንግጠናል ። በዝምታቸው የምናከብራቸው ሲናገሩ “ምነው ዝም ብለው በቀሩ” ብለናል ። እንደ ተራራ የገዘፉብን ብዙ ሰዎች ናቸው ። ከቦታቸው ታጥተው ወንዝ ለወንዝ ሲሄዱ ፣ በጎሣ በሽታ ሲለከፉ እናዝናለን ። ብዙ ያወራንላቸው ፣ “የእኔ ትልቅ” ብለን የእወቁልኝ ማስታወቂያ የሠራንላቸው አንሰው ሲገኙ ፣ ከእነርሱ መውረድ በላይ የእኛ ማመን ያበሳጨናል ።
ይህ ዘመን ተራሮች የሚሰወሩበት ዘመን ነው ። መደልደል ቢሆን እሺ እንላለን ። ወደ ባሕር ልብ ፣ ከልኬት ቍጥር ውጭ ሲሆኑብን ዓለምን እንፈራለን ። ፈላስፎችን የተከተሉ ፣ ምድራዊ ዝነኞችን ያፈቀሩ ፣ በውጫዊ ነገር ለሰው የዘፈኑ ይደነግጣሉ ፣ ይፈራሉ ። ሁሉ ሲንሸራተት ፣ በከፍታው ነዋሪ የሆነ ፣ የዘመናት ዘመን የሆነ ፣ ለዘመኑ ዘመን የሌለው መድኃኔ ዓለም ግን ከፍርሃት ያድናል ። የታመናቸው ሊጥሉን ፣ ያየናቸው ሊሰወሩብን ይችላሉ ። የእውነት መዝገበ ቃላት ያደረግናቸው ፣ “እነርሱ ካሉማ ጨለማም ብርሃን ነው” ብለን የዘመርንላቸው ሊሰወሩ ፣ ሊታጠፉ ፣ በበሉበት ግብር ሊቀሩ ይችላሉ ። ክርስቶስን ካላየን ከክርስቶስ ርስት መድረስ አይቻልም ። የነፍስ መንገድ ረጅም ነውና እርሱን ብቻ መሪ ካላደረግን ፍርሃት ቶሎ ይከበናል ። እግዚአብሔር ረዳታችን ከሆነ ግን ያመነው ቢከዳን ፣ ያከበርነው ቢያዋርደን ጉዞው ይቀጥላል ።
“ልብ እየጠበበ ጨጓራ ሲሰፋ ፣
ታዋቂ ሰው በዝቶ አዋቂ ሰው ጠፋ ።”
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም.